ዉጥረት በወላይታ- DW Amharic

ዉጥረት በወላይታ

በደቡብ ከልል ዎላይታ ሶዶ ከተማ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ የማህበራዊ አግልግሎት መስጫዎች እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸው ተሰማ። ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ዛሬ በከተማው መደበኛ አንቅስቃሴዎች አይስተዋሉም፣ አብዛኞቹ የንግድና የመንግስት አግልግሎት ሰጪ ተቋማትም ተዘግተዋል። የአግልግሎት መስጫዎች እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሊቋረጥ ያቻለው የዎላይታ ዞኑ ራሱን በቻለ የራስ ገዝ አስተዳደር ( ክልል ) ለመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ካለማግኘቱ ጋር በተያያዘ ሁከት „ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ ነው“ ተብሏል። ዶቼ ቨለ (DW) ያነጋገራቸው የዓይን አማኞች << በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች የጸጥታ አባላትን ከጫኑ ወታደራዊ ካሚዮኖች በስተቀር የታክሲ፣ የባጃጅ እና የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች አንቅስቃሴ አይስተዋልም ፣ መንገዶችም ጭር ብለው ይስተዋላሉ >> ብለዋል ። የወላይታ ዞን ምክር ቤት በክልል ለመደራጀት የሚያስችለውን ውሳኔ በማሳለፉ ጥያቄውን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ካቀረበ ዛሬ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ።ም አንድ ዓመቱን አስቆጥሯል ። << ያቀረብኩት ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ምላሽ ተነፍጎታል >> ያለው የዞን ምክር ቤትም ከሁለት ሳምንታት በፊት አስቸኳይ ጉባኤ በመጥራት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለጥያቄው በአስር ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል ። ምክር ቤቱ ዳግም ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ << የላጋ >> የተባለው የለውጥ አራማጅ ስብስብን ጨምሮ የከተማው ሴቶችና አባቶች ተከታታይ ሰልፎችን በማድረግ ጥያቄው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ። ሁኔታው ወደ ሁከት ሊያመራ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ያደረበት የዞኑ ወታደራዊ ዕዝ ( ኮማንድ ፖስት ) ዛሬ በከተማው ምንም አይነት የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄድ የተከለከለ መሆኑን ትናንት ማምሻውን በከተማው በሚገኙ የአካባቢው ራዲዮ ጣቢያዎች ማሳሰቢያ ሰጥቷል። በደቡብ ክልል ዎላይታ ፣ ካፋ እና ሃድያን ጨምሮ የተለያዩ የዞን መስተዳድሮች በክልል እንደራጅ ጥያቄ አቅርበው የክልሉን ምክር ቤት ይሁንታ እየጠበቁ እንደሚገኙ የሀዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ያደረሰን ዘገባ ያመልክታል።

DW Amharic