ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ አመራሮችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲለቀቁ አንድ የስዊድን ..

ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ አመራሮችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲለቀቁ አንድ የስዊድን የፓርላማ አባል ጥሪ አቀረቡ

ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ አመራሮችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲለቀቁ አንድ የስዊድን ..

ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ አመራሮችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲለቀቁ አንድ የስዊድን የፓርላማ አባል ጥሪ አቀረቡ
ኢሳት (የካቲት 9: 2009)
በኢትዮጵያ ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ አመራሮችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲለቀቁ አንድ የስዊድን የፓርላማ አባል ጥሪ አቀረቡ።
በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ለሃገሪቱ ፓርላማ ንግግርን ያቀረቡት የፓርላማ አባሉ እንደርስ አስተርበርግ፣ የስዊድን መንግስትና የአለም አቀፍ ማህብረሰብ በኢትዮጵያ በመፈጸም ላይ ይገኛል ላሉት የሰብዊ መብት ጥሰቶች ትኩረትን እንዲሰጡም አሳስበዋል።
በቅርቡ ለእስር የተዳረጉት ዶ/ር መረራ ጉዲናን እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን በዋቢነት ያነሱት የፓርላማ አባሉ አንደርስ በኢትዮጵያ በመፈጸም ላይ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በቂ ትኩረት አለማግኘቱ ስጋት እንዳሳደረባቸው በንግግራቸው አመልክተዋል።

ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በስልጣን ለመቆየት “የከፋፍለህ ግዛ” የፖለቲካ ስርዓትን ዘርግቶ እንደሚገኝ የገለጹት አንደርስ አስተርበርግ የሃገራቸው መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመጠቀም የሰብዓዊ መብት መከበርን አጀንዳው እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በኦሮሚያ፣ አማራ እና ጋምቤላ ክልሎች በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ንጹሃን ሰዎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው ለፓርላማው የተናገሩት አስተርበርግ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ምክንያት ብቻ ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ አክለው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ በአመቱ መጀመሪያ በኦሮሚያ ክልል ለእሬቻ በዓል አከባበር ወቅት በመቶዎች በሚቆጠሩ ንጹሃን ሰዎች ላይ ግድያን የፈጸሙ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ የስዊድን የፓርላማ አባሉ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ ጥሰቶች አለም አቀፉ ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ መንግስት በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ተቋማትን የተለያዩ አዋጅ በማውጣት እንዳይሰሩ ማድረጉን አስተርበርግ በፓርላማ ንግግራቸው ገልጸዋል።
በቅርቡ በብራዚል በተካሂደው የኦሎምፒክ ውድድር ተሳታፊ የነበረው አትሌት ፈይሳ ለሊሳ ሁለት እጆቹን በማጣመር በኢትዮጵያ ያለውን ግድያና አፈና ለአለም ማሳወቁን ያወሱት የፓርላማ አባሉ እርሳቸውም እጃቸውን በማጣመር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ያለውን ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳሳሰበው በመግለጽ ድርጊቱ በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄደበት ጥያቄን አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ግድያዎች በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድባቸው ቢጠይቅም መንግስት ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ ይታወቃል።
ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚይ ክልል ዘልቆ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ700 የሚበልጡ ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውንና በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለእስር መዳረጋቸውን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ሲገልጹ ቆይተዋል።
መንግስት በበኩሉ በድርጊቱ 560 ሰዎች መሞታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ከ20 ሺ የሚበልጡ ደግሞ ለእስር ተዳርገው ግማሽ ያህሉ መለቀቃቸውን በቅርቡ አስታውቋል።

Via Netsanet Beqalu Mannet