ኦነግ በመግለጫው መንግስትን ወቀሰ:-ውብሸት ታዬ

ኦነግ በመግለጫው መንግስትን ወቀሰ: ውብሸት ታዬ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጉለሌ በሚገኘው ጽ/ቤቱ ከደቂቃዎች በፊት በሰጠው መግለጫ በመንግስት በኩል የአስመራው ስምምነት እየተከበረ አይደለም ሲል ወቀሰ።

በዛሬው ዕለትም ከፍተኛ የሆነ የመንግስት ሰራዊት በሰላሌ፣ በባሌ፣ በጉጂና በወለጋ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን ሊቀ መንበሩ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ጠቁመዋል። “ሠራዊታችን ጥቃት አይፈጽምም ፤ ራሱን ግን እንዲከላከል ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።” ሲሉም አክለው ተናግረዋል።
ሊቀመንበሩ ወደኋላ መለስ በማለት በአስመራው ስምምነት ጦርነት ማብቃቱ፣ ሠራዊቱ አገር ቤት ሲገባ ስለሚስተናገድበት አግባብ (1300 ሠራዊት መሆኑን ጠቅሰዋል) እንዲሁም በግል ከአቶ ለማ መገርሳ እና ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ከዚህ በፊት የነበረው ዓይነት የሸፍጥ ፖለቲካ እንዳይኖር(ይህ ከሚሆን ባንመለስ ይሻላል በሚል) አደራ ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ሰላማዊ ሂደቱንና ለውጡን ለማፋጠን የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር ለመሥራት ቢሞክሩም በመንግስት በኩል ከዚህ በፊት የነበረውና የማያዋጣው አካሄድ መስተዋል ጀምሯል፣ የትናንትናው የኦዴፓ የጦርነት የመሰለ አዋጅና የዛሬው የጠ/ሚ/ር ጽ/ቤት መግለጫ ይህን ያሳያል ብለዋል።

አርሲ አርዳይታ ካምፕ ያለው ሠራዊታቸው የተያዘበት አግባብ የተሃድሶ ሳይሆን የእስር አይነት እንደሆነበት መግለጹና የፈጠረውን ተቃውሞ፣ በዛሬው ዕለት ከኦነግ ዋና ጽ/ቤት ምግብ በመመገብ ላይ ያሉት አባላቸው ዶ/ር ገዳና ሌሎች መያዛቸውንና የመሳሰሉትን በቅሬታ አንስተዋል፤ በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቀዋል ።

በወለጋ አከባቢ ችግር መፈጠሩን ተከትሎ መግባባት ለመፍጠር አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ በግላቸው ተንቀሳቅሰው እንደነበር ኦቦ ዳውድ አስታውሰው በመንግሥት በኩል ግን አዎንታዊ እርምጃ መውሰድ አልተፈለገም ብለዋል ። አያይዘውም ኢታማዦር ሹሙ ጄ/ል ሰዓረ መኮንን፣ ጄ/ል ብርሃኑ ጁላ፣ የደህንነት ሃላፊው ጄ/ል አደም መሐመድ እና የኦሮሚያ ም/ል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ጠይባ ሁሴን ባሉበት ያደረግነው ውይይት አልተተገበረም ሲሉ ገልጸዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ እየፈነዱ ስላሉ ፈንጂዎች እጃቸው እንዳለበት ተጠይቀው “እኛ ፈንጂ የለንም ሆኖም ገና 40 ፈንጂዎች እንደሚፈነዱ መረጃዎች አሉን መንግስት አስቸኳይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል” ሲሉ ስጋታቸውን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የ2012ቱ ምርጫ በወቅቱ ካልተካሄደ አሁን ልንገምተው የማንችለው ችግር ሊከሰት ስለሚችል ወቅቱ ሊዛነፍ አይገባም ሲሉ ያሳሰቡ ሲሆን እኛም ለምርጫው በሰላማዊ መንገድ ዝግጅታችንን እያደረግን ነው ብለዋል። ኦነግ ለአብሮነት ስጋት ነው ስለሚባለውም ከተቃዋሚዎች ጋር ጭምር ውይይት ማድረጋቸውንና ለአብሮነት ምንጊዜምአብረው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ሊቀመንበሩ ኦቦ ዳውድ ሲደመድሙ የሰላም ጉዳይ የኦነግና የመንግስት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ነው በሚል ድርጅታቸው በጽኑ እንደሚያምን ገልጸዋል።