የሁለቱ ኮርኔሎች ወግ: ሁለቱም ኮርኔሎች የቅርብ ጓዶቻቸውን አታለው መቀመቅ አስገብተዋል፡፡

የሁለቱ ኮርኔሎች ወግ: ሁለቱም ኮርኔሎች የቅርብ ጓዶቻቸውን አታለው መቀመቅ አስገብተዋል፡፡

1. ሁለቱም ኮርኔሎች ወጣቱ ባመጣው ለውጥ አማካኝነት ነው ወደ መንበረ ሥልጣን ላይ የመጡት፤
2. ሁለቱም ያስተማሯቸውን አዛውንቶች አንድ ወደ ሰማይ ቤት (ኃይለስላሴ) አሊያም ወደ ሰሜን (አቦ ስብሃት) ሸኝተው ነው መንበሩ ላይ የተደላደሉት፤
3. ሁለቱም ያመጧቸው ወጣቶችን ወይ ገድለዋል አሊያም በእስር አሰቃይተዋል፤
4. ሁለቱም “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” ማለትን ያበዛሉ፤ ማዕከላዊነት መለያቸው ነው፡፡ የተቃወማቸውን በፀረ ኢትዮጵያዊነት እና ባንዳነት ይከሳሉ፤
5. ሁለቱም ከወያኔ ጋር ጠበኞች ናቸው፡፡ ወያኔም የቀድሞውን ኮርኔል ወደ ሀራሬ እንድፈረጥጥ ሲታደርግ፣ በሁለተኛው ኮርኔል ስልጣኗን አጥታ መቀሌ ከትማለች፤
6. የቀድሞው ኮርኔል ከሻዕብያ ጋር እሳትና ጭድ ሲሆኑ ከአሁኑ ኮርኔል ጋር በፍቅር እስከ ሳዋ ድረስ ዘልቀዋል፤
7. የቀድሞው ኮርኔል የኢትዮጵያ መፍትሄ ከወደ ምስራቁ (socialism) ነው ሲለን፣ የአሁኑ ኮርኔል ወደ ምዕራቡ (capitalism) ተመልከቱ እያለን ነው፤
8. የቀድሞው ኮርኔል የኢትዮጵያ ችግር በፈጣሪ ማመናችን ነው ሲለን፤ የዛሬው ኮርኔል ብቻ እመኑ እንጂ ሁሉም በእጅ እና በደጅ ይሆናል በማለት ሰበካውን እያስነካው ነው፤
9. ለቀደመው ኮርኔል ባለሀብቶች አቆርቋዦች ሲሆኑ ለአሁኑ investors ናቸው፡፡ የቀደመው “አቆርቋዦች” ከሚላቸው ወስዶ ለደሃው ሲሰጥ፤ የአሁኑ ኮርኔል ደግሞ ከደሃው እየቀማ ባለሀብቶች እንድያለሙ እያደረገ ነው፡፡
10. የቀደመው ኮርኔል ሀገር ተርቦ ሳለ እርሱና መሰሎቹ በውስኪ ይራጩ ነበር (10ኛው አብዮት በዓል)፡፡ የአሁኑ ኮርኔል ሀገር ልትፈራርስ አንድ ሐሙስ ቀርቷት እርሱ ስለመናፈሻ ያወራል፡፡
11. ሁለቱም ኮርኔሎች የቅርብ ጓዶቻቸውን አታለው መቀመቅ አስገብተዋል፡፡ መንጌ አጥናፉ አባተን ሲያጠፋ፤ አብዮት ደግሞ ለማ መገርሳን ከድቷል፡፡


ድርብ ድንቁርና (compound ignorance)

አላዋቂ መሆን የሰው ባህሪ ነው፡፡ የሰው የህይወት ጉዞ ካለማወቅ ወደ ማወቅ የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ ከእንስሳ የለየን የማወቅ አቅማችን ብቻ ሳይሆን፣ አለማወቃችንን ማወቃችን እና ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን ጭምር ነው፡፡ ስለዝህ አላዋቂ መሆን ጥፋት አይደለም፡፡ በሁሉም አርዕስቶች ላይ አዋቂ የመሆን አቅሙም፣ብቃቱም፣ ግዜውም የለንም፡፡ አንችልምም፡፡ ስለዝህ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አላዋቂ ሆነን ማለፋችን የግድ ነው፡፡

ችግሩ ያለው አለማወቃችን ላይ ሳይሆን ሳናውቅ ያወቅን የመሰለን ግዜ ነው፡፡ ይህንን ነው ድርብ ድንቁርና ያልነው፡፡ አለማወቃችንን ጸጋዬ ገ/መድህን እንዳለው አንድም ከፊደል አንድም ከመከራ እንማረዋለን፡፡ አንድም በሳር “ሀ“ ብሎ አንድም ባሳር “ዋ” ብሎ በህይወት፣ በመከራ፣ በስቃይ” እንማረዋለን፡፡ ነገር ግን ድርብ ድንቁርና የድንቁርናው አይነት ለመማር ዝግጁ ስለማያደርግ -መማር አይፋታውም! ይህን አይነት ድንቁርናን አረቦች ዕውቀት ተከላካይ ድንቁርና ይሉታል (ፀረ- ዕውቀት ግርዶሽ እንደማለት)፡፡

የኢትዮጵያ ችግር የልህቃን ችግር ነው ሲባል ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል፡፡ ትንሽ ጠለቅ ብለን ከተመለከትን የኢትዮጵያ ችግር የልህቃን ሳይሆን የነዝህ ልህቃን ተብዬዎች ድርብ ድንቁርና ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሳያውቁ ያወቁ የመሰላቸው፣ አያውቅም ለሚሉት ህዝባቸው መፍትሄ ፈላጊ ሲሆኑ ውጤቱ ባለህበት ሂድ ሲብስ ደግሞ ወደ ኃላ ተመለስ መሆኑ አይቀርም፡፡

ፋብርካ በጣት በሚቆጠርበት አገር ላይ የላብ አደሮችን አብዮት ለማቀጣጠል በተነሳ የመጀመሪያው “የተማረ” ትውልድ የጀመረች ሀገር ከቀጣዮች “ትውልድ ልህቃን” የተለየ ውጤት መጠበቅ አዳጋች ያደርገዋል፡፡

ሐላፊነቱን ያልተረዳ መሪ ሲለው የማታ የቦቴ መኪና ሹፌር፣ሲለው የተጣሉ ሴቶች አስታራቂ፣ ሲለው አስጎብኝ፣ሲለው የእምነት አባት፣ሲለው የስነ ልቦና ባለሙያ፣ ሲለው የታርክ ምሁርና ተንታኝ የሚሆንበት ሀገር ይዘን እንበለጽጋለን ስንል አለማፈራችን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ፈሪድ ዘከሪያ ለትራምፕ የተጠቀመውን ቃል ቢንዋሰው “bullshit artist” ይዘን ከፍታ አይደለም “abys” ለመግባታችን አሁን ያለንበት ገሀዱ የሀገራችን ሁኔታ ማስተዋል ብቻ ይበቃናል፡፡ መቼም መናፈሻ ፓርኮችን መስራት የሀገራችን ችግር ይቀርፈዋል ብላችሁ ሙግት አትገጥሙም ብለን ተስፋ እናደርጋለን
በለበጣ እውቀት የተሸወደ “ድርብ ድንቁርና”መማረክ ከዝህ ውጭ ውጤት ምን ሊሆን ይችላል? ልህቃን ነበሩ የሀገር መፍትሄ መሆን የነበረባቸው፤ ችግሩ በነርሱ የከፋ ሲሆን መፍትሄ ከወዴት ይመጣል፡፡ “እሳት ከበረደው በምን ይሞቃል! የሚለው የሶማሊኛ አባባል ለዝህ ግራ አጋቢ ችግራችን ትክክለኛው ገላጭ ሳይሆን ይቀራል!

RAJO MEDIA