የአዲስ አበባ አስተዳደር ለኳታር ኩባንያ 60 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ፈቀደ

የአዲስ አበባ አስተዳደር ለኳታር ኩባንያ 60 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ፈቀደ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኳታር ግዙፍ ኩባንያ ኢዝዳን ሆልዲንግ ግሩፕ፣ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፕሮጀክቶች መስተንግዶ መመርያ መሠረት 60 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጥ ፈቀደ፡፡

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ተግባራዊ ከሆነበት 2004 ዓ.ም. ወዲህ መሬት በድርድር ማቅረብ የቆመ ቢሆንም፣ በከንቲባው ከታመነበት ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች ይፈቅዳል፡፡ እስካሁን ኢትዮ አሜሪካን ዶክተርስ ግሩፕና  የኳታሩ ኤዝዳን ግሩፕን ጨምሮ ከአምስት የማይበልጡ ኩባንያዎች ብቻ ተስተናግደዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አፍሪካ ኅብረት አቅራቢያ ከይዞታ ነፃ አድርጎ ይህንን 60 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ለማስረከብ በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ለዓለም ተሰራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኳታሩ ኩባንያ ፕሮጀክቶች ለአገሪቱ ትልቅ ጠቀሜታ ስላላቸው ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች በሚሰጠው መስተንግዶ መሠረት ሊስተናገዱ ችለዋል፡፡

አገራዊ ፋይዳ መመርያ ቁጥር 15/2005 ላይ በግልጽ እንዳሠፈረው ‹‹ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች›› ማለት ለኢትዮጵያ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ የልማት ፕሮጀክቶች፣ ወይም የትብብር መስኮችን ለማስፋት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አገሮቹ ከሌሎች አገሮች ጋር ለማሠራት የተሻለ ግንኙነት መሠረት እንዲጥሉ በመንግሥት የታቀዱና የተወሰኑ ፕሮጀክቶች ይስተናገዳሉ ይላል፡፡

ኩባንያው ኤዝዳን ሆልዲንግ ግሩፕ በአፍሪካ ኅብረት አካባቢ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል፣ ሪል ስቴትና ዘመናዊ የገበያ ማዕከል በ350 ሚሊዮን ዶላር ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ታውቋል፡፡

የኤዝዳን ሆልዲንግ ግሩፕ ሊቀመንበር ሼክ ዶ/ር ካሊድ ቢን ታሃኒ ቢን አብደላህ አል ታሃኒ በአዲስ አበባ በጥልቀት በሚገቡባቸው ፕሮጀክቶች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከከንቲባ ድሪባ ኩማና ከኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ምሥጋኑ አረጋ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ምክክር ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

መንግሥት የኳታር ባለሀብቱን ፕሮጀክት በሙሉ የተቀበለ በመሆኑ፣ በመሀል ከተማ በመልሶ ማልማት ቦታ ላይ ነዋሪዎች በፍጥነት ተነስተው ቦታው ለኩባንያው እንዲሰጥ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል አልይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ሙሉ ትኩረት ሰጥተው ቦታውን ከሰው ንክኪ ነፃ ለማድረግ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ወስደዋል፡፡

‹‹በቦታ አቅርቦት የተከናወነው ሥራ ከዚህ በኋላም ቦታ ለማዘጋጀት በሚካሄዱ ተግባራት ልምድ የተወሰደበት ነው፤›› ሲሉ አቶ ጀማል አመልክተዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ካላት 54 ሺሕ ሔክታር መሬት 30 ሺሕ ሔክታር የሚሆነው በመሀል ከተማ ይገኛል፡፡ ይኼ ቦታ የመልሶ ማልማት የሚካሄድበት ሲሆን፣ ነዋሪዎችን አንስቶ ወደ ግንባታ መግባት አስቸጋሪና የተወሳሰበ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በልማት ምክንያት የሚነሱ ነዋሪዎች በርካታ ቅሬታ የሚያነሱ ሲሆን፣ በተወሰነ ወቅት ሁሉንም ማንሳት ባለመቻሉም በርካታ ቦታዎች ታጥረው ተቀምጠዋል፡፡ በርካታ ባለሀብቶችም መሬቱን ከወሰዱ በኋላ በገቡት ውል መሠረት ግንባታ መጀመር አልቻሉም፡፡

አንድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ የኳታር ፕሮጀክት የቦታ አሰጣጥ ፈጣንና በቅንጅት የተሠራ ከመሆኑ በላይ ኢንቨስተሩ በፍጥነት ወደ ግንባታ ይገባሉ ተብሎ ታምኗል፡፡

የኳታሩ ኩባንያ በመካከላቸው ምሥራቅ ከሚገኙ ግዙፍ 500 የሪል ስቴት ኩባንያዎች 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡