የምርጫ ቦርድ ማሻሻያና የብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት ምንና ምን ናቸው?

የምርጫ ቦርድ ማሻሻያና የብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት ምንና ምን ናቸው?

SIMON MAINA

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የተለያዩ ህጎችን ለማሻሻል ይረዳ ዘንድ የፍትህና የህግ ስርዓት ማሻሻያ ምክር ቤት ካቋቋሙ ቆየት ብሏል።

በዚህ ምክር ቤት ስር ደግሞ ምርጫ ቦርድና የምርጫ ህግን ማሻሻል፤ በተጨማሪ እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እንባ ጠባቂ ተቋምና ፌደሬሽን ምክር ቤት ያሉትን ተቋማዊ ይዘታቸውን መፈተሽ ላይ የሚሠራ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት የተሰኘ ቡድን ተቋቁሟል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ የምርጫ ህጉና ምርጫ ቦርድን የማሻሻሉ ነገር ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ተብሎ ቡድኑ እዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሆነ ይናገራሉ።

ቡድኑ እንደ ሃሳብ እየተወያየባቸው ካሉ ነገሮች የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርጦ በፓርላማው ከሚፀድቅ ይልቅ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተሳትፎ ኖሯቸው የሚመረጥ ሰው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢቀርብና ከዚያ ወደ ፓርላማ ቢሄድ የሚለው አንዱ ነው።

• ወሎ በነዳጅ ‘ልትባረክ’ ይሆን?

ተቋሙን ከቦርድነት ወደ ኮሚሽን ማሸጋገርም ሌላው በቡድኑ ውስጥ የተነሳ ሃሳብ ነው። እነዚህና ሌሎች ነገሮች ላይ ለመምከርም ቡድኑ ቀጠሮ ይዟል።

የቦርዱ አባላት ሁኔታና ሌሎች ነገሮችም የተመለከቱበትን የምርጫ ህግን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ ለማሻሻል እየሰሩ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የቦርዱን ሰብሳቢ ጨምሮ የአባላቱን አሿሿም በሚመለከት በህገ መንግስቱ ላይ የተወሰኑ መመሪያዎች ሲኖሩ በአዋጅ የተቀመጡ ሌሎች መመሪያዎችም አሉ።

ምርጫ ቦርድንና ምርጫን የሚመለከቱ ህጎች ላለፉት ዓመታት መንግስትና ተቃዋሚዎችን ሲያጨቃጭቁ እንደነበር ይታወቃል።

አንዳንድ ድንጋጌዎች እንዲሁም ከተቋሙ ውጪ ያሉ የሚያከራክሩ ሌሎች ህጎችም ስላሉ ምርጫ ቦርድን ብቻ ሳይሆን ምርጫ ቦርዱና ምርጫ የሚመራበትን አጠቃላይ የህግ ማዕቀፍ ለማሻሻል እየሠሩ እንደሆነም ዶ/ር ጌታቸው ያስረዳሉ።

• ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ዘመቻው ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው?

ብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት. . .

ቡድኑ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ምርጫ በሚመለከት የሰብሳቢ ሹመት በተቃዋሚዎችና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይሁን የሚለው ሃሳቡ ወደ ተግባር ሳይገባ የቀድሞ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው ሊሾሙ መሆኑን በሚመለከት ለዶ/ር ጌታቸው ጥያቄ አንስተናል።

“እኛ ገና ያቀረብነው ነገር የለም አማራጮችን እያየን ነው” በማለት እንዲሁ እንደ ህግ ባለሙያ ነገሩን እንዴት እንደሚመለከቱት ግን ይገልፃሉ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ከተያዘ ተሿሚውን አቅራቢው የዚያ ፓርቲ መሪ ወይም በፓርቲው የተመረጠ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው። ምክር ቤቱም በዚያ ፓርቲ ቁጥጥር ስር ያለ ስለሚሆን የህግ አውጪውና ህግ አስፈፃሚው የእርስ በእርስ ክትትልና ቁጥጥር እንደማይኖር በመግለፅ “በእኛ ነባራዊ ሁኔታ ይህን የሚያስቀር ስርዓት ያስፈልጋል፤ በተቻለ መጠን ሰፊውን ባለድርሻ የሚያስማማ አካሄድ ይኑር ነው ሃሳባችን” ይላሉ።

ባለፉት ዓመታት ምርጫ ቦርድ ላይ እንደ ትልቅ ጉድለት ይነሳ የነበረው ገለልተኛ ያለመሆን ችግር ነበር።

ወ/ት ብርቱካን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር ሹመታቸውን ዶ/ር ጌታቸው እንዴት ይመለከቱታል?

ምንም እንኳ ስለ መሾማቸው በእርግጠኝነት የሚያውቁት ነገር ባይኖርም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል (አስተያየታቸው የቡድኑን አቋም አያንፀባርቅም።)

“ስርዓት የሚበጀውና መስፈርት የሚቀመጠው ለአንድ ሰው አይደለም። ወሳኝ መሆን ያለበት እሷ ያለፈችበትና የነበራት ሃላፊነት ሳይሆን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ተቀባይነት ያለው ህግ ማስቀመጥ ነው” በማለት ያጠቃልላሉ።

• ብርቱካን ሚደቅሳ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እንደሚሾሙ ይጠበቃል