የማዕድን ቦታ እንዲያስረክቡ የታዘዙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከኦሮሚያ ጋር በመደራደር ይዞታቸውን አስከበሩ

የማዕድን ቦታ እንዲያስረክቡ የታዘዙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከኦሮሚያ ጋር በመደራደር ይዞታቸውን አስከበሩ

ARE  THEY BEING INTIMIDATED?

Wow amazing !! There are some business negotiators who believe that the way to “win” a negotiation is by intimidating the other party. These people are trying to put you on the defensive.

ሐበሻ ሲሚንቶ ረቡዕ ይመረቃል

(Ethiopian Reporter) -የኦሮሚያ ክልል በጀመረው ‹‹የኢኮኖሚ አብዮት›› ምክንያት ለጥሬ ዕቃ ማውጫ የሚገለገሉባቸውን የማዕድን ሥፍራዎች እንዲያስረክቡ የታዘዙት ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ከክልሉ መንግሥት ጋር ባካሄዱት ረዥም ጊዜ የወሰደ ድርድር ተጨማሪ ገንዘብ በመክፈል ይዞታቸውን አስከበሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ 90 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የሚገኙትንና የአገሪቱን የሲሚንቶ ገበያ በውድድር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ የቻሉት ደርባ፣ ዳንጎቴና ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ባካሄዱት ድርድር የጥሬ ዕቃ ማውጫ የማዕድን ሥፍራቸውን ማስጠበቅ ችለዋል፡፡

ኩባንያዎቹ በተናጠል ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር ባካሄዱት ድርድር በአንድ ሜትር ኪዩብ ፑሚስ 20 ብር ለመክፈል በመስማማት፣ ከቁጥጥራቸው ውጪ ሊሆኑ የነበሩትን የማዕድን ሥፍራዎች ዳግም በይዞታቸው ሥር እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ምንጮች ጨምረው እንደገለጹት የእነዚህ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የጥሬ ዕቃ አቅርቦት መዛነፍ ስለሌለበትና ጥራቱም የተጠበ ሆኖ እንዲቀጥል፣ ዋጋውም ከዋዠቀ ውድድሩን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው ከይዞታቸው መውጣት እንደሌለባቸው ፋብሪካዎቹ ከክልሉ ጋር ምክክር በማድረግ ስምምነት ላይ መድረስ መቻላቸው ታውቋል፡፡

የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ፣ ‹‹እኛ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በተነደፈው የሥራ ዕድል ፈጠራ የመፍትሔው አካል መሆን እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ በአንድ ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ክፍያ ለመፈጸም ተስማምተናል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የገነቡት ደርባና ዳንጎቴ፣ እንዲሁም ከነባሩ በተጨማሪ ሰፊ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የገነባው ሙገር ሲሚንቶ የአገሪቱን የሲሚንቶ ገበያ ድርሻ በበላይነት ይመራሉ፡፡

ነገር ግን ለመክፈል በተስማሙት አዲስ የጥሬ ዕቃ ክፍያ የማምረቻ ወጪያቸው ላይ ችግር ስለሚኖረው፣ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ይገምታሉ፡፡

አቶ ኃይሌ እንዳሉት ግን፣ በአሁኑ ወቅት ምንም የታሰበ የሲሚንቶ ዋጋ ጭማሪ አይኖርም፡፡ የማምረቻ ዋጋ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለማወቅ የተወሰነ ጊዜ ይወስዳል ብለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኘው የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ያስገነባው ፋብሪካ፣ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ተመርቆ ወደ ገበያ እንደሚገባ ቀን ተቆርጧል፡፡

ለኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ ፈር የቀደደውና ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ የቻለው ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር፣ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች ከሆኑት ፒፒሲና አይአይዲ ጋር እኩል 50 በመቶ ድርሻ በመያዝ የሲሚንቶ ፋብሪካውን ግንባታ አጠናቋል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለዚህ ፕሮጀክት 945 ሚሊዮን ብር ብድር አቅርቧል፡፡ ሐበሻ ሲሚንቶ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በዓመት 1.4 ሚሊዮን ቶን የማመረት አቅም ሲኖረው፣ ማምረት የሚጀምረው የአቅሙን 83 በመቶ ያህል ነው ተብሏል፡፡

ይህ ፋብሪካ ወደ ምርት የሚገባው የኦሮሚያ ክልል የ‹‹ኢኮኖሚ አብዮት›› ከጀመረ በኋላ እንደመሆኑ፣ ክልላዊ መንግሥቱ ባስቀመጠው መንገድ መሄድን መርጧል፡፡

የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አቢ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ፑሚስ የጥሬ ዕቃ ማምረቻ ቦታ ለማግኘት ተንቀሳቅሶ ነበር፡፡ ነገር ግን ለተነሽዎች ካሳ ባለመክፈሉ ቦታውን መረከብ ባለመቻሉ፣ የኦሮሚያ ክልል አዲስ አሠራር ማምጣቱን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

‹‹ሐበሻ ሲሚንቶ ለወጣቶች ከተሰጠው ማምረቻ ጥሬ ዕቃ በመረከብ ወደ ምርት ይገባል፤›› ሲሉ አቶ መስፍን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ እንደሚመረቅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡