‹‹የምርጫ ቅድመ ዝግጅት የጊዜ መጣበብ እንዳይፈጠር ሰግቻለሁ›› ምርጫ ቦርድ

‹‹የምርጫ ቅድመ ዝግጅት የጊዜ መጣበብ እንዳይፈጠር ሰግቻለሁ›› ምርጫ ቦርድ

የዝግጅቱ ማፋጠንም ሆነ ማጓተት በመንግሥት እጅ መሆኑ ተገለጸ

 

(press.et)—-አዲስአበባ፡- በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየቀረቡ ያሉ የተለያዩ አጀንዳዎች በ2012 በጀት ዓመት በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ሥራው ላይ የጊዜ መጣበብ ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት እንዳደረበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የምርጫ የዝግጅት ጊዜውን ማጓተትም ሆነ ማፋጠን በመንግሥት እጅ እንደሆነም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አስታውቀዋል፡፡

የቦርዱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የቦርድ አደረጃጀትና የሕግ ማሻሻያን ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየቀረቡ ናቸው፡፡ የቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጣቸው ቅድመ ዝግጅቱን ማካሄድ ደግሞ አይቻልም፡፡ በማሻሻያው መሰረትም አደረጃጀቱ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ስለሚኖሩ ምርጫውን በቴክኖሎጂ ታግዞ ለማካሄድና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ የጊዜ መጣበብ ውጥረት ይፈጥራሉ፡፡

እየተጋገዙና እየተደማመጡ መሄድ ከተቻለ የጊዜ መጣበብንና መጨናነቅን ማስቀረት ይቻላል ያሉት አቶ ነጋ ፣ ምርጫ ቦርድ ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠትና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምዝገባ በማካሄድ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት ለማስፈጸም እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በህግ መፈታት ያለበት ደግሞ በመንግስት እንደሚታይ አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ በሀገሪቷ እንዲካሄድና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደገና እንዲዋቀር ላለፉት 20 ዓመታት ፓርቲያቸው ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበርና አሁንም ይህንኑ እያቀረበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መንግስት ፍላጎት ካለው ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች ተቀብሎ ወደሥራ መግባት እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

ማሻሻያዎችን ለማካሄድ ምክክሮች መጀመራቸውንና ምክክሮቹ በፍጥነት እንዲካሄዱ በማድረግ ወደ ሥራ መግባት የመንግሥት ድርሻ

እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ ነገር ካለ የማይቀበሉበት ሁኔታ እንደሌለም ገልጸዋል፡፡

በገዥው ፓርቲ ድጋፍ የሚደረግላቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶክተር መረራ፣ በምክክር ወቅትም ገንቢና አዲስ ሃሳብ ይዘው እንደማይቀርቡና ጉዞውን ማራዘም የሚፈልጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ ለምርጫ የሚደረገውን ዝግጅት ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያዘገዩበት አግባብ አለመኖሩን ጠቁመው፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥያቄ የቆየና ነጻና ገለልተኛ ምርጫ የሚካሄድበት አግባብ ይመቻች የሚል ነው ብለዋል። ይህንንም ሃሳብ ፓርቲያቸው በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲያንጸባርቅና በጽሁፍም  ሲያቀርብ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ በመንግስት በኩል ዝግጁነቱ ካለ ጥያቄዎቹ ተፈትተው ወደ ስራ መግባት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባለፉት ዓመታት የሚያቀርባቸውን ምክንያቶች አሁንም ደግሞ እያቀረበ ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ፣ የምርጫ ሥርዓቱ እንዲሻሻል ፓርቲያቸው ግፊት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ምርጫ እየቀረበ ሲመጣ መጣደፍ እንዳይኖር ቀድመው የሚታወቁ ጥያቄዎችን ቶሎ እየፈቱ መሄድ ከአስፈጻሚ አካላት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ምርጫውን ለማካሄድ እስከ ምርጫ ጣቢያ ድረስ የሚሰየሙ የምርጫ አስፈጻሚዎች በምን መንገድ መሆን እንዳለበት ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ታች ድረስ ወርዶ ለማደራጀትም የአካባቢ ደህንነትን እያረጋገጡ መሄድ የራሱ ስራ እንደሚያስፈልገው ግንዛቤ ተይዞ ከወዲሁ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ግን በሀገሪቷ ያሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 90 ሲሆን ከእነዚህ በቦርዱ ተመዝግበው እውቅና ያላቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን 62 ብቻ እንደሆኑ ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011

በለምለም መንግሥቱ