ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድር ጥሪ አቀረበ

ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድር ጥሪ አቀረበ

JONATHAN ALPEYRIE

(bbcamharicnews)—–በትናንትናው ዕለት ኦነግ ባወጣው መግለጫ ዘለቄታዊ ሰላም እንዲመጣ ለህዝቡ በተለይም ለኦሮሞ ህዝብ ጥሪ አቅርቧል።

“ሁሉም ሰላም ወዳድ ወገኖች፣ በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ይህ መንግሥት እያካሄደ ያለውን ጦርነት እንዲያቆም አስፈላጊ ጫና ማድረግ ያስፈልጋል” ብሏል።

መግለጫው በተጨማሪ በኦነግና በመንግሥት የተደረሱት ስምምነቶችንም ለማደስና ዘላቂነት እንዲኖረው ሶስተኛ ወገን እንዲሳተፍበት አማራጭ ይዞ ቀርቧል።

” የተደረሰውን ስምምነት በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን የሚመለከት፣ አሁን የተፈጠረውን አዲስ ሁኔታ ለማስታረቅና ለመፍታት በሚያስችል ሁኔታ ለማሳደስና ለማጠናከር (to consolidate)፣ ሦስተኛ ወገን በሚገኝበት በአዲስ እንድንወያይበት ጥሪ እናቀርባለን።”ብለዋል።

ስምምነቱን በተመለከተ የግንባሩ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ ደባ ለቢቢሲ “ሶስተኛ ወገን በአካል ባይገኝም ነገር ግን ማወቅ ያለባቸው አካላት አውቀዋል” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ስለ ሶስተኛ ወገን ማንነት መግለጫው በዝርዝር ያስቀመጠው የለም።

“በኢትዮጵያ ፖለቲካ የኦነግ ስም ቅመም ነው” የኦነግ የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ

የኦነግ እና የመንግሥት እሰጣገባ

ሁለቱ አካላት በምዕራብ ኦሮሚያ ላይ ለሚደርሱ ግድያዎች እየተወነጃጀሉ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ኦነግ “ኢሕአዴግና የመንግስት ስርዓቱ ከጸረ-ዴሞክራሲ አቋምና አካሄዱ ፈቀቅ ባለማለቱ እዉነተኛ መስዋዕትነት የከፈሉት ወገኖች ለዉጡን ለማሳካትና ስርዓቱንም ለማሻሻል ተሳታፊ እንዲሆኑ አልተደረገም። በመሆኑም በስርዓቱ የሚካሄዱ አፈናዎች፣ እስራት፣ ግድያ፣ እና ሌሎችም የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዛሬም ድረስ እንደቀጠሉ ናቸዉ።” ብሏል።

መግለጫው ጨምሮም በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ዘመቻ እንደከፈተበት ገልፆ ስምምነቶቹም እንዳይተገበሩ እንቅፋት እየሆነ ነው ብሏል።

ከጥቂት ወራት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሚመራ ልዑክ ወደ ኤርትራ ተጉዞ ከኦነግ ጋር ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል።

በርካቶች መንግሥት ከኦነግ ጋር አሥመራ ላይ የደረሰውን ዝርዝር ስምምነት ለህዝብ ይፋ አላደረገም በማለት መንግሥትን ይወቅሳሉ።

የኦነግ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳም በቅርቡ ለሃገር ቤት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ በሁለቱ ወገን የተደረሰው ስምምነት ለህዝብ ግልጽ እንዳይሆን እያደረገ ያለው መንግሥት ነው ብለዋል

የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ፤ የተደረሰው ስምምነት ሆን ተብሎ ዝርዝሩ ከህዝብ ተደብቋል የተባለው ከእውነት የራቀ ነው ያሉ ሲሆን፤ የስምምነቱ ተፈጻሚነትም በፈለጉት ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ኦነግ ከመንግሥት ጋር በተኩስ አቁም ስምምነት መከበር ፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አስከባሪ እና ደህንነት አካል ገለልተኛ እንዲሆን ማድረግ፣ የኦነግ ሠራዊት ወደ መንግሥት ኃይል እንዲካተት ማድረግ ላይ የተስማማ ቢሆንም አለመከበራቸውን ግን ይናገራል።

ኦዲፒ በበኩሉ በተለያዩ የክልሉ ዞኖች ውስጥ እንደ አዲስ ጦር መልምሎ እያሰለጠነ እንደሆነ በመግለፅ፤ የኦነግ አመራር በጠቅላላው ሰላማዊ ትግልን እንደ አማራጭ አድርጎ መቀበሉ አጠራጥሮናል በማለት የወነጀለው ሲሆን የኦነግ አመራር እና በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የጦር አመራሮች የሚሰጡት መግለጫዎች የተለያዩ ናቸው ብሏል።

አቶ አዲሱ በተጨማሪ ሕገ-ወጥነት እየተስፋፋ ነው፤ አመራሮቻችንም እየተገደሉ ነው ብለዋል።