ከመፈናቀል የተረፉት አርሶአደሮች የሰቆቃ ኑሮ:”እነሱ የአርሶአደሩ ችግር አልታይ ስላላቸው ሰሚ ጆሮ ያለው ካለ የአርሶአደሩን ጥያቄዎች በሰላማዊ ሰልፍ እንጠይቃለን።

ከመፈናቀል የተረፉት አርሶአደሮች የሰቆቃ ኑሮ:”እነሱ የአርሶአደሩ ችግር አልታይ ስላላቸው ሰሚ ጆሮ ያለው ካለ የአርሶአደሩን ጥያቄዎች በሰላማዊ ሰልፍ እንጠይቃለን።

ያ ሁሉ ሮጦ ያልጠገበ ወጣት እንደ ማገዶ የነደደበትን አላማ አሁን እንደቀልድ አንዴ ፅንፈኛ አንዴ ምን እያሉ ሲያላግጡበት ዝም ብሎ ለማየት የሚያስችል ሞራል የለንም።”

ከመፈናቀል የተረፉት አርሶአደሮች የሰቆቃ ኑሮ

ከመሬታቸው የተነቀሉ አርሶአደሮች የደረሰባቸው በደል እንዳለ ሆኖ በቀረችው ይዞታቸው ላይ ህይወታቸውን የሚገፉት ፊንፊኔ የዋጠቻቸው የኦሮሞ አርሶአደሮች በአራቱም የፊንፊኔ አቅጣጫዎች በብዛት ይገኛሉ።

– ጎሮ መስመር :- ቦሌ ለሚ፣ ጭላንፈታ፣ ወረገኑ፣ ቡቺ፣ ኦሾ፣ እዶሮ፣ ገላን ጉራ፣ ኮዬ፣ ቱሉ ዲምቱ …
– ቡልቡላ መስመር :- ሪፌንቲ፣ አባ ሻሜ፣ ቂሊንጦ፣ በሰቃ፣ ወዴሶ፣ መልካ ሸኔ፣ ሳሎ ጊዮርጊስ …
– ሰሚት/አያት መስመር :- መሪ፣ ቃጢላ፣ ጃርሶ፣ ጨፌ፣ አባዶ፣ ፀበል፣ ኤካ-አያት፣ ሎቄ፣ ቤኬ ሰፈራ …
– 02 ማዞሪያ መስመር :- አንቆርጫ፣ ንብ እርባታ፣ ቀርሳ፣ ጉራራ፣ ዳንሴ፣ አቡሽ ሱቅ፣ ጨለለቆ፣ እንጦጦ ተራራ …
– በለቡ መስመር :- ፉሪ፣ ሰፈራ፣ ሀና፣ ቆጣሪ፣ ኤርቱ፣ ቡሬ፣ ጀሞ…
– በአየር ጤና/ቤቴል መስመር :- ቀራንዮ፣ ፊሊዶሮ፣ ከፊል ወለቴ፣ ረጲ …

እነዚህ የአርሶአደር መንደሮች አብዛኞቹ ከከተማ መውጫና መግቢያ ዋና አስፋልት መንገዶች፣ ከሪል እስቴትና ኮንዶሚኒየም መኖሪያ መንደሮች፣ ከኤርፖርት፣ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ቢሆንም መብራት፣ ውሀ፣ መንገድ፣ መሰረተ ልማቶችንና ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት… ሆን ተብሎ ተከልክለዋል። በራሳቸው ወጪ መሰረተ ልማት እናስገባ ሲሉ እንኳ በፕላን ተቃርኖ ክልከላ በማድረግ ፍቃድ እንዲከለከሉ ተደርገዋል። ይባስ ተብሎ የገበሬው ቀዬ ከከተማው እና ከየኮንዶሚኒየሙ የሚመጣ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ፣ አፈርና የግንባታ ፍራሽ፣ የፋብሪካዎች ዝቃጭ መድፊያ ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪ ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው በገዛ መሬታቸው ላይ የመኖሪያ ቤት እንዳይሰሩ ተከልክለዋል። መሬት ሳያጡ፣ የግንባታ ቁሳቁስ ሳያጡ፣ አቅም ሳያጡ በፊት አጥራችሁ ከያዛችሁት ግቢ ውጪ በማሳ እና በግጦሽ ይዞታችሁ ላይ ቤት አትሰሩም ተብለው በመመሪያ ተከልክለዋል። የልጅ ልጅ እንተውና አንድ አርሶአደር በትንሹ 5 ልጅ ሲኖረው ሁሉም እዚያው አንድ ግቢ ውስጥ ከነሚስቶቻቸው/ባሎቻቸው እየኖሩ ይገኛሉ። እምቢ ብለው ቤት ሰርተው ከተገኙም ቤቱ እንዲፈርስ ተደርጎ መሬቱም ወደ መሬት ባንክ ገብቶ መንግስት ይወስደዋል።

አርሶአደሩ መሰረተ ልማትም ሆነ የቤት ግንባታ የተከለከለበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ቀዬው በ’ልማት’ ሰበብ ሲነሳ መንግስት የሚከፍለው ካሳ እና ምትክ ቦታ እንዳይበዛበት እና አርሶአደሩን በነፃ ከቀየው ለማፈናቀል ካለ ፅኑ ፍላጎት ነው።

እስከ አሁን ባለንበት ሁኔታ አርሶአደሩ በገዛ ይዞታው አርሶ ከመብላት ውጪ ይዞታውን ለሌላ ነገር ማዋል አይችልም፣ መንግስት ቦታውን እስከሚረከበው ቀን ድረስም መሰረተልማት አይሟላም፣ በሄክታር የሚቆጠር መሬት ባለቤት ሆኖ ልጆቹ ግን በመኖሪያ ቤት ችግር በአንድ ግቢ ተጨናንቀው ይኖራሉ፥ በተቃራኒው ግን በተቀማ የገበሬው መሬት ላይ ያለከልካይ የተሰሩ ሪል እስቴቶችና ኮንዶሚኒየሞች አስፈላጊው ሁሉ ተሟልቶላቸው ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ። ይህ ከአእምሮ በላይ ነው።


አዲሶቹ የፊንፊኔ ካቢኔ አባላት ወደ አመራርነት ከመጡባት ቀን ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዞር ብለው ያላዩትን አርሶአደር ከኛ በላይ ጠበቃ የለህም ይሉታል። እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው።

ወደ አመራርነት በመጡ በሳምንታት ውስጥ ያልበላቸውን በማከክ የፊንፊኔ ነዋሪዎች ከግንባታ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ብዙ ተንገላተዋል በማለት በስራ ላይ የነበረውን መመሪያ የከተማ ካቢኔውን ሰብስበው እንዲቀየር ወስነዋል። ይህን መመሪያ ሲያሻሽሉ ግን አርሶአደሩ በሄክታር የሚቆጠር መሬት ባለቤት ሆኖ የግንባታ ፈቃድ መመሪያው አርሶአደር አጥሮ ከያዘው ግቢ ውጪ በገዛ የማሳ እና የግጦሽ መሬቱ ቤት እንዳይሰራ የሚከለክለውን ባለማስተካከላቸው እስካሁንም ድረስ ልጆቹ እና የልጅ ልጆቹ በአርሶአደሩ ግቢ ተጨናንቀው እየኖሩ ይገኛሉ። እምቢ ብሎ አርሶአደሩ ቤት ሲሰራ አሁንም ቢሆን የደንብ አስከባሪዎች መጥተው ያፈርሱበታል፣ ቦታውንም ወደመሬት ባንክ እንዲመዘገብ ተደርጎ መንግስት ይወስደዋል። አሁንም አርሶአደሩ በገዛ መሬቱ እንዳይገነባ የሚከለከለው ቀዬው በ’ልማት’ ሰበብ ሲነሳ መንግስት የሚከፍለው ካሳ እና ምትክ ቦታ እንዳይበዛበት እና አርሶአደሩን በነፃ ከቀየው ለማፈናቀል ያለው ፅኑ ፍላጎት ስለቀጠለ ነው። በጣም የሚያሳዝነው ነገር አርሶአደሩ በገዛ መሬቱ የጨረቃ ቤትን ያክል መብት እንኳ አልተሰጠውም።

ሌላውን ወጣት፣ ኳስ ተጫዋች ደጋፊና አርቲስቶች እየጠሩ በአዳራሽ ሲያወያዩ አብረው ሻይ ቡና እየጠጡ ፎቶ ሲነሱ አርሶአደሩ ግን በወረዳ አቅም እንኳ ሰሚ አጥቶ ክፍለከተማና ማዘጋጃ ቢሮአቸው ድረስ ሄዶም እነሱን አግኝቶ ለማነጋገር አልተፈቀደለትም። ጉዳዩ ወደ ሚዲያ ከወጣ በኋላ ባለፈው ም/ከንቲባው የጠራው ስብሰባም ፊንፊኔ ለዋጠቻቸው አርሶአደሮች በይፋ ያልተነገረ እና በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ የተሳተፉበት ነበር።

እነሱን ጭምር ነፃ አውጥቶ ወደ አመራርነት ያመጣውን ለውጥ ለማሳካት ሳይሰስት ልጆቹን ለአውሬ የገበረውን አርሶአደር ጉዳይ ችላ ለማለት አእምሮአቸው እንዴት እሺ እንዳላቸው ይገርመኛል። ድጋሚ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ካልነገራቸው ከነመፈጠሩም አያስታውሱትም። የቁርጥ ቀን ልጆች የኮዬ ፈጬ ጉዳይ ይፋ ባይወጡት ኖሮ አሁን ለይስሙላ ያደረጉትን ያክልም እንኳ አርሶአደሩን ዞር ብለው እምደማያዩ እርግጠኛ እንድንሆን አርገውናል። ም/ከንቲባውን ጨምሮ የከተማው ከፍተኛ አመራሮች የግል ቤታቸውን የሚያሰሩ እስኪመስል ድረስ በየኮንዶሚኒየም ሳይት እየዞሩ ወገባቸውን ይዘው ሲቆጣጠሩ እዚያው አጠገብ ሜዳ ላይ ተበትኖ የወደቀውን አርሶአደር ዞር ብለው ያላዩት ለምንድን ነው? እነሱ የአርሶአደሩ ችግር አልታይ ስላላቸው ሰሚ ጆሮ ያለው ካለ የአርሶአደሩን ጥያቄዎች በሰላማዊ ሰልፍ እንጠይቃለን። ያ ሁሉ ሮጦ ያልጠገበ ወጣት እንደ ማገዶ የነደደበትን አላማ አሁን እንደቀልድ አንዴ ፅንፈኛ አንዴ ምን እያሉ ሲያላግጡበት ዝም ብሎ ለማየት የሚያስችል ሞራል የለንም።

~by Bojja Afriikaa.


Tsegaye Ararssa 


አካነት ፋርፈተኒ ነማ ነማተዬ (ለማተዬ)እኒራፈተኒ