ኢትዮጵያ፤ ይነጋላት ይሆን?ከጊንጪ እስከ አርሲ፤ ከኮፈሌ እስከ ባሌ፤ ከአምቦ እስከ ጎንደር፤ ከባሕርዳር እስከ ጉደር፤

ኢትዮጵያ፤ ይነጋላት ይሆን? ከጊንጪ እስከ አርሲ፤ ከኮፈሌ እስከ ባሌ፤ ከአምቦ  እስከ ጎንደር፤ ከባሕርዳር እስከ ጉደር፤ ከቢሾፍቱ እስከ ዳሮለቡ፤ከሐረርጌ እስከ ቢሾፍቱ፤ ከተማ-መንደሮች ስንጠራ፤ ሟች ቁስለኛ ሥንቆጥር፤ የጠፋ ሐብት ንብረት፤የተሰደደ ሰዉ ሥናሰላ ሁለት ዓመት አለፈን።ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ የግድያ ግጭቱ ማዕከላት ወልዲያ፤ቆቦ፤ መርሳ እና ሲሪንቃ ናቸዉ

(DW) —አዲስ አበባ ለእንግዶችዋ ክብር ሆቴል ጎዳናዎችዋን አፅድታ፤ አደባባይ-አዳራሾችዋን በባንዲራ አሸብርቃ የአፍሪቃ መሪዎችን ተቀብላ፤ ሸኘች።ወልዲያ ግን ሙታኖችዋን ቀብራ፤ ቁስለኞችዋን አክማ፤ አጎዛዋን ሳታጥፍ ለሌላ ተቃዉሞ-ግጭት ትንተከተካለች።የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዳቮስ-ስዊዘርላንድ ላይ ሥለ ዓለም ፀጥታ፤ ሥለ ማሐበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲመክሩ እንደ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሚያዙት የፀጥታ ኃይል ሰሜን ወሎ ላይ ከድጋይ ወርሪዎች ጋር «ዉጊያ» ገጥሞ ነበር።በዉጤቱ ወልዲያ፤ ቆቦ፤ መርሳ፤ሲሪንቃ አስከሬን ይቆጥሩ ገቡ።ነዳዱ።በጢስ ጠለስ ታፈኑም።ከወራት በፊት አምቦ፤ጨለንቆ፤ ዳሮለቡ ነበሩ።አሁን ሰሜን ወሎ።ከ2008 ጀምሮ ብዙዎች ብዙ ጊዜ ጠይቀዋል። «መፍትሔ አለዉ ይሆን?»

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርም ደሳለኝ፤ ከዳቮስ መልስ።አርብ ጥር 18።  አርብ ቆቦ።የከተማዋ ነዋሪዎች።    ቅዳሜ እና እሁድ።መርሳ።

ባለፈዉ ሳምንት ወልዲያ ላይ በተጀመረዉ ተቃዉሞ እና ግጭት የተገደሉት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር አይታወቅም።የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ግን በአራቱ ከተሞች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከሰላሳ ይበልጣል።የቆሰለ እና የታሰረዉን ሰዉ ብዛት፤ የጠፋዉን ሐብት ንብረት መጠን እስካሁን በዉል የቆጠረዉ የለም።ፍጥጫ፤ እስራት፤ ሥጋት መሸማቀቁ ግን ዛሬም ሰሜን ወሎ ላይ እንዳረበበ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዳቮስ ድረስ ተጉዘዉ የመከሩለትን ሠላም እና ፀጥታ ለሕዝባቸዉ ነፍገዉ ለማን፤ ለምንስ ሊያረጉት ይሆን?

ከሕዳር 2008 ጀምሮ በኦሮሚያ፤ በአማራ እና በከፊል ደቡብ ኢትዮጵያ የተጀመረዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ ለማቀዝቀዝ የኢትዮጵያ መንግሥት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመደንገድ-«ጥልቅ ተሐድሶ» እስካለዉ እርምጃ ወስዷል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶችን በየጦር ሠፈሩ አስሮ ፈትቷል።ከካቢኔ  ሹም ሽር፤ እስረኞች እስከ መፍታት ደርሷል።ተቃዉሞ፤ ግጭት ግድያዉ ግን ተዛመተ እንጂ አልሰከነም።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ አረጋዊ እንደሚሉት  የእስካሁኑ እርምጃ ዉጤት ያላመጣዉ የገዢዉ ፓርቲ (የኢሕአዴግ) መሪዎች ትክክለኛ መፍትሔ ለመስጠት ባለመዘጋጀታቸዉ ነዉ።

በወሊሶ ዩኒቨርስቲ የአምቦ ኮሌጅ መምሕርና ብሎገር ስዩም ተሸመ እንደሚሉት ደግሞ ኢሕአዴግ ለሕዝቡ ጥያቄ ተገቢ መልስ መስጠት አይችልም።አልቻለምም።

ሥብስብ ለሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ የተባለዉ ድርጅት መሪ አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም በበኩላቸዉ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄ የሰጠዉ መልስ የኃይል እርምጃ ነዉ ባይ ናቸዉ።                ከጊንጪ እስከ አርሲ፤ ከኮፈሌ እስከ ባሌ፤ ከአምቦ  እስከ ጎንደር፤ ከባሕርዳር እስከ ጉደር፤ ከቢሾፍቱ እስከ ዳሮለቡ፤ ከምዕራብ ሐረርጌ እስከ ቢሾፍቱ፤ ከተማ-መንደሮች ስንጠራ፤ ሟች ቁስለኛ ሥንቆጥር፤ የጠፋ ሐብት ንብረት-የተሰደደ ሰዉ ሥናሰላ ሁለት ዓመት አለፈን።ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ የግድያ ግጭቱ ማዕከላት ወልዲያ፤ቆቦ፤ መርሳ እና ሲሪንቃ ናቸዉ ።

እስካሁን አንድም ገዳይ፤ ሐብት ንብረት አጥፊ ለፍርድ መቅረቡን  መንግሥት አላሳወቀም።ለአንድም ጉዳተኛ ካሳ መክፈል አይደለም ለመክፈል ሥለመታሰቡም አልሰማንም።አንዱም የመንግስት እርምጃ ሕዝብን

አላረካም።የዩኒቨርስቲ መምሕርና ብሎገር ስዩም ተሸመ እንደሚሉት መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄ ሁነኛ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ በሕዝብ ላይ ከፖሊስ አልፎ ጦር ሠራዊት ማዝመትን ነዉ-የመረጠዉ።

የሕግ ባለሙያ ሙሉጌታ አረጋዊ በበኩላቸዉ  ሕዝብ በመንግስት ላይ ያለዉ እምነት በጅጉ መንምኗን ባይናቸዉ።የመንግሥት ባለሥልጣናትም ከሥልጣናቸዉ ባለፍ ሌላ ነገር የሚያስቡ አይመስሉም።

ኢትዮጵያ ከከፋ ደም መፋሰስ እንዳትገባ የማይፈልግ፤ የማፀልይ የማይመኝ ኢትዮጵያዊ በርግጥ የለም።የሚፈራዉን ለማስቀረት ግንባር ቀደሙ መፍትሔ ሰጪ መንግሥት መሆን እንደሚገባዉም ብዙዎች ያምናሉ።አቶ ሙሉጌታ ግን መንግስት መፍትሔ ለመስጠት መጀመሪያ እንደመንግስት ባንድነት መቆም አለበት ይላሉ።ጊዜም የለም።

የመብት ተሟጋች ያሬድ ኃይለማርያም በበኩላቸዉ መንግስት መፍትሔ ለመስጠት አቅሙም ፍላጎትም የለዉም ባይ ናቸዉ። አቶ ስዩምም በአቶ ያሬድ ሐሳብ ይስማማሉ።

ጊዜ በርግጥ የለም።ምናልባትም መሽቶ ይሆን ይሆናልም።ግን አሁንም አልጨለመም።ይነጋ ይሆን?  ምን ያሕል ጊዜ ይፈጃል?

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ