የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ: የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምህረት አዋጅን አፀደቀ

የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ: የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምህረት አዋጅን አፀደቀ

(fanabc)—አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የምህረት አዋጁን በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል።

የምህረት አዋጁ በተዘረዘሩ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የተሳተፉና ለድርጊታቸው የተሰጠውን ተገቢ ተጠያቂነት በመሰረዝ፥ ወደ ህብረተሰቡ በመግባት በሃገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እድል የሚሰጥ ነው።

በተጨማሪም የፖለቲካ መብታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት መንግስት በወንጀል ተጠያቂ ሊያደርገን ይችላል በሚል ስጋት፥ ከሃገር ወጥተው በተለያዩ የዓለም ሃገራት የሚገኙ ዜጎች ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ያስችላልም ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በጥላቻና የእርስ በርስ ጥርጣሬን ለማስወገድ በመፈቃቀድና በአንድነት መንፈስ በተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት፥ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትም ሆነ ይቅር መባባልን ተግባራዊ በማድረግ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

አዋጁ ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት በተዘረዘሩ የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው በህግ የሚፈለጉም ሆነ ጉዳያቸው በምርመራ ሂደት ያለና የወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ወይም የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ምህረት የሚሰጥ ይሆናል።

ከዚህ ባለፈ ግን አዋጁ ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ ምህረትን የማይሰጥ መሆኑን የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ተናግረዋል።

በፀደቀው አዋጅ ላይ የኩብለላ ወንጀል ምክንያት የተከሰሱ የሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊት አባላት የነበሩ ስላሉ የኩብለላ ወንጀል ምህረት ከሚሰጥባቸው የወንጀል አይነቶች መካከል አንዱ እንዲሆን ተካቷል።

በአዋጁ መሰረትም ምህረት ያገኙ ሰዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን ካፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሪፖርት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ሪፖርት ያላደረገ ግለሰብ ወይም አካል መንግስት በልዩ ሁኔታ ካልወሰነ በስተቀር የምህረቱ ተጠቃሚ እንደማይሆን ተገልጿል።

የምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተለያዩ የወንጀል ድርጊት የተሳተፉ ሰዎች ምህረት ለመስጠት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብም በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል።

በበላይ ተስፋዬ