“ለውጡን ከመቀልበስ የሚያድን ሰፊ መሰረት ያለው መንግሥት ያስፈልጋል” ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

“ለውጡን ከመቀልበስ የሚያድን ሰፊ መሰረት ያለው መንግሥት ያስፈልጋል” ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

​​​​​​ኢትዮጵያ የተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳር የሚፈጥር፣ ለነፃና ፍትኃዊ ምርጫ ዋስትና የሚሰጥና በአገሪቱን የታየውን ለውጥ ከመቀልበስ መታደግ የሚችል መሰረቱ የሰፋ መንግሥት እንደሚያስፈልጋት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናግረዋል። ፕሮፌሰር መረራን ጨምሮ የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አመራሮች እንደሚሉት ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች

(dw)—–በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ እና አቶ አዲሱ ቡላላ የሚሳተፉበት መርኃ-ግብር ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. አዘጋጅቶ ታዳሚዎቹን ይጠባበቃል። በመርኃ-ግብሩ”የአገራችን ጉዳይ ያገባናል፤ የሕዝባችን ጉዳይ ይመለከተናል” ለሚሉ በፍራንክፈርት እና አካባቢዋ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ግብዣ ቀርቦላቸዋል። በፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው ዛልባው ሾንሆፍ አዳራሽ ኮከብ አልባው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ተሰቅሏል፤ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” የሚለውን ጨምሮ መፈክሮችም ይታያሉ። የውይይት መርኃ-ግብሩ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ሊጀመር ቢታቀድም በአዳራሹ የሚገኙት አዘጋጆቹን ጨምሮ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

ስምንት ሰዓት ይጀምራል ተብሎ በነበረው መርኃ ግብር ሦስቱ ፖለቲከኞች እና ከ100 በላይ ታዳሚዎች ይገኛሉ ቢባልም ከአንድ ሰዓት በኋላም በቦታው አልደረሱም።

በውይይቱ ሊታደሙ ብቅ ብለው በኢትዮጵያውያን የሰዓት አጠቃቀም እየተደነቁ ተመልሰው የሔዱ ጥቂት ግለሰቦች ታይተዋል። ከሁለት ሰዓት መዘግየት በኋላ አስተናባሪዎች ይቅርታ ጠይቀው የመርኃ-ግብሩን መሰረዝ ተናገሩ።

በአዳራሹ ከነበሩ ጥቂት ሰዎች በጣት የሚቆጠሩት መሰረዙን ሰምተው ሲሔዱ ሶስቱ እንግዶች ዘግይተው ደረሱ። ከ100 በላይ ሰዎች ይመጡበታል የተባለው መርኃ-ግብር ቢሰረዝም ታግሰው የጠበቁ በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከእንግዶቹ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ጀመሩ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነት እና ልዩነት፣ የብሔር ፖለቲካ ፈተና፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኹኔታ እና የጠቅላይ ምኒስትሩ የተመለሱ ጥሪን የመሳሰሉ ርዕሰ-ጉዳዮች ተነስተው መደበኛ ያልሆነ ውይይት ተካሔደ። በውይይቱ ወጥነት ባይኖራቸውም አንገብጋቢ እና አወዛጋቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መነሳታቸው አልቀረም።

በቦታው የተገኙት የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራሮች ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የሚናገሩት ስለ አገራቸው ሐሳብ ለገባቸው እፎይታን የሚሰጥ አልሆነም። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የወጣቶች ክንፍ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ለሆነው አዲሱ ቡላላ “ግድያዎች፣ መፈናቀሎች፣ ግጭቶች እና ስደት በየቦታው እየታየ ነው። ቄሮም ሆነ ፋኖን የመሳሰሉ ወጣቶች የታገሉላቸው፣ የጠየቋቸው ጥያቄዎች እስካሁን መሬት ላይ አልተመለሱም። ያለው የተስፋ ቃል ነው። የተስፋ ቃል የተስፋ ቃል ነው። ወደ ተግባር መለወጥ አለበት። ከዚህም በበለጠ ደግሞ መንግሥት እንደ መንግሥት ሰላም እና ጸጥታን ማስከበር የመጀመሪያ ግዴታው ነው። ዶክተር አብይ ይኸን እየተወጡ አይደሉም። በዛሬው ቀን ብዙ ጦርነት እየተካሔደ ነው። ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ ቤቶች ይቃጠላሉ፤ ሰዎች ይገደላሉ፤ ንብረት ይዘረፋል፤ ቤቶች ይፈርሳሉ። በሌላ ደግሞ መስቀል አደባባይ ቤተ-መንግሥት አካባቢ ግብዣ አለ ፌሽታ ነው። እዚያ ጋ ደግሞ ለቅሶ ነው” ሲል ነገሩ ሁሉ ጉራማይሌ እንደሆነበት ያስረዳል።

የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ሊቀ-መንበሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንደሚሉት በኢትዮጵያ የተያዩ መሻሻሎች ቢኖሩም አገሪቱ ግን አሁንም በመስቀለኛ መንገድ ላይ እየነጎደች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ከቀውስ በሙሉ ለመውጣቷ ተስፋ እንኳ መጥፋቱን የሚናገሩት መረራ “የፖለቲካ እስረኞች ተፈተዋል፤ የፖለቲካ ድርጅቶች በተወሰነ ደረጃ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፤ መናገር ጀምረዋል፤ እነዚህ ነገሮች ጅምሮች ናቸው። ሥርዓቱ ግን አልተለወጠም። አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አልፈጠርንም። በነፃ እና ፍትኃዊ ምርጫ ሥልጣን ላይ የወጣ መንግሥት የለም። የሚመጣው ምርጫ ነፃ እና ፍትኃዊ ለመሆኑ ዋስትና የለንም”  ሲሉ ያስረዳሉ።

አዲሱ ቡላላ እንደ ፕሮፌሰር መረራ ሁሉ ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ መቆሟን ይስማማል። አዲሱ የለውጥ አራማጆች ተብለው የሚወደሱት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ እና እሳቸውን መሰል ፖለቲከኞች ወደ ሥልጣን የመጡት በኢሕአዴግ ፈቃድ ሳይሆን በሕዝብ የተቃውሞ ግፊት እንደሆነ ያምናል። ሕዝብ የሚተማመንበት የራሱ የሆነ ሥርዓት ይፈልጋል የሚለው አዲሱ ጠቅላይ ምኒስትሩ ይኸን ፍላጎት ማሟላት ከተሳናቸው ያላቸውን ድጋፍ ሊያጡ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃል። “ሕዝብ የሚፈልገው የሚተማመንበትን፣ ሊያወጣም ሊያወርድም የሚችለውን ሥርዓት ማበጀት ነው። ያ እስካሁን አልተፈጠረም። ይኸ እንዲፈጠር አብይ በተሻለ ፍጥነት፣ በተሻለ አኳዃን ይኸን ነገር ተግባር ላይ እስካላዋለ ድረስ ድጋፉን ያጣል። ይኸን ድጋፍ ካጣ ደግሞ በውስጥ ችግራቸው ሊጠነክሩበት ይችላሉ። እሱንም ከዚያ ገፍተው ሊያስወጡት ይችላሉ። የሕዝብ ትግልም ወደ ኋላ ሊንሸራተት ስለሚችል አገሪቷ ያለችበት ሁኔታ በጣም የሚያሰጋ መንታ መንገድ ላይ ሆነን ወደ ግራም ወደ ቀኝም መሔድ ያልቻልንበት ሁኔታ ነው ያለው”

ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት

የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በእንግድነት ተቀብለው ቢያንስ በአደባባይ ፌሽታ ውስጥ የከረሙት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ባለፈው ቅዳሜ “ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያሳፍር ሁኔታ ዛሬም ሰዎች ይሞታሉ፤ በሚያሳዝን ሁኔታ ሰዎች ወጥተው መመለስ ይቸገራሉ” ሲሉ ተናግረዋል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች ዛሬም እንዳልበረዱ ጠቅሰው “እንዳታስገድዱን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመቆጣጠር የአገሪቱ ጦር ሰራዊት እና የፌድራል ፖሊስ ጣልቃ እንዲገቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ዋና ጸሀፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ በአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች ግጭት፣ መፈናቀል እና ግድያ መበርታቱን እየጠቀሱ ጠቅላይ ምኒስትሩ አገሪቱን ማረጋጋት በሚችሉ እርምጃዎች ቅድሚያ እንዲሰጡ ይመክራሉ። “ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ እና ለውጥ መምራት አይችልም” የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱት አቶ ደጀኔ “እኛ ቁጭ በል እና ተቋማዊ አድርግ፣ አረጋጋ፣ ብቻህን ካልቻልክ ከሚችሉ ፓርቲዎች ጋራ ቁች ብለህ ሥራ ብለን 16 ነጥብ ያለው የመደራደሪያ ነጥብ ሰጥተንዋል። ብቻሕን መምራት አትችልም እና ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት አደራጅ የሚል ጥያቄ ጠይቀናል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አቶ ደጀኔ የጠቀሱት እና 16 ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥነው የድርድር ሰነድ  የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስን ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎችን በአባልነት ባቀፈው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በኩል ለመንግሥት የቀረበ ነው። ፕሮፌሰር መረራ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥር እና ሁሉን አቀፍ የሆነ የፓርቲዎች ስብሰባ እንዲደረግ ለመንግሥት ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል። በፓርቲዎቹ የስብሰባ ውጤት የሚመሰረተው ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት በተለይ ለሶስት ጉዳዮች ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ መረራ ያስረዳሉ።

“አንደኛ ለሁለት አመት የተረጋጋ ሁኔታ የሚፈጥር መሠረቱ የሰፋ መንግሥት ያስፈልጋል። ሁለተኛ ለነፃ እና ፍትኃዊ ምርጫ ዋስትና የሚሰጥ ፣ ሕዝቡ ድምፄ አይሰረቅም እስኪል ድረስ ሊያደርስ የሚችል ለነፃ እና ፍትኃዊ ምርጫ ዋስትና የሚሰጥ መንግሥት ያስፈልጋል፤ ለውጡን ከመቀልበስ አደጋ የሚያድን ወይም ሊደግፍ የሚችል ሰፊ መሰረት ያለው መንግሥት ያስፈልጋል”

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ላቀረበው የእንደራደር ጥያቄ የጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን ፕሮፌሰር መረራ ተናግረዋል። ድርድሩ የሚካሔድበት ቀን ግን አልተቆረጠም። አቶ ደጀኔ ጣፋ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ እምባ ጠባቂ፣ ጸረ-ሙስና የኢሕአዴግ አሽከሮች ናቸው” ሲሉ ፓርቲያቸው በተቋማቱ ላይ ዕምነት እንደሌለው ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ የታዩት ለውጦች ለነፃ እና ፍትኃዊ ምርጫ በቂ አይደሉም የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ እንፈልጋለን፤ የመከላከያ እና የደኅንነት ኃይሉ እንዲሻሻል እንፈልጋለን። ምርጫ ቦርድ እንዲሻሻል እንፈልጋለን። ሚዲያ እንዲሻሻል እንፈልጋለን። በተግባር ገና ናቸው። ተቋማት አልተለወጡም”ሲሉ ተናግረዋል።

እነ ፕሮፌሰር መረራ ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረቡት ጥያቄ እስኪሳካ የፓርቲያቸውን ቢሮዎች በማስፋፋት ላይ ይገኛሉ።ፓርቲው በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልሎች 200 ገደማ ቢሮዎች ሊከፍት ዝግጅት ላይ ይገኛል።

በፍራንክፈርት የተዘጋጀው መርኃ-ግብር እንደታቀደለት ባይሳካም ሦስቱ ፖለቲከኞች ሐሳባቸውን አጋርተዋል። ፖለቲከኞቹ በሌሎች የጀርመን ከተሞች በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች ይሳተፋሉ። አዘጋጆቹ በጉዳዩ ላይ ቃለ-መጠይቅ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ ሰብሳቢ አቶ አፈወርቅ ተፈራ በከተማዋ የሚካሔዱ ሌሎች ስብሰባዎች በመኖራቸው፣ የዕረፍት ወቅት በመሆኑ እንዳቀዱት አለመካሔዱን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ