“ ኮሲ ፆም ሲያድር፣ ሙጃ ያበቅላል” ኢልማ አባ-ረጋሣ” ፀጋዬ አራርሳ

ፀጋዬ አራርሳ “ ኮሲ ፆም ሲያድር፣ ሙጃ ያበቅላል” ኢልማ አባ-ረጋሣ”

ፀጋዬ አራርሳ “ ኮሲ ፆም ሲያድር፣ ሙጃ ያበቅላል” ኢልማ አባ-ረጋሣ"

( satenaw) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ የሚዥጎደጎዱ ትንታኔዎችን፣ አመለካከቶችንም ሆኑ መግለጫዎችን  ደግፌም ሆነ ተቃውሜ ብዕሬን ከወረቀት አገናኝቼ አላውቅም። አልፎ አልፎ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ግን ከሰዎች ጋር ኃሳብ መለዋወጡም ሆነ አንዳንዴ ክርክር ቢጤ ማድረግም እንዳለ ሆኖ። በብሔራዊ አጀንዳ ዙሪያ አደባባይ ሊወጣ የሚችል ቁም ነገር አቀናብሬ ለመጻፍ የእውቀት አቅሙም ሆነ የጽሁፍ ተሰጥዖ እንደሌለኝ ስለማምን ነው።  አንዳንድ ቀልቤን የሳቡና  በእኔ አቅም ልክ ናቸው የምላቸው ጉዳዮች ተፅፈው ሳነባቸውም ሆነ ተነግረው ሳዳምጣቸው ለመሳተፍ ነሸጥ ሊያደርገኝ ይሞክርና አንዳንዴ ኃሳቤ በሌላ ሰው ተገልጾ፤ አንዳንዴ ደግሞ ሳመነታታ ምንም ሳላደርግ የተነሳው ጉዳይ ቢያንስ በውስጤ ያረጅና አርፈዋለሁ።

አገሬንና ወገኔን በክፉ ጊዜ ጥዬ የሸሸሁ በመሆኔ ሁሌም ውስጤ ሰላም ኖሮኝ ወይም ከራሴ ጋር ተስማምቼ እየኖርኩ አይደለሁም። ፍርኃቴንም አሸንፌ የውስጤን መሻት ልኖረው አልደፈርኩም። በአጭርና ግልፅ ቋንቋ ራሴን ለመግለፅ – ፈሪ ነኝ። በቃ!። በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሆኜም ቢሆን በሃገሬ ውርደትና በወገኔ ስቃይ  ቆሽቴ እርር ድብን ማለቱ ግን እውነት ነው።  በሽሽት ላይ ሆኜ ከስደተኛ ታጋዮች ጋር ተቀላቅዬ ”ታጋይ ”ነቱን መንፈሴ ዳድቶት አያውቅም። የስደት ህይወት ከተቀላቀልኩ ጀምሮ እኔም ሆንኩ ሌሎች ስደተኛ ወገኖቼ – ድርሻችን፤ በአገራቸው ሁነው ሁሉንም ግፍና መከራ በመጋፈጥ ቆርጠው የሚታገሉት ወገኖችን በምንችለው ሁሉ ማገዝ ነው ባይ ነኝ።

ዛሬ ያለወትሮዬ ይህቺ ፅሁፍ ፈንቅላኝ ለመውጣት ምክንያት የሆኑኝ ፦

  1. ”ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም።” ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ

”ዶ/ር ” ፀጋዬ አራርሳ በኤስ.ቢ.ኤስ (SBS) ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ ዝግጅቶች ላይ የሚያቀርባቸውን አስተያየቶች አብዛኞቹን ተከታትያለሁ። እርጋታ በተሞላበት ሁኔታ በሥርዓት ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብም አስተውያለሁ። ”ዶ/ር ” ፀጋዬ፤ አዲስ አበባ ተውልዶ ማደጉን፣ ከሰላሌው ተውላጅ አባቱና ከአባይ ማዶ የጎጃም ተወላጅ እናቱ መወለዱን፣ ከጎንደር ተወላጇ የቀድሞ ባለቤቱ ልጅ መውለዱንና የኦሮምኛ ቋንቋውን እንኳን በወጉ ሳያውቅ ”በኦሮሞ ጥያቄ” ዙሪያ የሚያቀርባቸውን አስተያየቶች ከግምት በማስገባት፤ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ እፀፆች የመፍትሔ ኃሳቦች ናቸው ብሎ የምሩን ያመነባቸውን ከወገኖቹ ጋር ለመጋራት የሚፍጨረጨር ቅን ወገን አድርጌ ነበር ስረዳው የኖርኩት። ግን ሁሌም ሸሸክ የሚለኝ ስሜት አለ።

ወያኔን ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ኖረው፤ የአገልግሎታቸው ወሮታ ተቆጥሮላቸው ለትምህርትም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ውጪ አገር ሲላኩ፤ መጀመሪያ ትንፋሻቸውን አጥፍተው የመኖሪያ ፈቃዳቸውን በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ወይም ትንፋሻቸውን በተቃውሞ ማሰማቱ ለጥገኝነት ጥያቄያቸው ጠቀሜታ እንዳለው ሲመከሩ/ሲገነዘቡ፤ ያንኑ ጠብ-እርግፍ ብለው ሲያገለግሉት የኖሩትን የአገዛዝ ሥርዓት ላይ መቶ ሰማኒያ ዲግሪ ዞረው ጥንብ እርኩሱን ሲያወጡ ስሰማና ሳይ በውስጤ ክፉኛ እታዘባቸዋለሁ። የበደሉትን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅና ንሰሃ መግባት ያባት ነው! አቶ አሰፋ ጫቦ ”ድርሻ-ድርሻችንን እናንሳ” እንደሚሉት። መቼም ”ዶ/ር ” ፀጋዬ ደፍሮ የወያኔን ከፍተኛ የፖለቲካ መሪዎች ጨምሮ  ካድሬ ዳኞችን ለማሰልጠን ”ሲቪል ሰርቪስ ኮሎጅ ለመመደብ መመዘኛው እውቀት ወይም ችሎታ ነው” ብሎ ደፍሮ ይከራከል ብዬ መገመት አልደፈርኩምና ነው። እሱ  እንኳን ድፍረቱ ኖሮት ቢሞክር፤ የቀድሞ  አለቃውም ተማሪውም የነበሩትና በአሁኑ ጊዜ በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ትርፉ ኪ/ማሪያም (የአቶ ዓባይ ወልዱ ባለቤት) ዝም የሚሉት አይመስለኝም።

የህወሃት/ወያኔ ተላላኪ ሆነው በመረጡት ሳይሆን በታዘዙበት የጎሳ ሰልፍ ተኮልኩለው  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፍዳና መከራውን ሲያስቆጥሩት የኖሩትን ህዝብ፤ በደላቸውን ሳይናዘዙና ይቅርታ ሳይጠይቁ መልሰው ”ነፃ አውጪዎችህ እኛ ነን” ሲሉ ምንድን ነው የሚባለው? ለአንድ ጤናማ ዓዕምሮ ላለው ሰው እንዲህ መሆን ይቻለዋልን?

”ዶ/ር ” ፀጋዬ!”ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም”? ኸረ አሳምሮ አለ!  ኢትዮጵያዊ ማንነት ነበረ፣ አለ፣ ይኖራልም። አንተ ውስጥ አለ ወይም በግድ ይኑር አላልኩም። አልልምም። ያ ከእኔም አልፎ ተርፎ በሕይወት የሌሉትን ወላጆቼን ያስወቅስብኛል። ባለጌ ልጅ ወላጆቹን እንደሚያሰድብ መቼም ሳትሰማ አትቀርም? ”ባለጌ ያሳደገው” አስብሎ። የእኔን ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም አትበልብኝ ብዬ ነው የምሞግትህ። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አትዮጵያዊያንንም ያስቆጣን ይኸው ይመስለኛል።

ብዙ አስረጂ እየጠቀስኩ ኃሳብህን መሞገት እችላለሁ። ለነገሩ በውስጤ ብዙ አውጥቼ አውርጄ ነው ልሞግትህ የተሳሁት። ለምን? ከአልከኝ የጎሠኝነት ፖለቲካ እንደ መጠጥ ስካር አድሮ ይለቃል ከሚሉት ወገኖች ነበርኩ። እንዲያውም ከስካሩ አልፈው የዞረ ድምር ውስጥ ያሉም ይመስለኝ ነበር። አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ዓዕምሮ ህመም ተለውጦባቸው በሃኪም እንደሚረዱ የማውቃቸውም አሉ። ህሙማኑን ከሚያውቁዋቸው ሰዎችም ሰምቼ አውቃለሁ። አንዳንዶች እንዲያውም ጎሠኝነትም ሆነ ዘረኝነት ራሱ የዓዕይምሮ መቃወስ የሚወልደው ነው ይላሉ። እኔ እንኳን ስለዚህ ምንም እውቀት የለኝም።

አባቴ እንዻጫወተኝ፤ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በትውልድ አካባቢያችን፤ አባቱ (አያቴ) ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ጅባትና ሜጫ አውራጃ ከፋሽስት የጣሊያን ወራሪ የቀኝ ገዥዎች ጋር ሲዋጉ በባንዳዎች መሪነት ከሌሎች ዘመዶቹና ወገኖቹ ጋር ይማረካሉ። እንዴት እንደታሰሩም ሲያወጋኝ፤ እግራቸውን በሚያስገባ ልክ ግንድ ተቦርብሮ ሲያበቃ ከታች ሁለቱም እግራቸው በተቦረቦሩት ሁለት ቀዳዶች ይገባል። ከዚያ ከጉልበታቸው በላይ እንዲያልፍ ይደረግና በግንድ ‘ሰንሰለት’ ይታሰራሉ ማለት ነው። በዚህ ሂደት የጉልበታቸው ሎሚ ፈሶ ብዙ ተሰቃይተው ህይወታቸው ያለፈ የቤተሰቡ አባላትም ጭምር እንደነበሩበት አውግቶኛል።

ይህን ሲያጫውተኝ ዝም ብሎ ተራ ወግ ሊያወጋኝ ፈልጎ እንዳልሆነና ይልቁንም ኢትዮጵያን ከቀኝ ተገዢነት ህዝቧንም ከባርነት ለመታደግ የተከፈለውን ዋጋ ልብ እንድል መሆኑን አስገንዝቦኛል። አያቴም ሆነ አባቴ የቀለም ትምህርት ለማግኘት ዕድል አላገኙም። አማርኛ መናገር አይችሉም። ለእኔም ይህንን ታሪክ ሆነ ሌሎችንም ያወጋኝ አፌን በፈታሁበት የኦሮምኛ ቋንቋ ነው። አያቴም አባቴም ኢትዮጵያዊ ሆኖው ኖሮው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ በሚወዷት አገራቸው እቅፍ ውስጥ ለዘለዓለሙ አርፈል። በኤርትራ በረሃ ውስጥ ሁለት ውድ ወንድሞቼ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከር ሲዋጉ በክብር ተሰውተዋል። ኢትዮጵያዊያንን በጎሣ ለመከፋፈል የመጀሪያዎቹ ሞካሪዎች የፋሽስት ጣሊያን ወራሪዎች ይመስሉኛል። ሙከራውን ለማክሸፍ አባ ዶዮ  ሰርገኛ ጤፍ አቅርበው ይኸን መለያየት ከቻላችሁ ብቻ ነው ኢትዮጵያዊያንን መለያየት የሚቻለው ያሉትን እንደገና ማስታወሱም ሆነ ማጤኑ ተገቢ ይመስለኛል። (ስለ አባ ዶዮ ማንነት ለማወቅ ወደ ጊንጪ ወረድ ብሎ ማንንም ጠይቆ በቂ መረጃ ማግኘት ይቻላል።)      

ወንድሜ ”ዶ/ር ”ፀጋዬ! ኸረ የእነ አብዲሳ አጋ፣ ዘርዓይ ደረስ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ ገረሱ ዱጊ ጃጋማ ኬሎንና ስለሌሎችም ኢትዮጵያን ለመታደግ ስለሰሩት ጀብዱና የጀግንነት ታሪክ ምንም አልሰማህም? ስለ አብቹ፤ አባትህ ምንም አላወጉህም? ”አብቹ ለጋ ለጋ ቶኬራ ሂንመርማሪኒ፤ ለቺቱ ነጋ ነጋ ቆሬን ሲወራኒኒ” ተብሎ ሲዘፈንለት አልሰማህም? እናትህስ ስለ በላይ ዘለቀ ጀግንነትና ኩሩ ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊ ኩራትና ቁጭት በተቀላቀለበት ድብልቅልቅ ስሜት ተውጠው አላጫወቱህም? ይህን ካላወጉህ በድለውሃል ለማለት ያስደፍራል።

ይኸውልህ ወንድሜ እነዚህና እጅግ በጣም ብዙ ተመሳሳይ ከቤተሰቤ ጀምሮ የመላው የሃገሪቱ ልጆች በድፍን የጦቢያ ምድር ላይ የከፈሏቸው መሰዋዕትነቶችና በደማቸው የከተቡትና በእኔም ውስጥ የታተመው ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም መባሉ አስቆጥቶ፣ አብከንክኖ፣ እረፍት ነስቶኝ፣ ውስጤን ሲንጠኝ ከርሞ በራሱ ጊዜ እንደ እሳተገሞራ ፈነዳ። ጩኸት ሆኖ። ”ኢትዮጵያዊ ማንነት ነበረ! አለ! ይኖራልም!” የሚል የማንነት የቁጣ ጩኸት ሆኖ!። አንደበተ ርትዑ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ፤ ሲቃ እየተናነቀውና ትንፋሹ እየተቆራረጠ (ቁና ቁና እየተነፈሰ) ሊነግርህ የሞከረው ይህንኑ ነው። ስሜቱን ለመቆጣጠር በመቻሉ፤ አክብሬዋለሁ። ”አፍ ሲከፈት አንጎል ይታያል” ነው የሚባለው? ”ዶ/ር ” ፀጋዬ! ለአንተ፤ ኢትዮጵያዊነትህ በፓስፖርትህ ላይ ብቻ ይሁንልህ! የአንተንም እምነት የሚጋሩ ካሉ እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ! ታዲያ የእኛንም በእልፈ ዓዕላፍ ተከታታይና ተያያዥ ትውልዶች መሰዋዕትነት በውስጣችን የታተመውን አትዮጵያዊ ማንነት እንደ እምነታችን እንዲሆንልን፤ ሊተውልን ይገባል!

ሻምበል ዓፈወርቅ ዮሐንስ ”የጠላሽ ይጠላ”ን ስንኝ የቋጠሯት በመጨረሻዋ ሠዓታቸው ነበር። ጥላሁን ገሠሠ አዚሞት ለመስማት አልበቁም። አቶ አክሊሉ ኃ/ወልድም፣ ደርግ ሊረሽናቸው ስማቸው ሲጠራ፤ የሚረሽኗቸው ወታደሮች አገር ማስተዳደሩን ስለማይችሉበት እሳቸው ከተገደሉ በኋላ አገሪቱን ስለሚገጥሟት አደጋዎች በቁጭት እየተናገሩ ወሚገደሉበት እንደተወሰዱ ተፅፎ አንብቤያለሁ።

ይኸውልህ ”ዶ/ር ” ፀጋዬ! ‘ኢትዮጵያና – ኢትዮጵያዊ ማንነት’ ለአንተ ባይኖሩም፤ ሌሎች ግን በሕይወት ዘመናቸው ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም ሆነ በግፈኞች እጅ ሕይወታቸውን ሊነጠቁ በመጨረሻዋ ሰዓት በሞት አፋፍ ላይ ሆነውም እንኳን የሚያዜሙላቸውና የሚንሰፈሰፉላቸው ናቸው።

በጎሣ መነፅር ካልሆነ ነገሮችን ማየት ለሚሳናቸውና አንዳንድ መናኛ ክርክር ለማንሳት ለሚሞክሩ ግለሰቦች፦

  • ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሰምተውም አያውቁ ይሆን? እላለሁ። ሞትን እኮ በፀጋና በክብር የተጎነጩት ስለኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ነበር። ስለሰማዕትነት ገድላቸው በኢትዮጵያዊ ባለ ቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ቀዌሳ የተደረሰውን ”ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” ተውኔት መመልከቱ፣
  • የጄኔራል ዋሲሁን እና ካሳዬ ጨመዳንም የአውደ ግንባር ውሎዎችና የመሰዋዕትነት ገድሎች የሚያወሱ መጽሐፍቶችንም ገልበጥ-ገልበጥ ማድረጉ፤ ከሸውራራ እይታ ብቻ ሳይሆን ከትዝብትም ያድናል ባይ ነኝ። እኒህ ለአብነት ያህል የጠቀስኳቸው ከኦሮሞ ቤተሰብ የወጡ ውድ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። እንዲያው እንደ አንዳንዶች ”ገበሮች” አይደሉም።

2.” ኢትዮጵያን እንበታትናታለን (ኢትዮጵያ ሂን ቢቲኔሲና)”

ሎንዶን ላይ በተደረገው ”የኦሮሞ ምሁራን ስብሰባ” ላይ  ”ኢትዮጵያን እንበታትናታለን! – ኢትዮጵያ ሂን ቢቲኔሲና!”)የሚል ዛቻ መሰንዘሩን ታዝቤያለሁ።

ከነገረ ቀደም ይህን ዛቻ ከተመለከትኩ በኋላ ስብሰባው ሙሉ በሙሉ የ’ምሁራን’ እንዳልሆነ ተገንዝቤአለሁ። ለምን ቢሉ፤ ይኸ ዓይነቱ አባባል ከምሁር ቀርቶ ከማንኛውም ተራ ግን ዓዕምሮው ጤነኛ ከሆነ ሰው አፍ አይወጣም ብዬ ስለማምን ነው። መጫር፣ መበታተን የአዕዋፍ ባህርይ ይመስለኛል። የተሰጣ እህል ሲያገኙ በልተው ብቻ አይሄዱም። ኸረ በልተው ሳይጠግቡ ነው ጭረው፣ በትነው ከአፈርና ከ”ደገላ” መቀላቀል የሚጀምሩት!። ጤነኛ የሆነ ሰው ግን የራሱን ቀርቶ የሰውም ስጥ እንኳን ዘገን አድርጎ ያልፍ እንደሆነ እንጂ ሲበታትን አላጋጠመኝም።

በእኔ ግምት የኦሮሞ አክቲቪስቶችም ሆኑ ፖለቲከኞች ”መገንጠል፣ መበታተን” የሚባለውን ወንዝ የተሻገሩት መስሎኝ ነበር። መገንጠል የህዝብን ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዴት ሊያመጣ እንደሚችል ብዬው ብዬው ሊታየኝም/ሊገባኝም ያልቻለ እሳቤ ነው። ያንን መንገድ ኤርትራም ደቡብ ሱዳንም ሄደውበት አይተነዋል። አልሰራም። ሊሰራም የሚችል አይመስለኝም። ዴሞክራትነት፣ አምባገነንነት፣ አደርባይነት፣ ኮሚኒስትነት፣ ሶሻሊስትነትም ሆኑ ሌሎች ፖለቲካዊ እምነቶች (ርዕዮተ -ዓለሞች) የአንዱ ወይም የሌላኛው ማህበረሰባዊ ስብስብ (ጎሳ፣ ብሔር፣ ብሔረስብ፣ ወዘተ) የወል (የጋራ) አመለካከት/እሴት ሊሆኑ አይችሉም። ስለሆነም ሰዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ለመሰባሰብ በሚጋሩት የፖለቲካ ፍልስፍና መሆን አለበት ብለው ከሚያምኑት ወገኖች ነኝ። ርዕዮተ ዓለም ለእያንዳንዱ ግለሰብ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ነው። የማህበረሰብ ስብስብ አባልነት ግን በምርጫ ሆኖ አያውቅም። በኔ እምነት የኦሮሞንም የአማራንም ሆነ የሌሎችን ዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ለማክበርም ሆነ ለማስከበር የሚያስፈልገው ለሰው ልጆች ሁሉ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ራስን ማስገዛትና የአገዛዝ ሥርዓትን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መቀየር ይመስለኛል። ቢያንስ ቢያንስ ግን የኦሮሞም ሆነ የሌሎች ጎሳዎች መብት ኢትዮጵያን ማፍረስን አይጨምርም። ለኦሮሞም ህዝብ ሆነ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀው የህወሃት/ኢህአዴግን የአገዛዝ ሥርዓት አስወግዶ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ዕውን ማድረግ ከቻልን ብቻ ይመስለኛል።

”ኢትዮጵያጵያዊያን ለየብቻቸው በብሔር፣ ብሔረ-ሰብ፣ ወዘተ  ማንነታቸው ተደራጅተውና ታግለው ሲያበቁ በጋራ ሆነው ፍትህ፣ ዴሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን እንገነባለን።” የሚለው ፈሊጥ ህወሃት ሄዶበት ለሌላው ቀርቶ እወክለዋለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብም እንዳልሰራ እንዴት ነው ማስተዋል ያቃተን? በተግባር እንዳየነው የጎሣ ፖለቲካ ጠቦ ጠቦ ከመንደር ይወርድና መጨረሻው ቤተ-ሰብ ይሆናል። በህወሃት ያስተዋልነው ይኸንኑ ነው። ትግራይ ተብሎ ተጅምሮ፤ ወደ አድዋ ወርዶ መጨረሻው በእነ መለስ እና አቦይ ስብሃት ቤተሰብ ቁጥጥር ሥር ውሎ የምናየው። የቀድሞው ኦነግም፤ የኦሮሞ . . . ብሎ የተጀመረው ”ትግል ” ወርዶ ወርዶ ከአንድ መንደርና የፀሎት ቤት በወጡ ግለሰቦች ለመሾፈር በቅቶ እንደነበረ ሌላው ማስረጃ ይመስለኛል። የአዲሶቹ ”የኦሮሞ አክቲቪስቶችና መሪዎች”  ስብስብም በአርሲ ልጆች ፊታውራሪነትና ሐረርጌዎች ደጀንነት ነው የሚሾፈረው ይባላል። የኦህዲዶቹም ”ጄኔራል ሁን ስለተባለ ጄኔራል የሆነው” ከማል ገልቹም ሆነ ጁነዲን ሰዶንና የመሳሰሉት ወደ እዚህ ስብስብ የመቀላቀላቸው ዋና መለኪያውም ይኸው የጎሣ ፖለቲካ መገለጫው ‘መንደርተኝነት’ ነው እየተባለ ነው። ለጊዜው አርሲነት!

ይበልጥ አስገራሚው ጉዳይ ይህን የማይሰራና መክሸፉ በገሃድ ያየነውን የከሰረ የጎሣ ፖለቲካ እናራምዳለን የሚሉ  እንደ አዲስ መፍላት መጀመራቸው ነው። የአዲሶቹ የጎጥ ቡድኖች ጥድፊያ የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን አረመኔ ጎጠኛ አገዛዝ በቃኝ ብሎ ለመገላገል የተያያዘው ትግል ጫፍ በመድረሱ ይመስላል፤ ጥድፊያው አይሏል።

ከጥቂት ወራት በፊት አገር ቤት ዘልቀው ሲጨፍሩና ሲዶልቱ የከረሙ ሳይቀሩ “ከእኔ በላይ ታጋይ“ እያሉን ነው። መመስረታቸውን ሳንሰማ ጥምረታቸውን እያሳወቁን ነው። በስደት ‘አየር ላይ ተወለድን’ የሚሉን  ”የደመና ላይ የጎበዝ አለቆች” የእውነቱን ፍልሚያ በአገር ቤት እያካሄዱ ካሉት በላይ ሽለላና ቀረርቶውን ሲያስነኩት ማየቱና መስማቱ ማሳፈርና ማሳዘን ብቻ ሳይሆን ጥርጣሬም የሚያጭር ነው።

አዲሶቹ ”የአማራው ህልውና ታዳጊዎች” ፉከራቸውን ያሰሙት ከአብደራፊ፣ ከካዛ-እየሱስ፣ ከዳንሻ፣ ከመተማ፣ ከመተከልና ከመሳሰሉት መሆኑ ቢቀር፤ ከሱዳንና ከኬንያ ቢሆን እንኳን ያባት ነው።   ከአሜሪካ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከአውሮፓ፣ . . .ወዘተ ተኩስ ከፍተው ወያኔን ድል በመንሳት የአማራን ህልውና ሊታደጉ!? ከዚያም ”ጉሮ ወሸባዬ” ሊባል?! እነዚህ ዓይናቸውን በጨው ያጠቡ ይሉኝታ ቢስ የሥልጣን ጥመኞችና የወያኔ ትክሎች ህዝብ ሃይ ሊላቸው ይገባል ባይ ነኝ። ሰከን በሉ ሊባሉ ይገባቸዋል። ይህን ደርሶ የትግሉ ፊታውራሪነት ለባለቤቱ ለአገር ቤቱ ህዝብ ተትቶ፤ በደጀንነቱ ተግባራት መረባረቡ ተገቢ ይመስለኛል።

የዓዕምሮ መታወክ ያለባቸውንም በድፍረት የሃኪምም ሆነ የፀበል ክትትላቸውን በትግሥት እንዲቀጥሉ ወገናዊ ምክር መስጠቱ ከማንኛውም ማህበራዊ ኃላፊነት ከሚሰማው ጤነኛ ሰው የሚጠቅ የሞራል ግዴታ ይመስለኛል።

ከ”ዓለም የሠርቶ አደሮች ትሆናለች! ዓለም-አቀፋዊ ” ፊታውራሪነት ወደ ሌብራል ዴሞክራሲ ደቀ-መዝሙርነት ተረማምደው፣ በነፃው ፕሬስ በኩል በማቆራረጥ ወደ ስደት ከወጡ በኋላ ”የአማራ ህዝብ ህልውና ታዳጊዎች ነን” ለማለት የደፈሩትና ሙሉ ግዜአቸውን፤ የሃገሪቱን ውድቀት፣ የህዝቧን መከራና ስቃይ በመደስኮር ለራሳቸው የምቾት ህይወት ጥሩ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ያደረጉትም ከእነዚህ ጋር የሚመደቡ ሌሎቹ ማፈሪያዎች ናቸውና ራስን ከስሜታዊነት አላቆ ቆሞ ብሎ ማየቱ ቢያንስ ቢያንስ ራስን ከጸጸት ለመታደግ ይበጃል ባይ ነኝ።

እኔ እንደተራዳሁት ለዚህ ሁሉ የተዳረግነው የአብዛኛዎቻችን እጆቻችንን አጣጥፎ መቀመጥና የኢትዮያዊነት አጀንዳ ባለቤት አልባ እንዲሆን መፍቀድ ይመስለኛል። ”ኮሲ ፆም ሲያድር፣ ሙጃ ያበቅላል (ማሳ ፆም ሲያድር፣ አረም ያበቅላል)”  እንዲሉ።