“ኢትዮጵያ ውስጥ የስኳር እጥረት የለም “ለኬንያ 44 ሺህ ኩንታል ስኳር መላኩ በብዙዎች..

“ኢትዮጵያ ውስጥ የስኳር እጥረት የለም ” ለኬንያ 44 ሺህ ኩንታል ስኳር መላኩ በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል።

ስኳር ለመግዛት የተሰለፉ ሰዎች

(bbcAmharic) –ሰሞኑን የንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሁሉም የከተማና የክልል ንግድ ቢሮዎች ስኳር በኮታ እያደሉ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግስት ለኬንያ 44 ሺህ ኩንታል ስኳር መላኩ በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል።

በሃገሪቷ በአብዛኛው አካባቢዎች ስኳር ለማግኘት ብዙ ሸማቾች ይንገላታሉ።

በዓመታት ውስጥም የስኳር ዋጋ መናርና በቀላሉ አለመገኘት ለብዙዎች ፈተና ሆኗል።

ቢቢሲ ያነጋገራት ቤቴል ቡና በማፍላትና በመሸጥ የምትተዳደር ሲሆን በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ ስኳር በማጣቷ የንግድ ቦታዋን ለመዝጋት እንደተገደደች ትናገራለች።

ለዓመታት ከንግድ ሚኒስቴር በተተመነው ሂሳብ መሰረት ቀበሌዎች ስኳር የማከፋፈሉን ሥራ ወስደው ቆይተዋል።

ቤቴልም ይህንን መሰረት በማድረግ ጉዞዋን ወደ ቀበሌ ብታደርግም አሉታዊ መልስ እንዳገኘች ትናገራለች።

ከቀበሌ ውጪ በአንዳንድ ሱቆች ስኳር ለመግዛት ብትሄድም የአንድ ኪሎ ዋጋ ከ 28- 30 ብር ይደርሳል።

ቤቴል ብቻ ሳትሆን ብዙዎች ንዴታቸውንና መሰላቸታቸውን በተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገጾች እየተናገሩ ነው።

በተለይም የሃገር ውስጥ የስኳር ፍላጎት ባለተሟላባት ሁኔታ ወደ ውጭ መላኩ ለብዙዎች ጥያቄ አጭሯል።

በግንቦት ወር በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የኬንያ መንግስት 100 ሺህ ኩንታል ስኳር ለመግዛ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት 44ሺህ ኩንታል መላኩን የስኳር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉህም ገልጸዋል።

“ሃገሪቱ ውስጥ የስኳር እጥረት የለም ” የሚሉት አቶ ጋሻው ከንግድ ሚኒስቴር በሚቀርብለት ኮታ መሰረት ኮርፖሽኑ 569 ሺህ ኩንታል ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ ይናገራሉ።

ማከፋፈሉ ደግሞ በሸማች ማሀበራት፣ በህብረት ሥራ ማህበራት፣ በኢትፍሩትና በቀድሞው ጅንአድ አማካኝነት ይካሄዳል።

ለዓመታት ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ስኳር ከመላክ ታቅባ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ልካለች።

አቶ ጋሻው እንደሚሉት በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ የስኳር ፋብሪካዎች 3.5 ሚሊዮን ኩንታል የሚያመርቱ ሲሆን 2 ሚሊዮን ኩንታል ደግሞ ከተለያዩ ሃገሮች ይገባል።

በሃገሪቱ ውስጥ ያለው የስኳር ፍለጎት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጋሻው ይህ ፍላጎትም እየጨመረ እንደሆነ አክለው ይገልጻሉ።

“በዓለም ገበያ መርህ መሰረት ይህ የተለመደ አሰራር ነው፤ ገበያው ጥሩ ሲሆን ወደ ውጭ ሃገራት መላክ እጥረት ሲያጋጥም ደግሞ ከሌሎች ሀገራት ማስገባት በብዙ ሃገራት የሚሰራበት ነው” ይላሉ።

አቶ ጋሻው የምርት እጥረት የለም ቢሉም በሃገሪቷ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን እጥረትም ጠንቅቀው ያውቁታል።

ኢትዮጵያ ስኳር ለዜጎቿ ሳይዳረስ ለኬንያ መሸጥ ጀምራለች

የስኳር ኮርፖሬሽን የአቅርቦት ሥራ እንደማያከናውን የሚናገሩት አቶ ጋሻው፤ ለተጠቃሚው በሚደርስበት የገበያ ስርጭት በኩል ችግሮች እንደሚታዩ ይገልፃሉ።

“በህገውጥ መንገድ ስኳር ወደ ሱዳንና ወደ ሌሎች ሃገራት ይላካል፤ ነጋዴዎችም ትርፍ ፍለጋ ያለአአግባብ በማከማቸት የስኳር እጥረት እንዲያጋጥም አድርገዋል” ይላሉ።

በሃገሪቱ ውስጥ ስድስት የስኳር ፋብሪካዎች ሲኖሩ በቀጣዮቹ ዓመታትም ስምንት የስኳር ፋብሪካዎች እንደሚከፈቱና እያደገ የመጣውንም የህዝቡን የስኳር ፍላጎት ሊያሟላ እንደሚችል አቶ ጋሻው ገልጸዋል።

መንግሥት የምርት እጥረት የለም በሚልበት ሁኔታ ገበያው ላይ እጥረት ይታያል። ታዲያ የስኳር እጥረት ለዓመታት እየተንከባለለ የመጣ ጥያቄ ሆኖ እያለ፤ የገበያው ስርጭት ላይ ችግር መኖሩ ከታወቀ መፍትሔ ለማግኘት እንዴት አልተቻለም የሚል ጥያቄ ያሰነሳል።

የኢኮኖሚ ባለሙያውና የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም የስኳር ኢንደስትሪው በአጠቃላይ ለዘመናት በቆዩ ፋብሪካዎች የሚሰራ በምርታማነት ረገድ መሻሻል ያልነበሩት እንደሆነ ይገልጻሉ።

ከ2000 ዓ.ም በኋላ በተያዘው እቅድ መሰረት ቀዳሚ ለሚባሉት ፋብሪካዎች የማሻሻያ፣ የማስፋፊያና የማሽን አደረጃጀት ለውጥ ማድረግ እንደተጀመረ አቶ ጌታቸው ይናገራሉ።

እንደዚያም ሆኖ ሃገሪቷ ወደ ውጭ ከምትልከውና ከሌሎች ሃገራት ከምታስገባው ጋር ሲወዳደር የምታስገባው ይበልጣል።

ይህንንም ሁኔታ ለመቀየር መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ይናገራሉ።

“መንግስት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚያፈሰው በተወሰነ መልኩ ወደ ውጪ እንዲላክና በሃገሪቱ ውስጥ በተወሰነ መልኩ መደጎም እንዲችል አላማው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለን የኢንደስትሪ ዘርፍ ነው” ይላሉ አቶ ጌታቸው።

በሃገሪቱ በውስጥ ያለው ፍላጎት ሳይሟላ እንዴት ስኳር ወደ ውጭ ትልካለች ለሚለው ጥያቄም አቶ ጌታቸው ሲመልሱ “የአንድ ሃገር ምርትን ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት ወይም ወደ ውጭ ሃገር መላክ የሚታየው ከዓለም የገበያ አንጻርና ለሃገሪቷ ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ ነው” በማለት የሌሎችን ሃገራት ሁኔታም “ምርቶቻቸውን ወደውጭ የሚልኩት ሞልቶ ስለተረፋቸው አይደለም” በማለት ይናገራሉ።

እንደምሳሌም የሚጠቅሱት ኢትዮጵያ ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል የምትሸጠው ከጂኦ ፖሊቲካል ጥቅሙ በተጨማሪ የዋጋ ልዩነት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ስለሚያመጣ ነው።

ይሄም ሆኖ ግን እንደ አቶ ጌታቸው አባባል፤ እንዲህ ህብረተሰቡ በቀጥታ የሚጠቀምባቸውን ምርቶች ሃገሪቷ ወደ ውጭ ሃገር እየላከች ህብረተሰቡ ግን ያን ምርት ለማግኘት የሚከፍለው ዋጋ እጅግ ብዙ ከሆነ፤ ከገቢ አንፃር የሚገኘውን ጥቅም ትርጉም አልባ ያደርገዋል።

“ኢትዮጵያ ስኳር ወደ ውጭ ላከች ሲባል ህብረተሰቡ ስኳር ለመግዛት የሚከፍለውን ዋጋ፣ ረዥም ሰልፍና እንግልቱ ነው የሚታየው” ይላሉ።

በአንዳንድ አካባቢዎች የስኳር ዋጋ 40 ብርና ከዚያም በላይ የሚሸጥበትና ከፍተኛ እጥረት የሚያጋጥምበት ሁኔታ እንዳለ የሚገልጹት አቶ ጌታቸው፤ ይህንን ሁኔታ ስኳር ወደ ውጭ ከመላኩ በፊት ሊፈተሽና የፖሊሲ አቅጣጫ ሊሰጠው ይገባል ይላሉ።

“ባለፉት አምስት ዓመታት የስኳር ምርት ብቻ ሳይሆን የገበያ ሰንሰለቱ እንዲሁም አስተዳደር ዝብርቅርቅ ያለ ነው። በዚህም ለረጅም ጊዜ መፍትሄ ሳይገኝ በመቆየቱ ተጠቃሚው እየተጎዳ ነው። በዚህ ያልተረጋጋ ገበያ ላይ ደግሞ ወደ ውጪ የመለኩን ጉዳይ ምክንያታዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው።” በማለት አቶ ጌታቸው ይገልጻሉ።