ዐለም ባንክ ለኢትዮጵያ ለመደበው 2 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና ድጋፍ መስተጓጎሉን ተከትሎ፣ መንግሥት ከባንኩ ጋር ለመነጋገር ጥያቄ እንዳቀረበ

ቸኮለ! የዛሬ ሰኞ መስከረም 4/2013 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች
 
1. ዐለም ባንክ ለኢትዮጵያ ለመደበው 2 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና ድጋፍ መስተጓጎሉን ተከትሎ፣ መንግሥት ከባንኩ ጋር ለመነጋገር ጥያቄ እንዳቀረበ ዋዜማ ሰምታለች፡፡ የመንግሥት ጥያቄ በጥቅሉ በኢኮኖሚ ማሻሻያው አተገባበር ላይ እንነጋገር የሚል እንደሆነ ታውቋል፡፡ ባንኩ ለኢትዮጵያ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ቃል የገባው ብድር እና ድጋፍ ለባንኩ ቦርድ ቀርቦ እንዳይጸድቅ መስተጓጎል እንደገጠመው የዋሽንግተኑ የባንኩ ቢሮ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በኢኮኖሚ ማሻሻያው መርሃግብር መሠረት፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወሩ ሂደት ባግባቡ እንዳልተተገበረ ባንኩ ያምናል፡፡ Link- https://cutt.ly/mfOpqba
 
2. መንግሥት ነባሮቹን የመገበያያ ገንዘብ ዐይነቶች እንደለወጠ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ በለውጡ በ10፣ 50 እና 100 ብር መገበያያ ገንዘቦች ላይ የቀለም እና ይዘት ለውጥ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም 200 ብር ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ 5 ብር ግን ወደፊት በሳንቲም እስከሚተካ ድረስ ባለበት ይቆያል፡፡ የገንዘብ ለውጡ ሙስናን እና ከባንክ ውጭ የሚደረግ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር ይረዳል ተብሏል፡፡ ለውጡ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል እንደሆነ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡ ብሮቹ ላይ አዳዲስ የደኅንነት ገጽታዎች ተጨምረዋል፡፡ ነባሮቹን ገንዘቦች በአዲሶቹ ለመተካት ብሄራዊ ባንክ 3 ወር ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ለአዲሶቹ ገንዘቦች ኅትመት 3.6 ቢሊዮን ብር ውጭ ተደርጓል፡፡
 
3. ኖርዌያዊው ተመራማሪ ጀትል ትሮንቮል ትናንት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የኢምግሬሽን ሠራተኞች እና ደኅንነቶች ለሰዓታት ምርመራ እንዳደረጉባቸው በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡ ትሮንቮል ክስተቱ ያጋጠማቸው የትግራይን ክልላዊ ምርጫ ታዝበው ሲመለሱ ነው፡፡ ደኅንነቶች ከሀገር አላባረሩኝም፤ ሆኖም ለደኅንነትህ የኢትዮጵያ ቆይታህን አቋርጠህ ወደ ሀገርህ ብትመለስ ይሻላል ስላሉኝ ወደ ሀገሬ ተመልሻለሁ- ብለዋል ትሮንቮል በመልዕክታቸው፡፡ የምርጫውን ሂደት መከታተል ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ጋር ያላቸው የቆየ ጥናት እና ምርምር ሥራ አካል እንደሆነ የጠቆሙት ተመራማሪው፣ መንግሥት የአካዳሚክ ነጻነትን ያከብራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
 
4. በዕጩዎቹ እና ታዛቢዎቹ ላይ እንግልት እና ማስፈራራት እንዳደረሰ ሳልሳዊ ወያኔ ዛሬ በሰጠው መግለጫ መናገሩን የሀገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡ በምርጫው ዋዜማ የሕወሃት ካድሬዎች ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ መራጮች ሕወሃትን እንዲመርጡ አስገድደዋል- ብሏል ሳልሳዊ፡፡ ሕወሃት መንግሥትነቱን ተጠቅሞ፣ በፓርቲው ደጋፊዎች፣ ዕጩዎች እና በቤተሰባቸው ላይ በማኅበራዊ ሜዲያ ስም ማጥፋት እና ማስፈራሪያ ማድረሱንም አክሎ ገልጧል፡፡
 
5. ኦነግ ሊቀመንበሩን ዳውድ ኢብሳን ከሊቀመንበርነት እንዳገደ በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ዳውድ ግንባሩን ለክፍፍል ዳርገዋል፤ ከሕገወጥ ሸማቂ ቡድን ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል፤ በተደጋጋሚ ከሥራ አስፈጻሚው ተግሳጽ ቢሰጣቸውም አካሄዳቸውን ለማረም ፍቃደኛ አልሆኑም- ብሏል መግለጫው፡፡ እስከ ቀጣዩ የግንባሩ ጉባዔ ድረስ፣ ምክትል ሊቀመንበሩ አራርሳ ብቂላ ሊቀመንበርነቱን ይይዛሉ፡፡
 
6. እስራዔል እስከ ቀጣዩ የፈረንጆች ዐመት 2 ሺህ ቤተ እስራዔላዊያንን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት 51 ሚሊዮን ዶላር እንደመደበች ታይምስ ኦፍ እስራዔል ጋዜጣ በድረገጹ ዘግቧል፡፡ በጀቱ የተያዘው 2 ሺህ ቤተ እስራዔላዊያንን ለማስወጣት ነው፡፡ ጉዞውን በመጠባበቅ ላይ ያሉት ቤተ እስራዔላዊያን በአዲስ አበባ እና ጎንደር ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
 
7. የልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ በቀለ ከመስከረም 2 ጀምሮ ከሃላፊነት እንደለቀቁ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡ ሃላፊው ከባንኩ ሃላፊነታቸው ለምን እንደለቀቁ ለጊዜው አልታወቀም- ብሏል ዘገባው፡፡ ከባድ ቀውስ ውስጥ ያለው ልማት ባንክ ካለፉት ሁለት ዐመታት ወዲህ መዋቅራዊ ለውጥ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]