ከመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው የተሰጠ መግለጫ ቃል ኪዳናችንን አድሰን ኃላፊነታችንን እንወጣለን!

ከመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው የተሰጠ መግለጫ: ቃል ኪዳናችንን አድሰን ኃላፊነታችንን እንወጣለን!

#EthioMuslims #EthioMuslimCommittee

ከመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው የተሰጠ መግለጫ: ቃል ኪዳናችንን አድሰን ኃላፊነታችንን እንወጣለን!

«ኃጢአትን ወይም አበሳን የሚሠራም ሰው፣ ከዚያም በእርሱ ንጹሕን ሰው የሚሰድብ ቅጥፈትንና ግልጽ አበሳን በቁርጥ ተሸከመ!»
(ቅዱስ ቁርኣን | ሱራ አል ኒሳእ – 4፡108)

ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ

©ድምፃችን ይሰማ

ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ኢ-ፍትሃዊ በሆነ አድሏዊ ተጠቃሚነት እና በደል ላይ በመጓዝ ለኋላ ቀርነት እና ለእርስ በእርስ ግጭቶች የተዳረገች አገር ናት። ሙስሊሙ ማህበረሰብ ደግሞ ለረጅም ዘመናት፣ በተለይም በቅርቡ ባደረጋቸው መብት የማስከበር እንቅስቃሴዎች በደልን እና ኢ-ፍትሃዊነትን የማይሸከም ማህበረሰብ መፍጠር ተችሏል። በሂደትም የተለያዩ የስነ ልቦና ጦርነቶችን በማካሄድ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የአገሩ ባለቤት በሆነው ሙስሊም ማህበረሰብ ዜግነት ላይ ጥያቄ ለመፍጠር የተሞከረውን ከንቱ ሙከራ በማክሸፍ አገር ወዳድነቱንና የአገር ባለቤትነቱን ማስመስከር ችሏል። ለማንኛውም አገር ወዳድ እና ቅን ማህበረሰብ ግልፅ እንደሆነው የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅም ሆነ እድገቷን እውን ለማድረግ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የሐሳብም ሆነ የስነ ምግባር ልዕልና እንዳለው ባለፉት እንቅስቃሴዎች በተግባር አሳይቷል።

ባለፉት ዓመታት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የተቃጣውን ሴራ ለማክሸፍ ከመላው ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ጋር በመሆን እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ በአገሪቷ ለተለኮሰው የለውጥ ጅማሮ የፈር ቀዳጅነት ሚና ተጫውቷል። ሙስሊሙ ማህበረሰብ እምነቱን በነጻነት ለመተግበር የሚያስችለውን ከባቢ ለመፍጠርም ታግሏል። ይህንንም ተከትሎ ሙስሊሙ መብት ከመጠየቅ መብቱን ወደማስከበር እና በአገር ግንባታ ላይ ቁጥሩን የሚመጥን አሻራ መጣል ወደሚችልበት በመሸጋገር ላይ ይገኛል።

ቀጣዩ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው አቅጣጫ ሙስሊሙን ዳግም መብት ወደመጠየቅ እርከን ለማውረድ የሚሸረበውን ሴራ በማክሸፍ የነገ እጣ ፈንታውን በራሱ የሚወስን፣ መብቱን አስከብሮ በአገር ግንባታው ላይ ቁጥሩን የሚመጥን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችል ማብቃት ነው። በመሆኑም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው የጸረ ሰላም ኃይሎችን ሴራ ምንጮች ለይቶ በማውጣት የማድረቅ ስራ ያከናውናል። በፈር ቀዳጅነት በርካታ ለውጦችን ያስመዘገበው ህዝበ ሙስሊም ለመላው ኢትዮጵያዊያን እና ለአገሪቷ ነፃነትና ብልፅግና የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን ፍሬ የሚያፈራበት መስመር ውስጥ መግባት እና እስከ ፍፃሜው በፅናት እንዲቀጥል መደረግ ይኖርበታል።

ሙስሊሙን በጥቃቅን አጀንዳዎች መጥመድ፣ ትርጉም ባላቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንዳይሰራ ማባከን፣ አመራር ማሳጣት እና በመዝሃብና በብሄር በመከፋፈል እርስ በእርስ ማናቆር ሙስሊሙ ለዘመናት ያደረገውን ጥረት ፍሬ እንዳያፈራ በተግባር እየተከናወነ ያለ ሴራ ነው። ይህንንም ተገንዝበን በላቀ ስነ ምግባርና በሰለጠነ መንገድ የሙስሊሙን የነፃነትና የፍትህ ጉዞ ከዳር ማድረስ ተገቢ ነው። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ የሚከተሉትን ስራዎች በአላህ ፍቃድ ተከታታይነት ባለው መንገድ የምንሰራ ይሆናል፦

1) ህዝበ ሙስሊሙን በመዝሃብና በብሄር ለመከፋፈል የሚሞክሩትን አካላት በማጋለጥ የሙለሊሙን አንድነት ከምንጊዜውም በላይ ማስጠበቅ፤

2) ህዝበ ሙስሊሙ እስከዛሬ ያስመዘገባቸው ስኬቶች ሳይቀለበሱ ፍሬያቸውን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ፣ እንዲሁም አዳዲስ ስኬቶችን ለማስመዝገብ እንዲበቃ ተከታታይነትና ዘላቂነት ያለው ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር፤

3) ውጤቶቻችንን ማስጠበቅ የምንችለው ከላይ እስከ ታች ተደራጅቶ እና መብቱን አስከብሮ አገሩን በጋራ በመገንባት ሂደት ውስጥ የሚመጥነውን ሚና መጫወት የሚችል ጠንካራ ማህበረሰብ በመፍጠር በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙን በማደራጀት ከመስጊዶቻችን እስከ ተቋሞቻችን የሚዘልቅ የጋራ ህብረት መፍጠር፤

4) መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ የሙስሊሙን ሁለንተናዊ ጉዳይ በመያዝ ህዝባዊ መሰረት ያለው ጠንካራ አመራር ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ፤

5) ህዝበ ሙስሊሙ ላለበት አገራዊ ኃላፊነት ከጥቃቅን አጀንዳዎች በመውጣት ዘላቂና ጠቃሚነት ባላቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በየትኛውም ኃይል ሊቀለበስ የማይችል ሚናና የአገር ባለቤትነትን የማስጠበቅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፤

6) በሁሉም ዘርፎች የፓሊሲ፣ የስትራቴጂና የትግበራ አቅጣጫዎች ላይ የሚታይ ተፅዕኖ በማሳደር ሙስሊሙን ለይተው የሚያጠቁ ህግና ተግባራትን በማስቆም ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ፤

7) ህዝበ ሙስሊሙ ላለበት ተጨባጭ እና ለደረሰበት ግፍና በደል እንደመሳሪያ ሆኖ የሚያገለግለውን የሐሰት ትርክት፣ የተዛባ ምልከታና በጥላቻ የተሞላ አመለካከት በማፍረስ የጋራ አገራችንን በጋራ ለመገንባት በሚያስችል ትርክትና አመለካከት መተካት፤

8) ታማኝነቱን ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ያደረገ፣ ብቁና በሳል በሆኑ አመራሮች የሚመራ፣ በኢስላማዊ እውቀትና ስነ ምግባር የተገነባ፣ የሙስሊሙን ታሪካዊ ማንነትና ተጨባጭ ባገናዘበ ተክለ ቁመና ላይ የተሰደረ እና ከየትኛውም የመዝሃብና የአመለካከት ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ መላውን ሙስሊም በጋራ የሚወክል ጠንካራ ተቋም እንዲኖር ማድረግ፤

9) ከግማሽ በላይ የሆነው የአገሪቷ ሙስሊም ማህበረሰብ የሃይማኖት ተግባሩን የሚፈፅምበት በቂ መስጊዶችና ተቋማት ይኖሩት ዘንድ ለዓመታት ሲማፀን ቢኖርም በኢ-ፍትሃዊ አሰራርና በቢሮክራሲ ምክንያት ተገቢውን ምላሽ ያላገኘ በመሆኑ በቀጣይ የሙስሊሙን ቁጥር በሚመጥን እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን በሚያረጋግጥ መልኩ የተቋምና የቦታ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ መስራት፤

10) የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥቅሞች አስጠብቆ ለመቆየትና ቀጣይ ፈተናዎችን በስኬት ለማለፍ በማያቋርጥ ትግል ውስጥ መግባት አስፈላጊ በመሆኑ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ቀጣዩን እንቅስቃሴ መላውን ሙስሊም ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ ጊዜውንና ሙሉ አቅሙን ሰጥቶ ለመንቀሳቀስ ወስኗል። በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ ያሉትን አማራጮች ሁሉ በመጠቀም ራሱን ዝግጁ አድርጎ በመጠበቅ ከኮሚቴው የሚሰጡትን አቅጣጫዎች ተከትሎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን፤

11) የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭ የኢማን መድከም፣ የስነ ምግባር መበላሸት፣ እንዲሁም የአመለካከት ክፍተት በመሆኑ በተቅዋና ኢኽላስ የተሞላ፣ በስነ ምግባር የታነፀና ትክክለኛ ኢስላማዊ ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ ለማፍራት መስራት፤

12) ትናንት በአማራ ክልል፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን፣ በሞጣ ከተማ በአራት መስጊዶች እና በሙስሊሙ ንብረት ላይ የደረሰው እጅግ አሳፋሪ ቃጠሎና የማፍረስ አደጋ በተከታታይ ሲሰራ የነበረው የሙስሊም ጠልነት ፕሮፓጋንዳ ውጤት መሆኑ የሚታወቅ ነው። ይህን መሰል ተግባራት ሙስሊሙን ማህበረሰብ ከጀመረው ጉዞ በምንም መልኩ እንደማያደናቅፉት እያረጋገጥን የተከሰተውን ጥቃት በተመለከተ የሚከተሉትን ማሳሰቢያዎች እናስተላልፋለን፦

★ የክልሉ አስተዳደር ኃላፊነት ወስዶ ተጠያቂነት እና ግልፅነት ባለው መንገድ ለጉዳዩ በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ እናሳስባለን፤

★ ህገ-ወጡ የአማራ ክልል መጅሊስ ከእስልምና ጠል አካላት ጋር በመተባበር የሚያደርገውን እኩይ እንቅስቃሴ የሽግግር ጊዜው ፌደራል መጅሊስ እንዲያስቆምና የአማራ ክልል ማህበረሰብ ለረጅም ጊዜ እየጠየቀ ያለውን በአዲስ መልክ የማደራጀት ተግባር በፍጥነት እንዲያከናውን እናሳስባለን፤

★ የክልሉ መንግስት እስከዛሬ ለደረሱት ጉዳቶች ኃላፊነቱን ወስዶ ለተቃጠሉ፣ ለፈረሱና ጉዳት ለደረሰባቸው መስጊዶችና የሙስሊሙ ንብረቶች ተገቢውን ካሳ እንዲከፍልና በራሱ ወጪ ዳግም ሰርቶ እንዲያስረክብ እናሳስባለን፤

★ ይህ ጥቃት ለረጅም ጊዜ በተከታታይ ሲደረግ የነበረው ሙስሊም ጠል የሃይማኖት ሰበካ፣ የጥላቻ ንግግር፣ ፅንፍ በረገጡ የሃይማኖት መምህራን በሙስሊሙ ላይ የታወጀው ጦርነት፣ በሃይማኖት ተቋማት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚታዩ ስሜት ቀስቃሽ ፊልሞችና መግለጫዎች ውጤት መሆኑ የታወቀ ነው። በመሆኑም ሲኖዶሱም ሆነ በተዋረድ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት ሁኔታው ከመባባሱ በፊት ይህንን አደገኛ ስህተት እንዲያርሙ እናሳስባለን፤

★ መንግስትም በመንግስት የስልጣን እርከን ውስጥ ተሰግስገው የሚገኙ፣ በእስልምና እና በሙስሊሙ ጥላቻ የተሞሉ፣ እንዲሁም ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ነቅሶ በማውጣት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድና በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ ያላቸውን አካላት ለይቶ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፤

ሙስሊሙ ህብረተሰብ መብቱን ለማስከበር የሚያስችለውን እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርበታል። ስለዚህም በቀጣይ በሚደረጉት ተከታታይነት ባላቸው ተቃውሞዎች እና ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ህብረተሰባችን ህጋዊነትን እና ፍትሃዊነትን ጠብቆ እንዲሳተፍ፣ እንዲሁም ለፍትህና ለዲሞክራሲ ተቆርቋሪ የሆኑ አካላት በዚህ ኢ-ፍትሃዊነትን ለማውገዝ በሚደረገው ጥሪ ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

መሟላት ያለባቸውን ህጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተን በሚቀጥለው አርብ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የተቃውሞ ሰልፍ የምናደርግ በመሆኑ መላው ህብረተሰባችን በሙሉ ኃይሉና ስነ ምግባር በተሞላበት መንፈስ በመሳተፍ ታሪካዊ አሻራውን እንዲያኖር ጥሪ እናቀርባለን። ዝርዝር ቦታዎቹን እና ተግባራቱን በተመለከተ በተከታታይ መግለጫዎች የምናስታውቅ ይሆናል።

ለእውነት የሚወግንና ለፍትህ የሚተጋ ዜጋን በመፍጠር አገራችንን ወደ ስልጣኔ እናሻግራለን!
አላሁ አክበር!


#Shaashamannee