ወቅታዊውን ሁኔታ በማስመልከት ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ ወቅታዊ የአቋም መግለጫ

ወቅታዊውን ሁኔታ በማስመልከት ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ ወቅታዊ የአቋም መግለጫ

የፌዴራል መንግስትን ስልጣን በህገወጥ መንገድ ተቆጣጥሮ የሚገኘው አሃዳዊ ግለሰባዊ አምባገነናዊ ሃይል “ታሪክ ራሱን ይደግማል” እንዲሉ የኢትዮጵያ ዘውዳዊና ወታደራዊ ስርዓቶችን ግፎች አንድ በአንድ እየደገመ ከውጪ ሃይሎች ሳይቀር በመሻረክ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክና የኢሳያስ ስርዓት ቂም መወጫ ለማድረግ የአገርን ሉዓላዊነት አሳልፎ እስከመስጠት የደረሰ ክህደትና በደል በመፈፀም ላይ ይገኛል፡፡
 
ሰሞኑን ደግሞ የሃገር መከላከያ ሃይሎች ዳግመ አደረጃጀት በሚል ሽፋን የሃገርን ሉዓላዊነት አሳልፎ ለመስጠትና የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ በሴራ የተመላ ስልት ተግባራዊ ለማድረግ አቅዷል፡፡ ባለፉት 23 ዓመታት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የቆየውናና እልባት ያላገኘውን የድንበር ግጭት ለመከላከልና የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ትግራይ ውስጥ የተሰማሩትን የአገር መከላከያ ሃይሎች በማዳከም ህዝብንና ሃገርን አሳልፎ ለመስጠት በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን የትግራይ መንግስትና ሌሎች ፌዴራሊስት ሃይሎች በተደጋጋሚ እንደገለፁት ይህ አሃዳዊ ግለሰባዊ አምባገነን ሃይል በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የስልጣን ዘመኑ ስላበቃ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ውሳኔዎች የማስተላለፍ ምንም ዓይነት ህጋዊ ሃላፊነትም ሆነ ስልጣን የለውም፡፡ ስለሆነም የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የወቅቱን ሁኔታ በሚገባ በመገምገም የሚከተለውን ወቅታዊ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡-
 
1. የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሃይሎች ተወያይተው ከሚያስቀምጧቸው ቀጣይ መፍትሄዎች ውጪ በስልጣን ላይ ያለው ህገወጥ፣ አሃዳዊና ግለሰባዊ አምባገነን ሃይል የአገር መከላከያ ሃይሎችን አደረጃጀትና ስምሪት በተመለከተ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ህጋዊ ሃላፊነትም ሆነ ስልጣን ስለሌለው የተወሰኑት ውሳኔዎች ተቀባይነትም ሆነ ተፈፃሚነት የላቸውም፡፡ በዚህም መሰረት ከትግራይ ጋር የተያያዙ የስምሪትም ሆነ የአመራርና የአደረጃጀትና ለውጦች፣ የሰራዊትም ሆነ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነትና ተፈፃሚነት እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል፡፡ የሃገር መከላከያ ሃይሎች ይህንን ህገወጥና ከህገመንግስታዊ ተልዕኳቸው ውጪ የሚደረግ አደረጃጀትና ስምሪት መቀበል እንደሌለባቸው እናሳስባለን፡፡ በዚህ ሃይል ሃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ምክንያት ለሚፈጠር ችግር ተጠያቂዎቹ በስልጣን ላይ ያሉት አሃዳውያን ግለሰባዊ አምባገነኖቹ አቢይ አህመድና ኢሳያስ ናቸው፡፡
 
2. የትግራይ ህዝብ በህጉ መሰረት የሚገባው በጀትም ሆነ ሌሎች ድጋፎች ከግለሰባዊ አምባገነን ሃይል ኪስ የሚሰጠው ሳይሆን ከራሱ ከትግራይ ህዝብ በግብርና በቀረጥ የተሰበሰበና በበጀት መልክ ተሸንሽኖ የሚሰጠው ህጋዊ ድርሻው መሆኑ ታውቆ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የትግራይ በጀት ሊለቀቅ ይገባል፡፡ ይህ ህገወጥ ሃይል የትግራይን ህዝብ ህገመንግስታዊ መብት በመጣስ በጀት የሚቆርጥም ሆን የሚያቀርጥ ከሆነ በቀጥታ ጦርነት ማወጅ በመሆኑ፤ በውጤቱ ለሚፈጠር ማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ብቸኛው ተጠያቂ በስልጣን ላይ ያለው ህገወጥ፣ አሃዳዊ ግለሰባዊ አምባገነን ሃይል ነው፡፡
 
3. የትግራይ ህዝብ በዚህ ግለሰባዊ አምባገነናዊ ሃይልና ሸሪኮቹ የሚደርሱብህን ቁጥር ስፍር የሌላቸው በደሎች “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” በሚል አስተዋይ አካሄድ አገርን ለማዳን ስትል እላፊ ዋጋና መስዋእትነት እየከፈልክ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ትእግስትህን ሊረዱ የማይችሉ አዳዲስ ግልሰባዊ አምባገነኖች ማባሪያ የሌለው ግፍ፣ አድልዎና ግፊት እየፈፀሙብህ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም በደህንነትህና ህልውናህ ላይ ያንዣበበው ተጨባጭ አደጋ በዚህ ሁኔታ ሊቀጥል እንደማይችልና እንደማይገባ ተገንዝበህ እንደወትሮህ ሁሉ ጠላቶችህን ዳግም ለመመከትና ደማቅ ታሪክ ለመስራት ከፍተኛ ዝግጅት እንድታደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
 
4. ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በስልጣን ላይ ያለው ህገወጥ ሃይል ከማይመለከታቸው አካላት ጋር ሲያካሂደው የነበረው ውይይት በኢትዮጵያ ህዝቦችና ፖለቲከኞች ተፅእኖ ባይቋረጥ ኖሮ የሃገርን ሉዓላዊነት ኣሳልፎ በመስጠት ስምምነት ለመፈራረምና የገንዘብ ዳረጎትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዲሰጠው ተስማምቶ እንደነበረ ገሃድ ሆኗል፡፡ ይህ ሃይል የሃገርን ሉዓላዊነት አሳልፎ ከመሸጥ ወደኋላ የማይል መሆኑ ዳግም ግልፅ ሆኗል፡፡ ስለሆነም በስልጣን ላይ በሚገኘው ህገወጥ፣ አሃዳዊና ግለሰባዊ አምባገነን ሃይል ምክንያት ወደ አጠቃላይ ቀውስና የአገር መበታተን ከመገባቱ በፊት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በፌዴራሊስት ሃይሎች የቀረበውን የሰላምና የሃገር ማዳን ጥሪ መሰረት ያደረገ መፍትሄ እንዲያስቀምጡና ከከፍተኛ ጥፋት የሚድኑበትን መንገድ እንዲመርጡ እንዲሁም የጋራ ክንዳቸውን በዚህ ህገወጥ፣ አሃዳዊና ግለሰባዊ አምባገነን ሃይል ላይ እንዲያሳርፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
 
5. ህገመንግስታዊ ስርዓቱንና የሃገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ ቃል ገብታችሁ የተሰለፋችሁ የሃገር መከላከያ ሃይሎች፤ የሃገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እየወደቀ አይታችሁ እንዳላየ የምታልፉበት ሁኔታ ሊያበቃ ይገባል፡፡ በዚህ ሃይል ጨፍላቂ አካሄድ ከህገመንግስታዊ ተልዕኳችሁ ወጥታችሁ ከኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋራ እንድትጋጩና እንድትዳሙ እየተደረገ ነው፡፡ ሃገርን በመስዋዕትነታችሁ ለማዳን ተሰማርታችሁ ስታበቁ ዓላማችሁ ተጠልፎ የህገወጥ ግለሰባዊ አምባገነንና አሃዳዊ ሃይል ጠባብ ፖለቲካዊ ጥቅም ማስጠበቂያ መሳርያ በመሆን ላይ እንደምትገኙ አውቃችሁ ከህዝባችሁ ጎን እንድትሰለፉና የአገራችሁን ሉዓላዊነት ለማስከበር ታሪካዊ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ ጥሪ እያቀረብን ሃገርና ህዝብን ለማዳን በምታደርጉት ትግል የትግራይ ህዝብና መንግስት ከጎናችሁ ሆኖ እንደሚታገል እናረጋግጥላችኋለን፡፡
 
6. ይህ በስልጣን ላይ የሚገኝ ህገወጥ ሃይል ዓለማቀፋዊ ቃልኪዳኖችንና ግዴታዎችን በመጣስ ከዓለማቀፍ ምግባረ ሰናይ ተቋማት የተገኘ የምግብ ዋስትና እርዳታን ሳይቀር ለፖለቲካዊ ዓላማው ማራመጃ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ስለዚህ የተባበሩት የዓለም መንግስታት ድርጅትና ኤጀንሲዎቹ እንዲሁም ዓለማቀፍ ምግባረ ሰናይ ተቋማት ለምግብ ዋስትናና ለሰብዓዊ እርዳታ የለገሳችሁት እርዳታ ለህገወጥ አሃዳዊና ግለሰባዊ አምባገነን ሃይል ፖለቲካ መሳርያና ለትግራይ ህዝብን መጨቆኛ እየዋለ መሆኑን አውቃችሁ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እንድትቆጣጠሩ፤ ህገወጡ ሃይልም ዓለማቀፍ የሰብዓዊነት መርሆዎችን በመጣሱ ተጠያቂ ልታደርጉ ይገባል፡፡ የዓለም ማህበረሰብ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፍ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ የምትገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ይህች ሃገር ወደ እርስ በርስ ጦርነትና መበታተን ካመራች ቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ መዘዙ እጅግ ከባድ መሆኑን ተረድታችሁ ሃገርን በማዳን እንቅስቃሴው ላይ ህጋዊና ሞራላዊ ግዴታችሁን ልትወጡ ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚች ሃገር ለሚያጋጥመው ቀውስና መበታተን ከታሪካዊና ሞራላዊ ተጠያቂነት ማምለጥ አትችሉም፡፡
 
7. የኤርትራ ህዝብና የመከላከያ ሃይሎች፤ ለነፃነት በከፈላችሁት መራራ መስዋእትነት ውስጥ ውድ ዋጋ የከፈለውን የትግራይ ህዝብ ለማንበርከክ የኢሳያስ ስርዓት ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች ጋር ተሻርኮ ዳግም ወደ ደም መቃባት ሊያስገባን ላይ ታች በማለት ላይ ይገኛል፡፡ ሁለቱም ግለሰባዊ አምባገነኖች የህዝቦችን የወንድማማችነት ግንኙነት መንገድ ዘግተው ስልጣናቸውን ለማደላደልና ለማስጠበቅ የሚያስችላቸው ግለሰባዊ ግንኙነት በመፍጠር በሁለቱ ሃገራት ወንድማማች ህዝቦች ደም ለመንገስ ያላቸው ምኞት ህልም ሆኖ እንዲቀር ታሪክ የምንሰራበት ወሳኝ ምእራፍ ላይ የምንገኝ መሆናችንን ተረድታችሁ ከትግራይ ህዝብ ጎን ተሰልፋችሁ ግዴታችሁን እንድትወጡና የኢሳይስ ስርዓትን ደም አፋሳሽ አካሄድ እንድታስቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ የኢሳያስ ስርዓት በኢትዮጵያ ለሚያጋጥም ማንኛውም ችግር ከተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል፡፡
ዘለዓለማዊ ክብር ለሰማእታት!
 
የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም.
መቐለ
Dimtsi Weyane አማርኛ

ወቅታዊውን ሁኔታ በማስመልከት ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ የአቋም መግለጫ፣
ጥቅምት 14/2013 ዓ/ም

ወቅታዊውን ሁኔታ በማስመልከት ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ የአቋም መግለጫ፣ ጥቅምት 14/2013 ዓ/ም