እየተፈጠረ ያለው (የኢትዮጵያ ብልፅግና) ፓርቲ : ውሕደት፣ መፍረስ፣ ወይስ አዲስ ፓርቲ መፍጠር?

ውሕደት፣ መፍረስ፣ ወይስ አዲስ ፓርቲ መፍጠር?

1. እየተፈጠረ ያለው (የኢትዮጵያ ብልፅግና) ፓርቲ፣ የተዋሃደ ኢህአዴግ ሳይሆን፣ አዲስ ፓርቲ ነው። እንደ አዲስ ፓርቲነቱ፣ ደጋፊዎቹን አሰባስቦ፣ አባላት መዝግቦ፣ ፕሮግራም ቀርጾ፣ አመራሩን መርጦ፣ የድርጅት አርማ፥ ምልክትና፥ ሥም አውጥቶ፣ ጽሕፈት ቤት ከፍቶ፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ተመዝግቦ ፈቃድ እስኪያገኝ ድረስና በሚመጣው ምርጫ እስኪመረጥ ድረስ፣ እንደ መንግሥት ለመንቀሳቀስ አንዳችም ሕጋዊነት አይኖረውም። ለውጡንም በማስተዳደር፣ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሂደቱን ለማሳለጥ ምንም ሕጋዊም ሆነ ሕዝባዊ ማንዴት አይኖረውም። ‘ተዋህደናል’ ማለት፣ አዲስ ሕጋዊ ህልውና ያለው ሌላ ድርጅት ፈጥረናል ማለት ስለሆነ፣ እስካሁን ድረስ ብቸኛው በሕዝብ ‘የተመረጠ’ ድርጅት የሆነውን ኢህአዴግንም ተክተናል ማለት ነው። ይህ ሲሆን፣ ለውጡን የመምራት ኃላፊነት ያለው ድርጅት ፈርሶ ከለውጡ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውና ምንም ዓይነት ማንዴት የሌለው ሌላ ድርጅት ያለ ሕግ አግባብ ሥልጣን ተቆጣጥሮአል ማለት ነው። ኢህአዴግ ከፈረሰ ደግሞ፣ መንግሥት ማስተዳደርም፣ እራሱ ተለውጦ አገሩን ማሻገርም ስላቃተው፣ የሽግግሩ ሂደት ተስተጓጉሎአል ማለት ነው። በመሆኑም፣ አዲስ የሽግግር ጊዜ መንግሥት መደራደር አስፈላጊ ሊሆን ነው ማለት ነው። በመሆኑም፣ ይህቺ የተዋህደናል ጫወታ የፈርሰናል አንድምታ እንዳላትና አደጋውም ብዙ እንደሆነ ሊታሰብበት ይገባል።

2. አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ በቀድሞው የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውህደት ሲፈጠር፣ የነዚህ ድርጅቶች ዓላማ፥ ራዕይ፥ እና ግብ፣ ርዕዮትና የትግል መስመር፣ የኃይል አሰላለፍ ስሌት፣ ወዘተ ወይ ተጥሎ ወይ ተቀይሮ ይሄም በሕግ አግባብ ተደርጎ ፈርሰዋል ማለት ነው። እንደሚታወቀው፣ እነዚህ የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች በሙሉ የብሔር ድርጅቶች ናቸው።

እንደ ብሔር ድርጅትነታቸው፣ ዓላማና ግባቸው የብሔራቸውን የእኩልነት፣ እራስን የማስተዳደር፣ እና የእራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በመጠቀም ኢትዮጵያን በጋራ ማስተዳደር ነው/ነበር።

ርዕዮታቸውም፣ ከብሔር ጭቆና ሥርዓት ለመላቀቅ፣ የብሔር ሉዓላዊነትን በማስመለስ የተነጠቁትን/የተነፈጉትን የብሔር ሉዓላዊነትና የዜጎቻቸውን ሰብዓዊ ክብር መመለስ፣ እኩልነትንና ማህበራዊ ፍትህን ማጎናፀፍ እንዲቻል የእራስን ዕድል በራስ የመወሰን እንቅስቃሴ (movements for national self-determination) ማካሄድ ነው።

የኃይል አሰላለፍ ስሌታቸውም፣ መሠረታዊው የአገሪቱ የመንግሥት አወቃቀር ችግር የብሔር ተቃርኖዎች መኖራቸውን የተንተራሰ ሲሆን፣ ወገንተኝነታቸውም ለጭቁን ብሔሮች መብት ነው።

ዛሬ፣ ኢሕአዴግ ተዋሃደ ሲባል፣ እኒህ ዓላማዎች፣ ርዕዮቶችና የኃይል አሰላለፍ ስሌቶች ሁሉ ፋይዳቸውን ጨርሰዋል፣ በሌላ ዓላማ፣ ርዕዮትና ስሌት ተተክተዋል ማለት ነው። ይሄም በመሆኑ ፈርሰዋል ማለት ነው።

እስካሁን በተጨባጭ እንደምናየው ደግሞ፣ ድርጅቶቹም አልፈረሱም፣ የብሔሮች ጥያቄዎችም በአብዛኛው አልተመለሱም። በተቃራኒው፣ ለብሔር የመታገልና ከዚህም የሚመነጭ ብሄራዊ መነታረኮችና መፋጠጦች ተበራክተዋል።

3. የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ተዋህደው የብልፅግና ፓርቲ ሆነዋል ማለት፣ የትግል ዓላማቸው፣ ርዕዮታቸው፣ እና የኃይል ስሌታቸው ወይ አላስፈላጊ (obsolete) ሆኗል ወይ ድርጅቶቹ ከድተውት ወገንተኝነታቸውን ከሌላ መደብ/የፖለቲካ መስመር ጋር አሰናስለዋል ማለት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዳቮስ ላይ እንዳሉት፣ እሳቸው የካፒታሊስት ሥርዓት አቀንቃኝ ከሆኑ፣ ይሄ አሁን የተመሰረተው የብልፅግና ፓርቲም (ስሙም እንደሚጠቁመው) ለሃብታም (ካፒታሊስቶች) ወገንተኝነት ያለው ቀኝ ዘመም (market conservative) ፓርቲ ነው ማለት ነው። የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ደግሞ ክፕፍጥረት አንስቶ እስከዛሬ ድረስ ለሃብታም ካፒታሊስቶች የሚታገሉ ድርጅቶች ሳይሆኑ፣ ለጭቁን ብሔሮች ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትህና ብልፅግና የሚታገሉ የማህበራዊ ፍትህ አቀንቃኝ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች ‘ተዋሕደው’ የብልፅግና ፓርቲ ለመመስረት የሚያስችል ምንም የኋላ ታሪክም፣ እርሾ የሚሆን ፕሮግራምም ሆነ ወገንተኝነት የላቸውም። አንዳችም የሚያዋህዱት ዓላማ፣ ሃሳብ፣ ራዕይ፣ አመለካከት ወይም የሚዋዋሃድ ድርጅታዊና የአመራር ቁመና የላቸውም።

4. ኢሕአዴግ ተዋሃደ ለማለት፣ ሁሉም አባልና አጋር ድርጅቶቹ በጥምርነት አገርን በአንድነት ከሚያስተዳድር ድርጅት፣ ወጥነት ወዳለው የተሻለ መቀራረብና መወራረስ ደረጃ ደረሱ ማለት ነው።

በተጨባጭ የሚታየው ግን፣ አባል ድርጅቶቹ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የተራራቁበት ወቅት መሆኑን ነው። መጋጨት፣ በመግለጫ መሰዳደብ፣ በሴራ የመጠላለፍ፣ በሰይፍ መገዳደልና ለመጠፋፋት መዛዛት፣ ወዘተ የሰርክ ተግባር የሆነበት ወቅት የውህደት ጊዜ ሆኖ ሊወሰድ የሚችል አይደለም።

ከአባል ድርጅቶቹ አንዱ (እና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የግንባሩ አስኳልና ዋና አስተባባሪ/አድራጊ ፈጣሪ) የነበረው ሕወኃት በውሁዱ ፓርቲ ውስጥ አለመኖሩም የሚያሳየው መዋሃድን ሳይሆን መፍረስን ነው።

ስለዚህ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህቺን በተዋህደናል ሥም የብሔር ድርጅቶችን የማፍረስ ዓላማ ያዘለች ተንከሲስ ሃሳብ አስቀምጠው፣ “እኔ ኢሕአዴግ የማይመጥነኝ መሪ ስለሆንኩ ሌላ ፓርቲ አስፈልጎኛልና አዲስ (የብልፅግና) ፓርቲ መስርቼአለሁ” ቢሉ ይበልጥ የመታመን እድላቸውን ያሰፋሉ። ለሚቀጥለው ምርጫም በተሻለ ግልፀኝነትና ተአማኒነት ለመዘጋጀት ይችላሉ።ከዚህ ሁሉ የተሻለ አማራጭም አላቸው፦ ለኢሕአዴግ መልቀቂያ አስገብተው፣ ሥልጣናቸውን ለቀው፣ ወደ ኢዜማ መደመር።

የባለአደራ ‘የሽግግር አቀላጣፊ’ መንግሥትና ድርጅት መሪ ሆነው፣ በውህደት ሥም ድርጅቱንና መንግሥቱን ከላይ ሆነው እያፈረሱ፣ በውህደት ሥም ሽግግሩን ከመሸቀብ ቢቆጠቡ ለራሳቸውም፣ ለወዳጆቻቸውም፣ ለመንግሥትም፣ ለአገርም ትልቅ ውለታ ይውላሉ።
ብሩክና ብረህ ሰንበት!
Tsegaye Ararssa