ኦነግ የዋና ጽህፈት ቤቱን “ሕገ -ወጥ ብርበራ” ምርጫ ቦርድ እንዲመረምር ጠየቀ

ኦነግ የዋና ጽህፈት ቤቱን “ሕገ -ወጥ ብርበራ” ምርጫ ቦርድ እንዲመረምር ጠየቀ

“የድርጅቱ ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ ሌሎች አባላት በኃይል ከቢሯቸው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ እኛ በማናውቀው ምክንያት ከፓርቲው አመራሮችና ሰራተኞች ውስጥ በከፊል ወደ ጽህፈት ቤቱ እንዲገቡ ምንጩ ያልታወቀ የስም ዝርዝር ይዘው ከፊሎቹን ደግሞ እንዳይገቡ በማድረጋቸው የፓርቲው ወቅታዊ ሥራ እንዲስተጓጎል ተደርጓል” ይላል የኦነግ ደብዳቤ

(dw)–የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በዋና ጽህፈት ቤቱ አድርገዋል ያለውን ሕገ -ወጥ ብርበራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲመረምር ጠየቀ። ፓርቲው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፃፈው ደብዳቤ የኦነግ ሊቀ-መንበር ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ አባላቱ እና ደጋፊዎቹ በመንግሥት “ማስፈራሪያ እና አፈና እየደረሰባቸው ነው” ሲል ከሷል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የፈረሙበት እና ትናንት ማምሻውን በፓርቲው የፌስቡክ ገጽ የተሰራጨው ደብዳቤ “ከሐምሌ 25 ጀምሮ ገዢው ፓርቲ ባሰማራቸው የጸጥታ አካላት በዋና ጽህፈት ቤታችን ላይ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሕገ-ወጥ ብርበራ” ተደርጓል ሲል ከሷል።

“የድርጅቱ ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ ሌሎች አባላት በኃይል ከቢሯቸው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ እኛ በማናውቀው ምክንያት ከፓርቲው አመራሮች እና ሰራተኞች ውስጥ በከፊል ወደ ጽህፈት ቤቱ እንዲገቡ ምንጩ ያልታወቀ የስም ዝርዝር ይዘው ከፊሎቹን ደግሞ እንዳይገቡ በማድረጋቸው የፓርቲው ወቅታዊ ሥራ እንዲስተጓጎል ተደርጓል” ይላል የኦነግ ደብዳቤ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ፌድራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የሰላም ሚኒስቴር እና የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን በግልባጭ እንዲደርሳቸው የተደረገው ይኸው ደብዳቤ “በገዢው ፓርቲ ከድርጅቱ ሊቀ-መንበር ጀምሮ እስከ ታችኛው የድርጅት አባሎቻችን እንዲሁም የኦነግ የፖለቲካ አመለካከት የሚደግፉ ግለሰቦችን ማስፈራሪያ እና አፈና እየደረሰባቸው ነው” ሲል ይከሳል።

“ይኸ በተለመደው አሰራር ጠንካራ እና ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥትን ሥልጣን ያለ አግባብ መጠቀም ከውድድር ውጪ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያሳያል” የሚለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲመረምር ጠይቋል።

“እየደረሰብን ያለውን ሕገ -ወጥ የጽህፈት ቤት ብርበራ፣ ወደ ጽህፈት ቤት እንዳንገባ እየተደረገ ያለውን ሕገ-ወጥ ድርጊት እንዲያስቆምልን፣ የእርምት እርምጃ እንዲወስድልን” ብሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “የጉዳዩን ስፋት እና ጥልቀት መርምሮ ካመነበት ወደ ዐቃቤ ሕግ እንዲመራ” ሐሳብ አቅርቧል።