ውክልና በሕገ-መንግሥቱ አረቃቀቅ ሂደት…’በሕገ-መንግሥቱ አሰራር ሂደት አልተወከልንም’

ውክልና በሕገ-መንግሥቱ አረቃቀቅ ሂደት…’በሕገ-መንግሥቱ አሰራር ሂደት አልተወከልንም’ የሚለው የአማራ ልሂቃን (እና የፕሮፓጋንዳ ሠራተኞቻቸው) ተሳስቶ የማሳሳት ተግባር እንደ ቀጠለ ነው።

የሕገ-መንግሥቱ አሠራር ሂደት ሕዝባዊ ተቀባይነት ጉድለት (legitimacy deficit) እንዳለበት ግልፅ ነው። በሂደቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊነት ባልነበረ መጠንና፣ ከላይ ወደ ታች የወረደ ሕግ መሆኑ እየታወቀ፣ የትኛውም ሕዝብ ከሌላው የተለየ ውክልና እንደሌለውም በግልፅ እየታወቀ፣ በተለይ አማራ ብቻ ሳይወከል እንደ ቀረ አድርገው የሚያወሩ ከንቱዎች፣ አውቀው የደነቆሩ መሆናቸውን እያስመሰከሩ ነው።

ለመሆኑ ሕገ-መንግሥቱ እንዴት ነበር የተፈጠረው? ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?

ብዙ ብዥታዎች መጥራት አለባቸው።

አንደኛ፣ የሽግግር ቻርተሩና ሕገ-መንግሥቱ አንድ ዓይነት ሰነዶች አይደሉም። ሁለቱ፣ የተለያዩ ሰነዶች የመሆናቸውን ያህል፣ በተለያየ የአጸዳደቅ ሥርዓት ውስጥ እንዳለፉ ማስተዋል ያስፈልጋል። በሁለቱ ሰነዶች አፈጣጠር የተሳተፉት ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች አንድና አንድ እንዳልሆኑም ሊሰመርበት ይገባል።

ጥቂት ልዩነቶችን ግልፅ ላድርግ።

ቻርተሩ፣ ከሐምሌ 1983 እስከ ሕዳር 28፣ 1987 ዓም ድረስ በበላይ ሕግነት ያገለገለ ሰነድ ሲሆን፣ ሕገመንግሥቱ፣ ከሕዳር 28, 1987 ዓም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሥራ ላይ ጸንቶ ያለው ሰነድ ነው።

ቻርተሩ፣ ከመስክ በመጡ የነፃነት ታጋይ ድርጅቶች መካከል ስምምነት የተገለጸበት ሰነድ (pact) ነበር። ስምምነቱም፣ በሰኔ 1983ቱ የሽግግር ወቅት ኮንፈረንስ ላይ በተሳተፉ ድርጅቶች (አንዳንድ ወቅቱን ያጠኑ እንደ Sarah Vaughan ያሉ ሰዎች እንደሚነግሩን ከሆነ፣ ከ26 የፖለቲካ ድርጅቶችና ማሕበረሰባዊ ቡድኖች የተውጣጡ 87 የሚሆኑ አባላት) መካከል የሆነ ነበር። በዚህ ኮንፈረንስ ላይ በዋነኝነት የተሳተፉት ድርጅቶች፣ ኢሕአዴግ (ሕወኅት፣ ኢሕዴን፣ ኦሕዴድ የተባሉትን አባል ድርጅቶቹን ሰብስቦ፣ 32 አባላት ይዞ)፣ ኦነግ (10 አባላትን ይዞ)፣ እና ሌሎችም ብዙ… አፋርን፣ ሶማሌን፣ ሀረሪን፣ ኑዌር-አኝዋክን፣ በርታ-ጉሙዝን፣ ወዘተ ጨምሮ፣ ከደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ የነፃነት ታጋይ ድርጅቶች ነበሩ። የሠራተኞች፣ የሴቶች፣ የመምህራንና የዩኒቨርስቲ ‘ተወካዮችም’ እንደ ማህበረሰባዊ ቡድኖች ተሳታፊ ነበሩ። (በኋላ የመአሕድ መስራች የሆኑት ፕሮፌሰር አስራት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ‘ተወክለው’፣ በንቃት ሲሳተፉ እንደነበር የነበረ ሰው ሁሉ ያስታውሳል።)

እነዚሁ የኮንፈረንሱ ተሳታፊ ድርጅቶችና በወቅቱ የተሳተፉት 87 የሽግግሩ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቻርተሩን እንደ ጊዜያዊ የበላይ ሕግ (interim supreme law of the land) እንዳጸደቁት ይታወቃል።

ቻርተሩ፣ የሕገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ይቋቋማል ብሎ በደነገገው መሠረት፣ በ1984 ዓም፣ በአዋጅ ቁጥር 24/1984 አማካኝነት የሕገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን መቋቋሙን ይኸው አዋጅ ያረጋግጣል።

(አንዳንድ ሰዎች፣ ‘ሕገ-መንግሥቱ ኦነግና ሕወኅት ለብቻቸው ያረቀቁት ሰነድ ነው’ ብለው በድርቅና ሲከራከሩ ይሰማል። እውነቱ የሚያሳየው ግን፣ ኦነግ፣ በ1984 ዓም፣ የሕገ-መንግሥት ኮሚሽን ከመቋቋሙ በፊት ከሽግግር መንግሥቱ እራሱን በማግለል ለቅቆ የሄደ መሆኑ ነው።

‘የኦነጉ ሌንጮ ለታ በማርቀቁ ሂደት ተሳትፎአል’ ተብሎ የሚነገረው ወሬም ስህተት ነው። እራሱ ሌንጮም ሊመሰክር እንደሚችለው፣ የተሳተፈው ቻርተሩን በማርቀቅ ሂደት እንጂ (አቶ ሌንጮ እንደሚለው፣ እዚያም ላይ እንኳን ቢሆን መነሻ ሃሳብ የሚሆን ነገር ከመሞነጫጨር ያለፈ አልነበረም!) ሕገመንግሥቱ ሲረቀቅም፣ ውይይት ሲካሄድበትም ሆነ ሲጸድቅ (ከ1984 እስከ 1987 ዓም ባለው ጊዜ) እርሱም ሆነ ድርጅቱ በስደት ላይ ነበሩ።)

በአንፃሩ፣ ሕገ-መንግሥቱ የተረቀቀው፣ በአዋጅ ቁጥር 24/1984 አግባብ በተደራጀው የሕገ-መንግሥት ኮሚሽን ነበር። የኮሚሽኑ ሰብሳቢም አቶ ክፍሌ ወዳጆ ነበሩ። የአባላቱ ድርጅታዊና ሙያዊ ስብጥር በአዋጁ ውስጥ የተዘረዘረ ሲሆን፣ የየጊዜው ክንውኑም በኮሚሽኑና በተወካዮች ምክር ቤት አርካይቭ ላይ ይገኛል።

ረቂቁን ለሕዝብ በማቅረብ፣ ሕዝባዊ ውይይት ለማድረግ፣ በርከት ያሉ የተለያዩ ስብሰባዎች፣ ሲምፖዚየሞችና፣ የሲቪክ ቡድኖች ዘመቻዎች እንደተደረጉም በወቅቱ የተዘጋጁ ሰነዶች ያሳያሉ።

በተለመደው ኢሕአዴጋዊ (እና ኢትዮጵያዊ) አካሄድ፣ ሂደቱ ሁሉ ከላይ ወደታች (top-down)የተደረገ ቢሆንም፣ በተለያዩ አካባቢዎች፣ እስከቀበሌ ድረስ በመሄድ ሕዝብን ‘ለማወያየትም’ (በእነርሱ ቋንቋ፣ ‘ለማስረዳት፣ ለማሳመንና ለማስረጽ’) ጥረት ይደረግ ነበር።

በተጓዳኝም፣ በሽግግሩ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ፣ ለአንድ ወር ያህል በረቂቁ አንቀጾች ላይ አንድ በአንድ ውይይት ይደረግ ነበር። ይሄም በቴሌቭዥን ይተላለፍ ነበር።

በመጨረሻም፣ የእነ ክፍሌ ወዳጆ ረቂቅ፣ በሕገ-መንግሥት ጉባኤው በነኃሴ 1986 ዓም እንደጸደቀ ይታወቃል።

የዚህን የሕገ-መንግሥት ጉባኤ አባላትን ሕዝቡ ‘እንዲመርጥም’፣ በ1986 ዓም ‘ምርጫ’ ተካሄዶ፣ ‘ተወካዮች’ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ‘ተመርጠዋል’። እኒህ ‘ተወካዮችም’ ረቂቁ ለይ ሲወያዩ የተወሰደ 6 ቅጽ ቃለ-ጉባኤ፣ ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት አርካይቭና መፃሕፍት ቤቱ ይገኛል። በወቅቱም፣ የውይይቱ ሂደት በቴሌቭዥን ሲሰራጭ ነበር።

በወቅቱ የተካሄደው የ-ሕገመንግስት ጉባኤ አባላት ምርጫ ነፃም፣ ፍትሓዊም፣ እንዳልነበር ሁሉም ታዛቢዎች በወቅቱ የመሰከሩት ሃቅ ነበር።

የተመረጡትም አባላት፣ የኢሕአዴግና በኋላ ላይ ‘አጋር’ የተባሉት ድርጅቶች አባላት ብቻ ነበሩ። (በወቅቱ በአማራ ክልል የተወዳደሩት ድርጅቶች ብአዴንና መአሕድ ነበሩ፤ የተመረጡትም የብአዴን አባላት ነበሩ። ክልሉንም ያስተዳድሩ የነበሩት ብአዴኖች ነበሩ። በከተሞች ደግሞ፣ ለምሳሌ በአዲስ አበባ፣ የተወዳደሩና ያሸነፉም አማርኛ ተናጋሪ የግል ተወዳዳሪዎች ነበሩ።)

ዴሞክራሲያዊ ባልነበረ ‘ምርጫ’ የተመረጡ በነበሩ መጠን፣ እነዚህ የኢሕአዴግ አባላት፣ ማንንም አይወክሉም ሊባል ይችላል። ከዚህም በመነሳት፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው የሕገ-መንግሥት አጸዳደቅ ሂደት እንዳልነበር መመስከር ይቻላል።

ይሁን እንጂ፣ የአማራ ሕዝብ ብቻ ከሌላው ተለይቶ አልተወከለም ነበር ለማለት አይቻልም። ለዚህ ነው፣ ‘በሂደቱ አማራ ካልተወከለ፣ ታዲያ ማን ተወከለ?’ የሚል ጥያቄ የምናነሳው።

ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ እና ውይይት ሲካሄድ አርቃቂው (ክፍሌ ወዳጆም)፣ የእርሱ ረዳት የሕግ ባለሙያዎቹም (እነ መዓዛ አሸናፊን ጨምሮ)፣ በኮሚሽኑ የኢሕአዴግና የመንግሥት ቡድን መሪና የኮሚሽኑ ዘዋሪውም (ዳዊት ዮሃንስ)፣ አደሽዳሽ-አጨብጫቢ አባላት የነበሩትና የሕገ-መንግሥት ጉባኤውም የሽግግር መንግሥት ምክር ቤቱም ባለ ብዙ ቁጥር አባላት የነበሩት ድርጅትም (ብአዴንም)፣ በውይይቱ ሂደት በትጋት ሲካፈሉ የነበሩት (እነ ሕላዊ ዮሴፍ፣ ተፈራ ዋልዋ፣ እና ታምራት ላይኔም)፣ እና ብዙ ብዙ በጽሕፈት ቤትና ባጠቃላይ በቢሮክራሲው ውስጥ የነበሩና እስከዛሬም ያሉ ሌሎችም ባለሙያዎች በአብዛኛው አማሮች ነበሩ።

ከማንኛውም አባል በላይ ብዙ ጊዜ የተናገሩት ሰው (ሻለቃ አድማሴም) አማራ ነበሩ።

ሰነዱም የተረቀቀው፣ ውይይቱም የተካሄደው፣ በመገናኛ ብዙሃንም የተሰራጨው፣ ቃለ-ጉባኤውም የተመዘገበው፣ በአማርኛ ነው።

ነገረ-ሥራው የተዋቀረበት የእውቀት ሥርዓት (epistemic system) እና የተቃኘበት ትርክት ማዕከለ-አማራ (Amhara-centric) ኢትዮጵያዊነት ነበር።

በወቅቱ የበታች ካድሬ ሆኖ ባላንጦቹን እየጠቆመ ሲያሳስርና ሲያስር የነበረ የብአዴን ካድሬ፣ ልክ ዛሬ ገና ከእንቅልፉ የነቃ ይመስል፣ ተነስቶ፣ “ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ አማራ አልተወከለም ነበር፤ ቢወከልም ብዙ ጊዜ አልተናገረም ነበር፤ ተፅዕኖ ለመፍጠርም እድል አልነበረውም” ብሎ ማለት፣ አውቆ መደንቆር (willful ignorance) እና ሕዝብን ማደናቆር ነው።

ሕገ-መንግሥቱ ተረቅቆ የጸደቀበት ሂደት ዴሞክራሲያዊ (ማለትም፣ ነፃ፥ ፍትሃዊና እውነተኛ ፉክክር ያለበት) ምርጫ ተደርጎ የተመረጠ የሕገ-መንግሥት ጉባኤ ባልነበረበት አውድ ውስጥ ነበር፤ ከዚህም የተነሳ፣ የትኛውም ሕዝብ (የአማራን ሕዝብ ጨምሮ) በመረጣቸው ወኪሎች አልተወከለም ነበር ማለት አንድ ነገር ነው። የለም፣ ሌላው ሁሉ ሲወከል አማራ ብቻ ሳይወከል ቀርቶአል ብሎ ማለት ግን “ተጨፈኑ እናሞኛችሁ” የሚል ቀጣፊነት ነው።

እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ እንዲያውም፣ በነበረው የቋንቋና የባህል የበላይነት ውርስ ምክንያት፣ በዴሞክራሲ አለመኖር ውስጥም እንኳን፣ በፖለቲካም ሆነ በቢሮክራሲው ውስጥ በብዛት በመገኘት የተሻለ ድምፅ፣ ተሰሚነትና፣ ተጠቃሚነት የነበረው የአማራ ልሂቅ ነው።

እና ምን ለማለት ነው? ይሄ “እናሞኛችሁ ተሞኙልን ዓይነት ወሬአችሁንና የመንደር ህፃናት ወግ ትታችሁ፣ የትላልቅ ሰዎች (የ adult) ፖለቲካ ላይ በመሰማራት፣ “እውነተኛ ተቀባይነት ያለው ሕገመንግሥታዊ ሂደት እንዴት እንመሥርት? በአገር ደረጃ፣ የተሻለ ሕዝባዊ ተቀባይነት እንዲኖረው እንዴት እናድርግ? በዘላቂነትስ እንዴት ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካን ለማስተዳደር የሚረዳ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዘርጋ?” በሚሉ ጭብጦች ላይ ብትመክሩ ይበጃችሁ ነበር።

ከሌላው የተለየ ውክልና ይገባኝ ነበረ ማለት ግን የበላይ ስለሆንኩ ያልተገባ መብት (privilege) ይገባኛል የሚል የእብሪት ክርክር ነው። አያስኬድም። እንደ ቡድን፣ የበላይነትን ብቻ በመፈለግ እኩልነትን መፍራት ለዴሞክራሲ የማይመጥን ፋሽስታዊነት ነው። ወይም ከሌሎች ጋር ተግባብቶና ተቻችሎ በእኩልነት ለመኖር አለመፈለግ ነው። ይሄ ደግሞ ካንተ ይልቅ፣ በእኩልነት እጦት ምክንያት ተገፍቶ ለሚሄደው የተመቸ ይሆናል። ግልግል ነውና። ከፋሽስታዊ የበላይነት አቀንቃኞች ጋር አገርን ከመጋራት የከፋ እርግማን የለምና።

ሁላችንም አልተወከልንም፣ የአንዳንዶቻችን አለመወከል ግን ፍጹም ነበር። ዴሞክራሲ በሌለ መጠን የአማራም ሕዝብ በመረጣቸው እውነተኛ ወኪሎቹ አልተወከለም ነበር። በነበረው ዴሞክራሲ-ጎደል ሂደት ግን የአማራ ልሂቃን የበለጠ ተሳትፎና ድርሻ ነበራቸው። በዛ መጠን አማራም ተወክሏል። ታሪክን ማጣመም ትተን፣ ዛሬ ሁሉም በትክክል በሕዝብ ድምፅ በተመረጠ ወኪል የሚወከልበትን ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥታዊ ሂደት ለመፍጠር እንትጋ። አንዳንድ የብአዴን አባላት ዛሬ ዛሬ እንደሚሉት ‘አማራ አልተወከለም’ ማለት፣ ሸፍጥ የሞላበት የመንደር ህፃናት ፖለቲካ ነው። እወክለዋለሁ ለሚሉት ሕዝብም፣ ለአገርም አይመጥንም።

Tsegaye Ararssa


ቅዳሜ …
…ማለዳ !
#በእጅዎ ልትገባ የሚገባባቸው ምክንያቶች አሉ!
* ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪ ፕ/ር መሐመድ ሐሰን ከጉለሌ ፖስት መጽሔት ጋር ባደረጉት #ልዩ ቃለምልልስ ፦
*** የአገራችንን ዘልማዳዊና በእጅጉ በወገንተኝነት ፖለቲካ የተጠለፈ የታሪክ አጻጻፍ ዘዬ በሳይንሳዊ ስልትና በስነ አመክንዮ የሚሞግቱ ሲሆን፤ ማስተባበያ ሊቀርብበት ስለማይችለው የኢትዮጵያውያን የማንነት ዳራ ምሁራዊ ትንታኔያቸውን ይሰጣሉ። እንዲሁም ፦
** ከፌዴራሊዝም ስርዓተ መንግሥቱ ጋር ተያይዞ ስለሚቀርቡት አከራካሪ ጉዳዮች “ይበጃል” የሚሉትንና ሌሎች ሃሳቦችን ያጋሩናል።
*** ዕውቁ የነገረ ሁለንተና ተንታኝ ኢንጂነር ወንድምስሻ አየለ “የሴራ ፖለቲካው ምስጢር” (Game of Blame) በሚል ርዕስ ማንም ሰው ሊያነበው የሚገባ፣ በምርመራ አቀራረብ(Investigative approach)ረቂቅና ውብ የሆነ ወቅቱን የዋጀ ፊቸር ያስነብቡናል !
*** ወረ ኮርሜ ቡኮ(ዶ/ር) “የሽግግር ፍኖተ ካርታ(ROADMAP) ከጠሚር ዶር ዓብይ እንጠብቃለን…” የሚሉበት ጽሑፋቸው የአገራችንን ፖለቲካ በቅርብ መከታተል ለሚፈልጉ ሁሉ ጠቃሚና መረጃ ሰጪ(Informative) ነው።
* የኦሮሞ ጥናት ማሕበር(OSA) ለመጀመርያ ጊዜ በመዲናችን ያደረገው 33ኛው ጉባኤ በምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት አደረገ?
*በጋዜጠኛ አቦማ ታደሰ የተዘጋጀው”በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ድጋፍ ሰጪዎች” ሚና ግምገማ
*የጉለሌ ፖስቱ ጋዜጠኛ ሰሎሞን ዓለማየሁ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተከታታይ የጉዞ ማስታወሻ የመጀመርያ ክፍል
*የአንጋፋው ጋዜጠኛ ዓለምሸት ሞገስ “የተሃድሶዎች ተሃድሶ” የተሰኘ ሞጋች ጽሑፍ እና
*** ሌሎችም…
ከ…
#ጉለሌ ፖስት መጽሔት
ቅዳሜ ማለዳ !
የላቀ ሃሳብ ፤ ሚዛናዊ መረጃ

1 Comment

  1. The “Amhara” always have more laughs for the rest of Ethiopians.

    How come the “Amhara” suddenly wake up and become pro representation? Ironically, there is no problem when they run empire Ethiopia like their fiefdom, dispossessing and excluding others. Now, they have got their eyes on the Ethiopian Constitution, which gives relative rights to ethnic Ethiopians, and are crying to get it abolished. In fact, The “Amhara” cannot deny that they have had Lion’s share in all sectors that have shaped the fate of that country at the expense of other Ethiopians, including under the TPLF/EPRDF régime. The fact that the constitution was drafted in Amharic language and required good aptitude in Amharic itself says a lot, and exposes that the “Amhara” are ingenuine, when they claim being unrepresented. The Amhara Democratic National Movement/current Amhara Democratic Party (ADP) has not only been a major player in EPRDF, but also has been the main culprit in blocking any meaningful representations of the Oromo and other ethnic groups, using its influence to manipulate the TPLF and OPDO. “Amhara” cadres and bureaucrats facilitated the destruction of the Oromo as a nation using their leverage to guide and manipulate TPLF and OPDO daft cadres and officials. The Amhara are over represented in all federal institutions as well as the country’s private business sectors, due to the fact that they have used state machinery to expropriate other ethnic Ethiopians’ resources. This must be corrected and injustices redressed urgently in order to enable other ethnic Ethiopians to have meaningful representations. “Amhara” deceptions mustn’t be allowed anymore.

    The Oromo and other historically subjugated ethnic groups mustn’t be complacent to Abyssinian shrewd moves, and must take political developments in that country serious. They must be able to push for their fair representations, and exert pressure on the Ethiopian government to attend to their interests? The “Amhara” are only better than the Oromo and others in one and only one thing, unashamedly trying to take what is theirs as well as what belongs to other peoples.

    Oromo, Sidama, Somali, Walayita, Affar, Agaw, Hadiya, Gumuz, Kambata, Gurahage, etc., wake up and ask for your justified rights unashamedly. Stand with each other and support just causes of your fellow Ethiopians. A century and half deep sleep is more than enough for the Oromo and other historically repressed Ethiopians. Any justification for the Amhara to be over represented in federal institutions? Peoples, even grass eater fights back when pushed to the limit.

    OA

Comments are closed.