ኦነግ የመንግሥት ሠራዊት በተለያዩ ቦታዎች በመሰማራቱ ላይ ጥያቄ አለው

ኦነግ የመንግሥት ሠራዊት በተለያዩ ቦታዎች በመሰማራቱ ላይ ጥያቄ አለው

JONATHAN ALPEYRIE

(bbc)–ከሰሞኑ በኦሮሚያ አካባቢ በተፈጠሩ ግጭቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስራ አስፈፃሚ እንዲሁም የፖለቲካና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ጋሹ ለሜሳ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ጥያቄ፡ አስመራ ላይ ከመንግሥት ጋር ባደረጋችሁት ስምምነት መሠረት ነገሮች እየሄዱ እንዳልሆነ ታነሳላችሁ፤ መንግሥት ማድረግ ሲኖርበት ያላደረገው ነገር ምንድነው?

አቶ ጋሹ፡ አስመራ ላይ በተደረገው ስምምነት አገር ቤት እንደገባን ብዙ ነገሮች ነበሩ፤ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሚሟሉ ማለት ነው። አንድ በሰላማዊ መንገድ ለአገሪቱ የሚስማማውን የፖለቲካ ሂደት ማካሄድ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በ1992 (እአአ) ከአገር ስንወጣ የተዘረፉ የኦነግ ንብረቶች፣ ቢሮዎች ብዙ ነገሮቸ አሉ። እነዚህ ነገሮች ባግባቡ እንዲመለሱ፤ የ”ኦሮሞ ሪሊፍ አሶሴሽን” የሚባል ሰብአዊ ድርጅት ነው፣ እሱም ተመዝግቦ በሥራ ላይ እንዲውል ነበር የተስማማነው። [እነዚህ] ሁኔታዎች እስካሁን ድረስ እምብዛም አልተሟሉም። አንድ ጉለሌ ያለ ቢሮ ብቻ ከፊሉ ተመልሷል፤ ሌላው ትልቁ አልተመለሰም። እና ይሄ ይሄ ነው ያለው።

• “ለውጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ውጤት ነው” ዳዉድ ኢብሳ

በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ እንፍታ ነው የተባለው ከዚያ በኋላ መንግሥትም ተመልሶ አላስፈላጊ ጦርነት የመቀስቀስ ሁኔታ ይታያል ፤ በድንበር አካባቢ። እና ሕዝቡንም ደግሞ በየከተማው በየገጠሩ በጦር ማስፈራራት ጦር ማስፈር ይታያል። እነዚህ ችግሮቸ ናቸው ያሉት፤ እነዚህ ደግሞ እንደገና በንግግር በመመካከር የአገር ሽማግሌዎችን በመላክ እንፈታለን ብለን በዚያ ሂደት ላይ ነው ያለነው።

ጥያቄ፡ ምዕራብ ኦሮሚያ ላይ ያለ የኦነግ ጦር ወደ ካምፕ አልገባም። ለምን?

አቶ ጋሹ፡ አዎ ይሄ በሂደት ላይ ነው ያለው። እኛም እየተመካከርን ነው ። ይሄ በሂደት ላይ እያለ በመንግሥት ጦር በዚያ አካባቢያ ጦርነት ተከፈተ። ጦርነቶች ተቀሰቀሱ። ተገቢ ያልሆ ፕሮፓጋንዳ፣ የትጥቅ እናስፈታለን የሚል ዛቻና አነጋገር፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው ሲሰራጭ ነበር። ይሄ ሁሉ በሕዝቡ ዘንድ አጠያያቂ ሆነ። የመንግሥት የጦርም ደግሞ በየከተማውና በአካባቢው በስፋት በመስፈሩ ይሄ ሁሉ አጠያያቂ ጉዳይ ሆኖ እስካሁን ሳይሳካ በዚህ ሂደት ላይ ነው ያለው። ለወደፊቱ ግን ልክ እንደተስማማነው በሰላማዊ መንገድ እንፈታለን ብለን ነው ያቀድነው።

• «ኦነግ ሀገር ለመገንጠል ነው የምሠራው ብሎ አያውቅም» ሽጉጥ ገለታ (ዶ/ር)

ጥያቄ፡ ማክሰኞ ምዕራብ ሸዋ ላይ ምንድነው የተፈጠረው? በኦነግ ታጣቂዎችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጦች ነበሩ?

አቶ ጋሹ፡ እኛም እንደዛው ነው የሰማነው፤ ያው ከሚዲያ ነው የሰማነው እንጂ በእኛ በኩል ተኩስ ልውውጡ የተደረገበት ቦታ ያለ አይመስለኝም። የእኛ ሠረዊትም ደግሞ አላግባብ የተኩስ ልውውጥ የሚያደርግበት ቦታም አይደለም ያለው። ነገር ግን አሁንም ምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የኦነግ ሠራዊት አለው፤ እየተንቀሳቀሰ ያለ። የታጠቀ የኦነግ ኃይል ምዕራብ ኦሮሚያ ላይ ይንቀሳቀሳል።

ጥያቄ፡ በምን አግባብ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው?

አቶ ጋሹ፡ ምዕራብ ኦሮሚያ ላይ በጣም ትኩረት ተደረገበት እንጂ የሚንቀሳቀስ የታጠቀ የኦነግ ሠራዊት ምዕራብ ኦሮሚያ ብቻ አይደለም ያለው። በደቡብም አለ፣ በመሐልም አለ፣ በምሥራቅም አለ። በሰፊው የኦሮሚያ ቦታዎች እየተንቀሳቀሰ ነው ያለው። ግን ዋንኛው ትኩረትና የፖለቲካ ጫወታ ያለው በምዕራቡ ላይ ነው።

• በኦነግ እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በምዕራብ ኦሮሚያ ግጭት እንደነበር ተነገረ

እና ሠራዊቱ አሁንም ልክ እንደ ‘ጎሪላ’ ነው ያለው። ግን ያላግባብ ጦርነቶችን ውጊያና ግጭቶችን እየቀሰቀሰ አይደለም። ነጻ ባወጣቸው መሬት ላይ ሰፍሮ ነው ያለው። ግን ደግሞ ቀደም ሲል እንዳልኩት አስመራ ላይ በተስማማነው ውል የሠራዊቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዴት እንደሚሆን በሂደት ላይ ነው ያለው። ሰራዊቱ ግን እንዳለ ነው ያለው።

ጥያቄ፡ የኦነግ ሠራዊት ነጻ ባወጣቸው መሬቶች ላይ ሰፍሮ ነው ያለው ብለውኛል። መሬቶቹን ከማን ነው ነጻ ያወጣቸው?

አቶ ጋሹ፡ ከወራሪ መንግሥት ወይም ከወራሪ ሠራዊት ነው ነጻ ያወጣው። እኛ ወራሪ ብለን ወይም ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ብለን ከምንፈርጃቸው ከወያኔ ወራሪዎች ነጻ አውጥቶ ነው በአካባቢው አሁን ሰፍሮበት ያለው።

ጥያቄ፡ መንግሥት በየአካባቢው ያሰማራቸው ወታደሮች ችግር እየፈጠሩ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ጋሹ፡ አዎ እኛ ችግር ይፈጥራሉ ነው የምንለው። ጠላት በሌለበት ቦታ ጠላት ብሎ ሕዝቡ ላይ ማስፈር ችግር ይፈጥራል። ሕዝቡና መንግሥት እንዲጋጭ ያደርጋል። የሕዝቡን ሰላም ያውካል። ሕዝቡ ባለፈው ሥርዓት በጣም በጣም ነው በሥነ ልቦናው የተጎዳው።

• ኦነግ እና መንግሥትን ለማግባባት የሃገር ሽማግሌዎች እየጣሩ ነው

[ያኔ] ሰራዊቱ በየከተማው እየሄደ የሕዝቡን ቤት ይፈትሻል፣ ሕዝቡን ይዘርፋል፣ ያላግባብ ተማሪዎችን ያስራል፣ ይገድላል፣ ይደበድባል፣ ወደ ፍርድ ቤት ይወስዳል፤ ያ ሁሉ ሰቆቃ በሕዝባችን ላይ አለ ማለት።

አሁንም ደግሞ ሠራዊቱ በየከተማው ከባድ መሳሪያ በየመኪናው ላይ ደግነው ሲሄዱ ሕዝቡ ይሰጋል። ይሄ ደግሞ መንግሥትና ሕዝቡን ያጋጫል ማለት ነው። ሕዝቡ አመኔታ ያጣል። ይሄ አግባብ አይደለም፤ ሰራዊት ከከተማ ምን ያደርጋል? ገጠርም ቢሄድ ደግሞ አርሶ አደሩን ሕዝብ እንደዛው ሰፍሮበት ያላግባብ መደብደብ ማሰር ይሄ ሁሉ ራሱ ትክክል አይደለም። ሠራዊት ካምፕ ውስጥ ነው የሚኖረው። መንግሥት በሲቪሉ ላይ የሚያሰፍርበት ሁኔታ ተገቢ አይደለም። ስለዚህ ይሄ ችገር ይፈጥራል።

እንደገና ደግሞ በሰላማዊ መንገድ እንፈታለን ብለን፣ የአገር ሽማግሌዎችም ገብተውበት፣ በሁለቱም በኩል የተመረጡ አካሎች ሰላም ለመፍጠር በሚጥሩበት ጊዜ ሄዶ ያላግባብ ግጭት ከኦነግ ሠራዊት ጋር መፍጠር በራሱ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ አያመጣም። ነገሮችን በውጊያ ከሚፈታ በውይይት መፍታት ነው ተገቢ። ጦርነት ያብቃ ብለን ነው እኛ የምናምነው። ይሄ የኦነግ አመለካከት ነው ማለት ነው።

ጥያቄ፡ ከንግግርዎ የምረዳው መንግሥት ኦሮሚያ ላይ የጸጥታ ኃይል ማስፈሩ ስህተት ነው እያሉኝ ይመስላል?

አቶ ጋሹ፡ ያልኩት የመንግሥት ጸጥታ ኃይል ጸጥታ ባልሰፈነበት ቦታ ሰፍሮ ጸጥታን ማምጣት ነው እንጂ ጸጥታ ባለበት በሲቪሉ ሕዝብ መሐል ማስፈር ትክክል አይደለም ነው። ወታደሮችን ሁከት በሌለበት ቦታ፤ ሕዝቡ በሰላም በሚኖርበት ቦታ ሂዶ አስፍሮ ሕዝቡን ማወክ ተገቢ አይደለም። [እርግጥ ነው] የጸጥታ አስከባሪ ጸጥታ በሌለበት ቦታ መስፈር አለበት። ለምሳሌ በየድንበሩ ከኦሮሚያ ሕዝብና ከሌሎች ጎሳዎች ጋር ግጭት ነበር። ያንን ግጭት ማስቆም አለበት። ሠራዊት እዚያ ቦታ ነው የሚያስፈልገው።

ከተማ ውስጥ ደግሞ ሁከት ከተፈጠረ፣ ሕዝቡ ጸጥታ ከሌለው ፖሊሶች አሉ። ኦሮሚያ ፖሊስ አለ፤ የሌላም ፖሊስ አለ፤ በየክልሉ። ፖሊሶች ጸጥታ ማስከበር ያወከውንም በአግባቡ ለሕግ ማቅረብ አለባቸው።

• ከምዕራብ ኦሮሚያ ከተሞች ጥቃት ጀርባ ያለው ማን ነው?

ጥያቄ፡ አሁን ከኦነግ ታጣቂዎች ጋር ግጭቶች አሉ?

አቶ ጋሹ፡ አንዳንድ ቦታዎች አሉ። ይሄ እንዲቆም ደግሞ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው። ጦርነት አያስፈልግም። ችግር ካለ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ መፍታት ነው። እና አላግባብ ግጭቶች በየቦታው ይታያሉ።

ጥያቄ፡ የጸጥታ ችግር በሌለበት ቦታ ሠራዊት ማስፈር አይገባም እያሉኝ ነው። ከዚህ አንጻር አሁን ኦሮሚያ ላይ ሠራዊቱ ባላስፈላጊ ሁኔታ ሰፍሮባቸዋል የሚሉት የትኞቹ ቦታዎች ላይ ነው?

አቶ ጋሹ፡ በምዕራብ ወለጋ በብዙ ቦታዎች ተሰማርቷል። በመሐከለኛ ቦታዎች ብዙ ቦታ ተሰማርቷል። ነቀምት፣ ጊምቢ፣ ቤጊ እና ደንቢዶሎ በመሳሰሉ የምዕራብ ከተማዎች ውስጥ ሰራዊት ይሰማራል። በዚህ አባይ መንገድ ጊዳ፣ ኡኬ-ቀርሳ የሚባሉ፣ በምዕራብ ሸዋ በኩል እስከ ባኮ ብዙ ቦታዎችን መጥቀስ እንችላለን። ሠራዊቱ ተጭኖ በከተማ ሲያልፍ ይታያል። ይሄ ሁሉ ለሕዝቡ ስጋት ነው። ካለፈውም ሥርዓት ያ ሁሉ ሰቆቃ አለበት። አሁንም ደግሞ ምን መጣብን እያለ ነው ሕዝቡ።

ሕዝቡ የጸጥታ ችግር እንዳለበት ለኦነግም እየነገረ ነው፤ ይሄ ሁሉ ነው ያለው። እና ሠራዊት መኖር ያለበት በካምፑ፤ ኃይለኛ ችግር ከተፈጠረና በድንበር ላይ ችግር ካለ ደግሞ እዚያ ሰላም ማስፈን የሠራዊቱ ፋንታ ነው ማለት ነው።

• ”በደኖ የሚባል ቦታን ረግጨው አላውቅም” አቶ ሌንጮ ለታ

ጥያቄ፡ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ግጭቶች አሉ። ለነዚያ ግጭቶች የመንግሥት ሰራዊት መሰማራቱ ችግር ነው ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ ጋሹ፡ ግጭቶችን ለማብረድ የመንግሥት ሠራዊት መሰማራቱ ግዴታ ነው፤ አለበትም። በየድንበሩ ባለው ግጭት ሰበብ አድርጎ ወደ ከተማ መጥቶ ሕዝቡን ማወክ ነው ችግር። ግጭቱን ሳያበርዱ በዚያ ሰበብ በየከተማው ሰራዊቱን ማጓጓዝ፣ ማስፈር ተገቢ አይደለም ነው የምንለው። ግጭት መብረድ አለበት። ያ ግጭት ከሳምንት እስከ ወር፣ ከወር እስከ ዓመት መቆየት የለበትም።

ግጭቶች እየተፋፋሙ ነው ዛሬም ድረስ፤ ሰው እየተፈናቀለ ነው፣ እየተገደለ ነው፣ ከቦታ ቦታ ተፈናቅሎ ብዙ ፍዳ እያየ ነው። ያ ሁሉ ዕዳ ደግሞ መልሶ ሕዝቡ ላይ ነው የሚወድቀው። ሠራዊቱ ያንን ማብረድ ነው እንጂ ወደ ከተማ ተመልሶ ሕዝቡን ማወክ የለበትም።

ጥያቄ፡ ለግጭቶች የኦነግ ሠራዊት እየተወነጀለ ነው እኮ። እጁ አለበት ይባላል።

አቶ ጋሹ፡ መረጃ ካለ በዚህ ቦታ እንደዚህ አድርጓል፤ በዚህ ቀበሌ እንዲህ አይነት ግጭት ፈጥሯል ይባል። በዚህ ሰዓት፣ በዚህ ቀን፣ በዚህ ደቂቃ የእገሌን ንብረት ዘርፏል የሚል ተጨባጭ የሆነ መረጃ ያየነው የለም እኛ፤ ተጨባጭ መረጃ ኖሯቸው በዚህ ቀን በዚህ ሰዓት በዚህ ቦታ እከሌ እንዲህ ተደረገ የሚል የለም። ግን ደግሞ እንደዚህ እንሰማለን በየሚዲያው፤ ይሄ ለ27 ዓመት ሲጠቀሙበት የነበረ ነው።

ሁላችንም የምናውቀው በኢትዮጵያ ፖለቲካ የኦነግ ስም ቅመም ነው፤ የኦነግ ስም ከሌለበት ፖለቲካ አይጥምም [ልክ በቃ ጨው እንዳጣ ምግብ ማለት ነው]። ስለዚህ ለወንጀልም፣ ለሁካታም፣ ለድክመትም፣ ለሽንፈትም ማን መጠራት አለበት? ኦነግ ነው! ይህን ሕዝቡ በደንብ ያውቃል፤ ዓለምም ያወቀው ነገር ነው።

ባለፈው የወያኔ ሥርዓትም በየፓርላማው በየምኑ ኦነግን ካልወነጀሉ ለድርጊታቸው ለጥፋታቸው ሰበብ አልነበራቸውም።

ጥያቄ፡ ስለዚህ አሁን ኢህአዴግ ኦነግን እየወነጀለው ነው እያሉኝ ነው?

አቶ ጋሹ፡ በብዙ ቦታ ኦነግ ያላደረገውን አደረገ ማለት ያለ ነው፤ ለሆነው ነገር ሁሉ ኦነግ ነው ማለት ያለ ነው። እናንተ ጋዜጠኞችም የመንግሥት አካልም ሆነ የሚወነጅለውን አካል ተጨባጭ በሆነ ነገር ላይ አትጠይቁም፤ የት? መቼ? እንዴት? የሚል ጥያቄ አትጠይቁም።

በቃ ይሄን ነገር [አሁንማ] ለምደነው አይሰማንም፤ ኦነግን ያላግባብ መወንጀል ስህተት እንደሆነ ሕዝባችን በደንብ ተረድቷል። ኦነግ አያጠፋም ማለት ግን አይደለም፤ [እንደዛ ማለት] አንችልምም። [ነገር ግን] ኦነግ ባጠፋው ቦታ እኛ ከስህተታችን በደንብ ነው የምንታረመው።

ጥያቄ፡ አቶ ለማ መገርሳና አቶ ዳውድ ኢብሳ በጋራ ለመሥራት ስምምነት አድርገው ነበር። በጋራ እንሠራለን ትላላችሁ። ፍቃደኝነትም ታሳያላችሁ። ደግሞም ትወነጃጀላላችሁ። ስምምነታችሁ ፍሬ ማፍራት ያልቻለው ለምንድነው?

አቶ ጋሹ፡ የምትይው ይገባኛል። ግን ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጋር ስምምነት ላይ ነው ያለነው። በኦሮሞ ችግሮች ሁሉ አንድ ላይ ለመሥራት ስምምነት ላይ ነው ያለነው። አንዳንድ ሰዎች የሚያጋንኑት ከስምምነታችን ይልቅ ልዩነታችን ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ ነው። ብዙ የተነጋገርንባቸው፣ የተሰምማንባቸው፣ በመሬት ላይም እየሠራንባቸው ያሉ ነገሮች አሉ፤ ለወደፊቱም ደግሞ በመልካም እንጨርሳለን ማለት ነው።

ትናንሽ ነገሮች ካሉ፤ አለመስማማቶች ካሉ ይሄንን በሰላማዊ መነግድ እንጨርሳልን። ጥሩ ጥሩ የሆኑ ሽማግሌዎች አሉ፤ አባገዳዎች አሉ፤ ልዩነታችን በቀላሉ የምነፈታበት ሁኔታ አለ።

እኛም ደግሞ እንደ ድሮ አይደለም፤ የኦሮሚያ መንግሥት ፕሬዝዳንትም ሆነ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ካለፉት ጊዜያት የተማርናቸው ነገሮች አሉ። እኛም እርስ በራሳችን እየተነጋገርን በቀላሉ እንጨርሳለን፤ ልዩነት ግን መፈታት አለበት።

ጥያቄ፡ ኦነግ ምርጫ ቦርድ ተመዘገበ?

አቶ ጋሹ፡ አልተመዘገብንም፤ ግን በሂደት ላይ ነው ያለነው፤ እንመዘገባለን ብለን ነው እየጠበቅን ያለነው።

ጥያቄ፡ ምንድነው ያጋጠመው ችግር?

አቶ ጋሹ፡ በሂደት ላይ ነው ያለው፤ ይሄ ነው ተብሎ አሁን ለሚዲያ የሚነገር ነገር የለም።