ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ!

ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

የትግራይ ህዝብና መንግስት፣ በኣሃዳዊና ኣምባገነናዊ ቡድን፣ ተከታታይ ፀረ-ህዝብ እርምጃ አይምበረከኩም!!
በህገወጥ መንገድ በኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጫንቃ በማን ኣለብኝነት፣ ንጹሃንን በጅምላ እየጨፈጨፈ፣ ዜጎች ለሞት፣ እንግልት፣ ስደትና ሰቆቃ እየዳረገ ያለው ኣሃዳዊና ኣምባገነናዊ ቡድን፣ የትግራይ ህዝብን ለማንበርከክ የተለያዩ ተከታታይ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ነው፡፡
ይህ ኣሃዳዊና ኣምባገነናዊ ቡድን፣ ቀደም ሲል የትግራይ ህዝብ ድርሻ የሆነውን የድጎማ በጀት መከልከሉ ባስታወቀበት ማግስት፣ ከበረሃ አንበጣ መንጋ ጋር እየተናነቀ ያለውን የትግራይ ህዝብ ዓመት ሙሉ የለፋበት ቡቃያ የአንበጣ ሲሳይ እንዲሆን በይኖበታል፡፡ ይኸው ጸረ-ህዝብ ቡድን፣ ጸረ-አንበጣ መድሓኒት በአውሮፕላን እንደረጨ የሃሰት መረጃ በማስተላፍና ቀደም ሲል ከዓለም ኣቀፍ ማህበረሰብና ለጋሽ አገሮች ለገበሬዎች ሲሰጥ የቆየውን የሴፍቲኔት ፕሮግራም ማለት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለቀጣይ ሶስት ወራት መላክ የነበረበት 285 ሚልዮን ብር እንደከለከለ ጥቅምት 10/2013 ዓ/ም ያለ ምንም ይሉኝታ በይፋ ኣሳውቀዋል፡፡
 
ከዚህ በተጨማሪ የመቐለ ከተማ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት፣ ገረብ ግባ ግድብ ፕሮጀክት ኩንትራት ወስዶ እየሰራ ያለውን የቻይና ኩባንያ (CHAINA GEZHOUBA GROUP COMPANY LIMITED) (CGGC) የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሁለት ዲዛይነሮች ከቻይና ተነስተው በትራንዚት ወደ መቐለ ከተማ እንዳይመጡ፣ እንደተለመደው ጥቅምት 12/2013 ዓ/ም ቦሌ ዓለምኣቀፍ ኣውሮፕላን ጣቢያ ኣግቶ ኣስቀርታቸዋል፡፡ይህም በኣጠቃላይ የመቐለ ከተማ ነዋሪ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዳይሆን፣ ጎሮሮ በውሃ ጥም እንዲደርቅ የተፈረደ የመጨረሻ የጭካኔ መገለጫ ነው፡፡
 
ይህ ሁሉም ተከታታይና ተደራራቢ ጸረ-ህዝብ እርምጃ የትግራይ ህዝብ፣ ከኢትዮጵያ የፌደራል አወቃቀር ተገፍትሮ፣ እንዲወጣ የሚገፋፋ ተግባር አበክሮ እየሰራ ነው፡፡
በመጨረሻ በትግራይ ህዝብ ላይ ይህንን ሁሉ ተከታታይ ግፍ መፈጸም፣ አሃዳዊና አምባገነኑ ቡድን እድሜ ያሳጥር እንደሆነ እንጂ፣ በሚወስደው ተከታታይ ጸረ-ህዝብ እርምጃ የትግራይ ህዝብና መንግስት ይንበረከካሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ ስለዚህ የዓለም ኣቀፍ ማህበረሰብ ይህ ህገ-ወጥ ኣሃዳዊ ቡድን፣ ከኣንበጣ ጋር ኣብሮ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን፣ ብሄር ተኮር ጥቃት፣ ተገንዝቦ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወስድ፣ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በዚህ ኣጋጣሚ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
የትግራይ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
ጥቅምት 12/2013 ዓ/ም
መቐለ


አሁን የደረሰን ዜና!
በትግራይ ክለቦች ላይ የተጣለው እገዳ ተነሳ
የትግራይ የእግር ኳስ ክለቦችና ሌሎች የስፖርት ተቋማት ጭምር በኢትዮጵያ ማናቸውም የሊግ ውድድር ላይ እንዳይሳተፉ መንግስት ማገዱን መዘገባችን ይታወሳል ።
የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ዛሬ ጧት በትግራይ ክለቦች ላይ የተጣለው የእገዳ ውሳኔ ትክክል ባለመሆኑ ውሳኔውን ኮሚሽኑ ውድቅ በማድረግ እንዲነሳ አደርጋለሁ ብሏል ።
ስፖርት ኮሚሽንም የእገዳውን ደብዳቤ በተመለከተ ዛሬ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል ። በተጨማሪም የሚሽርበት ሌላ ደብዳቤ እንደሚፅፍም አሳውቋል። Via Awlo Media
………..
ሕገ-ወጡ ቡድን በስፖርት ውስጥ ገብቶ ሲንቦራጨቅ አገሪቱን ከአህጉራዊና አለምአቀፍ ውድድሮች እንደሚያሳግዳት አላወቀም ነበር። መንግስት ነኝ ለማለት ያህል ከትግራይ ጋር እልህ መጋባቱ እንጂ በኋላ የሚመጣበት መዘዝ የማመዛዘን ጭንቅላት የለውም። ከደካማው አብይ እስከ ተራ የቡድኑ ካድሬ በስሜት ከመነዳት ውጭ በእውቀት የመወሰን ችሎታ የላቸውም። አሁን የትግራይ መንግስት አገሪቱን ከማንኛውም ውድድር የሚያሳግድ ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱን ሲሰሙ ውሳኔያቸውን ለመቀልበስ እየተሯሯጡ ነው። ይብላኝ ይህንን የሆዳሞች ስብስብ ለሚደግፉ ሰዎች። የትግራይ ህዝብማ ራሱን ብልጥግና ብሎ የሚጠራውን ህገ-ወጥ ቡድን በጠላትነት ከፈረጀው ሁለት አመታት አልፈዋል። ከጠላት በጎ ነገር መጠበቅም ሞኝነት ነው። ትግራይ አገር ነች