ኦነግ እና የኦሮሞ ህዝብ:-ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ

ኦነግ እና የኦሮሞ ህዝብ
—-
ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
—-
እኔ (እኛ) የኦነግ ትውልድ አባል ነኝ፡፡ ከኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከልቤ ስደግፈው የነበረው ድርጅትም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ነው፡፡ ይህ ድርጅት አሁን ባለው ወቅታዊ ጥንካሬው የዛሬ 27 ዓመት የነበረውን ያህል አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ኦነግ ተዳክሟል ብለን እንደ አሮጌ ጣሳ የምንወረውረው ድርጅት አይደለም፡፡ የኦሮሞ ድርጅቶች ሁሉ ለህዝባቸው ነፃነት፣ አንድነት፣ ህልውና እና ክብር ያደረጉት ትግል ሲመዘን የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ነው። የኦሮሞ ህዝብ ትግል በተደራጀ ሁኔታ መካሄድ ከጀመረባቸው የ60ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ኦሮሞዎችን በነቂስ አሰልፎ ለነፃነታቸው ሲያታግል የኖረው ድርጅትም ኦነግ ነው፡፡

“ኦነግ እድሜ ብቻ ነው ያስቆጠረው፤ በረጅም ዘመኑ በተጨባጭ ያስመዘገበው ውጤት የለም” የሚሉ ወገኖች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይህ ኦነግን የማያውቁ ወገኖች የሚዘበዝቡት ደካማ ሙግት ነው፡፡ ኦነግ በፖለቲካውም ሆነ በሌላው ዘርፍ እጅግ በርካታ ውጤቶችን ነው ያስመዘገበው፡፡ ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ ህልውናን ለማስጠበቅ፣ የህዝቡን ማንነትና ክብር ለማስመለስ፣ የህዝቡን የፖለቲካ ንቃት ለማሳደግ፣ የትግል ርእዮት ለማስጨበጥ፣ ቋንቋውንና ባህሉን ለማሳወቅ እና ለማሳደግ፣ እንዲሁም ማህበራዊ ሕይወቱን ለማጎልበት ያከናወናቸውን ተግባሮች ብቻ ብንጠቃቀስ ግንባሩ በታሪክ ውስጥ ያለው ስፍራ ከፍተኛ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

• የኦሮሞ ህዝብን ማንነት ማጥፋት የተጀመረው ህዝቡ የሚጠራበትን ትክክለኛ ስም በመቀየር ነበር። ገዥዎች “ኦሮሞ” የሚለውን ስም አጥፍተው አፀያፊ ፍቺዎች የሰጡትን ስም በግዴታ በህዝቡ ላይ ጭነው ነበር። ይህንን ሆን ተብሎ የኦሮሞ ህዝብን ለማዋረድ የተደረገውን ሴራ ተዋግቶ ህዝቡ በዓለም ዙሪያ “ኦሮሞ” በተሰኘው ትክክለኛ ስሙ ብቻ እንዲታወቅ ያደረገው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ነው።

• በታሪክ ሂደት ተበታትነው ወደ መረሳሳት ደረጃ ደርሰው የነበሩትን የምስራቅ፣ የምዕራብ፣ የሰሜንና የደቡብ ኦሮሞዎችን ሙሉእ በሆነ ሁኔታ አንድ ላይ ያሰባሰበው ድርጅት ኦነግ ነው። አሁን ያለው የኦሮሞ ህዝብ አንድነት የኦነግ የስራ ውጤት ነው።

• የኦሮሞ ህዝብ በባህሉ፣ በቋንቋው፣ በትውፊቱና በታሪኩ ሳያፍር ማንነቱን እንዲገልጽና ኦሮሞነቱን በየትኛውም መስክ እንዲያሳውቅ ከማንም በላይ የጣረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ነው።

• ኦነግ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አባት ነው። Orommumaa እና Sabboonummaa የሚባሉትን ጽንሰ ሐሳቦች በመቅረጽ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ያበለፀገው ኦነግ ነው። ከሰላሳ ዓመታት በፊት ኢብሳ፣ ቶላ፣ መገርሳ በሚሉ ስሞች ልጆቹን መጥራቱን አቁሞ የነበረው ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑ ኦሮሞ ዛሬ ኮራ ብሎ “ሃዊ፣ ቀነኒ፣ ፊራኦል፣ ኦብሰን፣ ሳርቱ” የሚሉ ስሞችን ለልጆቹ እየሰጠ ያለው ኦነግ በቀየሰው መንገድ inspire ስለሆነ ነው።

• ኦነግ “የቁቤ አፋን ኦሮሞ” አባት ነው። አፋን ኦሮሞ በላቲን ፊደል እንዲጻፍ ምርምር አድርገው ውጤቱን ይፋ ያደረጉት ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ እና ኃይሌ ፊዳ ናቸው። እነርሱ ያጠናቀሯቸውን ጥናቶች በማዳበር ለመጀመሪያ ጊዜ በስራ ላይ ያዋለው ግን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ነው። ኦነግ በሽግግሩ ዘመን ከሰራቸው ስራዎች መካከል ትልቁ አፋን ኦሮሞ የትምህርት ቋንቋ ሆኖ የኦሮሞ ልጆች በቋንቋቸው እንዲማሩ ማድረጉ ነው (በዚህ ረገድ የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኢብሳ ጉተማ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል)።

• ኦነግ የዘመናዊው የአፋን ኦሮሞ ስነ ጽሑፍ አባትም ነው። በቁቤ አፋን ኦሮሞ የተጻፉ የግጥም እና የልብ ወለድ መጻሕፍትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳተመው ኦነግ ነው። በቁቤ የሚዘጋጁ ጋዜጦችና መጽሔቶችንም ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳተመው ኦነግ ነው።

• አሁን የስራ ቋንቋ ሆኖ የሚያገለግለውን የተማከለ የአፋን ኦሮሞ ዘይቤንም የፈጠረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ነው። ለቢሮክራሲ ስራ የሚያስፈልጉና በሂደት ለመጥፋት ተቃርበው የነበሩ የኦሮምኛ ቃላትን ከልዩ ልዩ የኦሮሚያ ዞኖች አሰባስቦ በመዝገበ ቃላት በመሰነድ በመላው ዓለም በሚኖሩ ኦሮሞዎች ዘንድ እንዲታወቁ ያደረገው ኦነግ ነው።

• ኦነግ የዘመናዊው የኦሮሞ የታሪክ ጽሑፍ አባትም ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ በመላው የኦሮሚያ ዞኖች ላይ ያተኮረ የታሪክ መጽሐፍ አሳትሞ ያቀረበው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ነው (ከዚያ በፊት ይወጡ የነበሩት የታሪክ መጻሕፍት በአንዱ የኦሮሚያ ዞን፣ ወይንም በአንድ የኦሮሞ ነገድ ላይ ብቻ ያተኮሩ ነበሩ)።

• ለመጀመሪያ ጊዜ የገዳ ስርዓትን አተገባበር በተሟላ ሁኔታ የሚተርክ መጽሐፍ የጻፉት ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ናቸው። የገዳ ስርዓትን በዓለም ዙሪያ በስፋት ያስተዋወቁት ግን በውጭ ሀገራት የነበሩት የኦነግ የውጭ ግንኙነት ቢሮዎች ናቸው።

• ኦነግ ሁሉን አቀፍ የኦሮሞ ጥናት አባትም ነው። በኦሮሞ ህዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ ኢኮኖሚ፣ ቋንቋና የነፃነት ትግል ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበትን ዓለም አቀፍ ኮንፈረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው የኦነግ የውጭ ግንኙነት ቢሮ ነው። በዛሬው ዘመን በዚህ ዘርፍ ተጠቃሽ ሆኖ የወጣው የኦሮሞ ጥናት ማህበር (Oromo Studies Association) የተመሠረተው ኦነግ ሲያዘጋጃቸው በነበሩት ኮንፈረንሶች ላይ ሲገናኙ በነበሩት ምሁራን አማካኝነት ነው።
—–

ኦነግ በነፃነት ትግሉ ዘርፍ ያደረገው አስተዋጽኦ ሲገመገም ደግሞ ከላይ ከሰፈረው በእጅጉ ይበልጣል። ስለዚህ ወደ ዝርዝሩ መግባቱ ለጊዜው አያስፈልገንም። በአጭሩ ግን “ኦሮሞዎች በነገድ፣ በጎሳ፣ በክፍለ ሀገርና በሃይማኖት ሳይለያዩ በኦሮሙማ መንፈስ አንድ ላይ ሆነው በተደራጀ ሁኔታ ለነፃነታቸው እንዲታገሉ የቀሰቀሰ፣ ለትግሉ ያሰማራ እና ያታገለ፣ በዚህም ከኦሮሞ ህዝብ መጠነ ሰፊ ድጋፍ፣ ከበሬታ እና አመኔታ የተሰጠው የመጀመሪያውና ዋነኛው ድርጅት ነው” በማለት ማስቀመጥ ይቻላል። የኦሮሞ ህዝብ የትግል መንፈስ ሳይቀዘቅዝ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ የደረሰው ኦነግ ባቀጣጠለው ጎዳና ላይ በመራመድ ነው።
—-
እነሆ ለብዙ ዓመታት የኦሮሞዎች የነፃነት ቀንዲል ሆኖ ትግሉን ሲያቀጣጥል የኖረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሰላማዊ የትግልን አማራጭን በመከተል በዘንድሮው ዓመት በሚካሄደው የክልል እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ለመሳተፍ ተዘጋጅቷል፡፡ በግንባሩ ስር ተሰልፎ ለነፃነቱ ሲታገል የኖረው የኦሮሞ ህዝብም የግንባሩ መሪዎች በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች በሚያካሄዷቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች በመሳተፍ አጋርነቱን ሊያሳያቸው ይገባል፡፡