ኢዜማ : ብሔሮችን የማይቀበል፣ የወል መብቶቻቸውን የማያከብር ፖለቲካ፣ የአገር አንድነት ማስከበሪያ ፖለቲካ ሳይሆን፣ የጠቅላይ-ተስፋፊነት (imperial) ፖለቲካ ነው!

ኢዜማ : ብሔሮችን የማይቀበል፣ የወል መብቶቻቸውን የማያከብር ፖለቲካ፣ የአገር አንድነት ማስከበሪያ ፖለቲካ ሳይሆን፣ የጠቅላይ-ተስፋፊነት (imperial) ፖለቲካ ነው!

What a brilliant journalist! What an unthinking blabbering on the part of Dr Berhanu Nega! ዘላለም እያጭበረበሩ መኖር አይቻልም። ቁርጣችሁን እወቁ!!!

የሕዝብን ጥያቄ እየካድክ ስለአስተዳደር ፍትህ፣ ስለ ዴሞክራሲ መታገል አትችልም። የሕዝብን መሠረታዊ የፍትህ ጥያቄ በመካድ የምታደርገው ትግል፣ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት ትግል ሳይሆን፣ የጥቂት ልሂቃንን የበላይነትን ለማስቀጠል የሚደረግ መውተፍተፍ ነው።

የብሔሮች ጥያቄ፣ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። የፍትህ ጥያቄ ነው። በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ ደግሞ ቀዳሚው መርሕ (axiomatic principle) ነው። ማደራጃ/ማዋቀሪያ መርሕ ከመሆኑም የተነሳ፣ የመጨረሻው የሕግ ሥርዓቱ መደላድል መሠረት (jural postulate) ነው። ይሄን ጥያቄ ማዕከል ያላደረገ (ወይም የካደ) የፖለቲካ ‘መፍትሄ’፣ ከመነሻው የወደቀ፣ ክሹፍ ፖለቲካ ነው።

በኢትዮጵያ፣ የብሔሮች ጥያቄ ምንጩ፣ ከውጭ የተቀዳ ርዕዮት ሳይሆን፣ የአገሪቱ ታሪክ የፈጠረው የፍትህ መድፋፋትና ወቅታዊው ተጨባጭ ሁኔታ ነው። ርዕዮቱ፣ ችግሩን ለመተንተን፣ ለመግለፅ፣ እና ተነባቢ ለማድረግ (ማለትም፣ articulate ለማድረግ) ቋንቋ ሆኖ አገልግሎ ይሆናል–በተማሪዎች ንቅናቄ ወቅት። ርዕዮቱ ለርዕዮትነቱ ሲባል እንዲተገበር ስለተፈለገ ብቻ፣ በተጨባጭ ህልውና ሳይኖረው፣ በርዕዮቱ አቀንቃኞች መሻት የተፈጠረ የምናብ ጥላ (phantom)ግን አይደለም።

ይልቅስ፣ ከውጭ የተቀዳው ግልብና ማህበራዊ መሠረት የሌለው (የተውሶ) ርዕዮት፣ የግለሰብ መብትን ለማግነን የሚቀነቀነው liberal (ሲብስም libertarian) አስተሳሰብና ዛሬ የከተማ አጭበርባሪዎች አንዴ “የዜግነት”፣ ሌላ ጊዜ “የብልፅግና” የሚሉት ትርጉም አልባ ጫጫታ ነው።

የብሔሮችን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ያደረጉ አስተሳሰቦች፣ ከቀኝም ከግራም፣ ከምዕራብም፣ ከምሥራቅም መንጭተዋል። የራስን ዕድል በራስ መወሰን፣ ለብሔር ጥያቄ መልስ እንዲሆን፣ Woodrow Wilsonም፣ Vladmir Leninም (ከሌሊንም በፊት ሌሎች) ሃሳብ አቅርበዋል። ስታሊን የመጀመርያውም፣ ብቸኛውም፣ የመጨረሻውም ሰው አልነበረም፤ አይደለም።

ዛሬ ዛሬ፣ የነብርሃኑ ጉዳዩን ከስታሊን ጋር ማቆራኘት፣ ጥያቄውን ለመመለስ የተደረገውን ጥረት ለማጣጣል እንዲመቻቸው፣ ስሙ ከጭቆናና አፈና ጋር በፕሮፓጋንዳ እየተያያዘ ከሚነሳ ሰው ጋር በማነካካት እውነተኛ የፍትህ አራማጅ ፖለቲካን ለማጠልሸት ነው። ይህችም ፕሮፓጋንዳ መሆኗ ነው።

ስታሊን ጋ መብቱ በዴሞክራሲ አለመኖር ምክንያት አልተተገበረም ማለት፣ የብሔሮች መብት በሕግ መታወቁ ስህተት ነበር፣ ዛሬም ስህተት ነው፣ ማለት አይደለም። (በነገራችን ላይ ስታሊን፣ የብሔር ጥያቄን “ለቀልድ ነው የፃፍነው” አላለም። ይሄ ተራ ውሸት ነው።)

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ስላልነበረ፣ ፌደራሊዝሙ ሙሉ በሙሉ አልተተገበረም ማለት፣ የፌደራል አደረጃጀቱ በመርህ ደረጃ ትክክል አይደለም ማለት አይደለም። ዴሞክራሲ ስላልነበረ፣ የብሔሮች መብት አልተከበረም ማለት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመፍጠር መብቶችን የማስከበር ግዴታ ይጥልብናል እንጂ፣ ዴሞክራሲ ሲመጣ መብቶችን የመሰረዝ ሁኔታ ያስከትላል ማለት አይደለም።

የብሔሮችን ጥያቄ፣ ከቀኝ እና ግራ ርዕዮቶች ውጪ የዓለምአቀፍ ሕግ፣ በ ዘመነ League of Nationsም ሆነ በዘመነ United Nations በተለያየ መልክና ደረጃ እውቅና ሰጥቶት መልስ የሰጠው ጉዳይ ነበር። League of Nations የአናሳ ቡድኖችን መብት በሚያስከብር ሥርዓትና አግባብ፣ United Nationsም የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብትን በUN Charter (1945)፣ በUDHR (1948)፣ በICCPR እና በICESCR (1966/1976)፣ በ1960 እና በ1970 በወጡ የጸረ-ቅኝ ግዛት ዓለምአቀፍ አዋጆች (Declarations) በማውጣት comprehensive ምላሽ ሰጥቶአል።

ይሄ ሁሉ እየታወቀ፣ የወል መብቶችን በሕግ እውቅና መስጠት በኢትዮጵያ ብቻ የተደረገ (ይሄም በአገር ላይ የተሴረ በደል እንደሆነ አድርጎ) ፕሮፓጋንዳ መስራት፣ ያው የሃበሻ ሸፍጥ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ያለው አነጋገር አይደለም። ሸፍጥና ፋሽናችሁ ሲያልፍ ችግሩ እዚያው አግጦ ይጠብቀናልና።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፌደራሊዝም፣ በቋንቋ ላይ ብቻ ተመርኩዞ የተመሠረተ ሥርዓት አይደለም። ክልሎች የተፈጠሩበት መስፈርትም አንድ፣ ያውም ቋንቋ፣ ብቻ አይደለም። በግልፅ የተደነገገው ሕግ የሚለው፣ መስፈርቶቹ፣ ሀ) አሰፋፈር፣ለ)የሕዝብ ፈቃድ፣ መ)ቋንቋ፣ እና ሠ)ማንነት ናቸው። አሰፋፈር፣ በቦታ (in place and space) ነው የሚፈጸመው። ስለ ጂኦግራፊ ስናወራ ደሞ፣ የምናወራው ያው ስለ ቦታ (ስለ place and space) ነው። “መልክዓምድራዊ መስፈርት እናካትት” የሚሉት የኛ ጉዶች፣ ከዚህ በላይ ምን ዓይነት ጂኦግራፊያዊ መስፈርት ነበር የሚፈልጉት? “የሕዝብ አሰፋፈር” የሚለው መስፈርት ከመልክዓምድራዊ ተጠየቅ ውጪ እንዳልሆነ እያወቁ፣ መልክዓምድር (ወይም ጂኦግራፊ) ማለት ሌላ፣ ልዩ፣ በሕገመንግስቱ ውስጥ የታጣ መስፈርት እንደሆነ አስመስለው ማውራት ተራ ማምታታት ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ እኩል ልዕልና ያላቸው፣ እኩል ክሱት የሆነ ልዕልና የተጎናጸፉ (ማለትም co-equal and co-eval sovereignty ያላቸው) አሃዶች ናቸው። እነዚህ አሃዶች፣ መብታቸውን መጠቀማቸው ግጭት አይፈጥርም። ግጭት የሚፈጥረው፣ (በቅርቡ በሲዳማ እና በወላይታ ከክልልነት ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ እንደታየው)፣ ሕግን ጥሰህ፣ መብቱን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አለመመለስህ ነው፤ ሕገመንግሥታዊ መብትን ስለጠየቁ ብቻ (አብይ እንዳደረገው) አፈና መፈጸምህ ነው።

የመገንጠል መብት፣ እንደ ማንኛውም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ሁሉ፣ የሁሉም ብሔሮች መብት ነው። ትልቅነት፣ ትንሽነት አይወስነውም። የሚጠቅመውንና የሚሻለውን የሚወስነው፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ፣ ሕዝቡ ብቻ ነው። ሕዝቡ የሚወስነው ውሳኔ፣ መገንጠል የመሆኑን ያህል፣ ከሌሎች ጋር አብሮ ለመኖር ወይም ለመዋሃድም ዕድል አለው። “በሕጉ መሠረት መብትህን ስትወስን ትገነጠላለህ፣ መገንጠልህ አገር ያፈርሳል፣ ይሄን ደሞ እኛ (ምርጦቹ የኢትዮጵያ) ልሂቃን ስለማንቀበል እንወጋሃለን፣ ይሄም እርስ በርስ ጦርነት ይፈጥራል” ማለት፣ ተራ ግን የተለመደ፣ ሃፍረተ-ቢስ የሃበሻ ልሂቃን እብሪት ነው። ኢዴሞክራሲያዊነት ነው። ሕዝብን መናቅ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች ኢትዮጵያን ከዶክተር ብርሃኑና ከመንጋው የበለጠ እንጂ ያነሰ አይወዷትም። ኢትዮጵያ ታስፈልገኛለች ካሉ (ደሞም ይላሉ ብዬ አስባለሁ–ለራሳቸው ሲሉ!) እነሱ እራሳቸው ይጠብቋታል እንጂ፣ “ብትወድም ባትወድም፣ እሷን ትተህ መሄድ መብት መሆን የለበትም፣ ከሆነም መከበር የለበትም።” ማለት የተስፋፊ-ጠቅላይነት መጎምዠት (imperial desire) ነው።

ይሄ ነው የነኢዜማ (ወይም የእነ ‘አብራኑ’) አመለካከት። ይሄ ነው ኢትዮጵያህን የሚያፈርሳት። እብሪትህ እና ሽፍጥህ፣ ሴራህ፣ ነው የሚያራኩታት፣ የሚበትናት።

ለማንኛውም ዕዳችሁን ቻሉ። ሕዝቡን ግን ለቀቅ አድርጉት። አትመፃደቁበት።

“የሰፋሪና የደላላ ጥምር መንግሥት ነው የሕዝብን ትግል የጠለፈው” አለ ኮሎኔል ገመቹ አያና ሰሞኑን። ትክክል ነው። አገሪቷንም የሚያፈርሳት፣ ይሄ የሰፋሪና የደላላ ሽርክና (በታሪክም፣ የነፍጠኛና የአካባቢ ባላባት ትብብር) የሚወልደው ጸረ-ሕዝብነት፣ ጸረ-ዴሞክራሲያዊነት፣ እና ሥርዓተ-አልበኝነት ነው።
Tsegaye Ararssa


ከ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርት (ኢዜማ) መሪ ጋር የተደረገ ቆይታ