(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 29-2010) የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት የጠራውን ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በአንድ ቀን ማጠናቀቁ ተሰማ።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ: (ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 29/2010) የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት የጠራውን ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በአንድ ቀን ማጠናቀቁ ተሰማ።

ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚወዛገቡባትን ባድመን በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ መሰረት ያለ ቅድመ ሁኔታ ለኤርትራ ለመስጠት የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ አሳልፏል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ግዙፍ የሀገሪቱ ተቋማትን ከውጭና ከሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ጋር በሽርክና ለመያዝ ወስኗል።

ውሳኔዎቹም በኢትዮጵያውያን ዘንድ አብይ መወያያ ሆነው ወጥተዋል። የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማክሰኞ በጀመረውና በዕለቱ ባጠናቀቀው ስብሰባ በመንግስት ይዞታ ስር በግንባታም ሆነ በስራ ላይ የሚገኙ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል ለሃገር ውስጥና ለውጭ ሃገር ባለሃብቶች እንዲተላለፉ ወስኗል።

በከፊልና ሙሉ በሙሉ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፉ ውሳኔ የተላለፈባቸው የባቡር፣የስኳር ልማት ኢንደስትሪ ፓርክ፣የሆቴልና የልዩ ልዩ ማኑፋክቸሪንግ ተቋማት ናቸው።

ከግማሽ በላይ በመንግስት ይዞታ ስር ሆኖ ሌሎች የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉበት ውሳኔ የተላለፈባቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ኢትዮ-ቴሌኮም፣የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች እንዲሁም የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ድርጅት ናቸው።

እነዚህ የሀገሪቱን ኩባንያዎች በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደ ሃገር ውስጥና ወደ ውጭ ባለሃብቶች ማሸጋገር የስራ እድል ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስራ አስፈጻሚው ስብሰባ በኋላ በሙስና መከላከል ዙሪያ በተጠራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት እነዚህ ኩባንያዎች በሙሉና በከፊል ወደ ግል ሲዛወሩ ከፍተኛ የሌብነት የሙስና ድርጊቶች ሊፈጸሙ ስለሚችሉ መገናኛ ብዙሃንና የሚመለከታቸው ወገኖች ከፍተኛ ክትትል በማድረግ እንዲያጋልጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ትላንት ባካሄደውና በእለቱ ባጠናቀቀው ስብሰባ ከግንቦት ወር 1990 ጀምሮ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የቆየውን የድንበር ውዝግብ የሚቋጭ ውሳኔም አሳልፏል።

በሚያዚያ ወር 1994 በኔዘርላድ ዘሔግ የተሰየመው የድንበር ኮሚሽን ያሳለፈውን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበል የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ትላንት በመወሰኑ ባድመ ለኤርትራ የሚሰጥ ይሆናል።

ሚያዚያ 28/1990 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የፈነዳው ጦርነት ለሁለት አመታት ከቀጠለ በኋላ አልጀርስ ላይ በተደረሰ የሰላም ስምምነት የተኩስ አቁም መደረጉ ይታወሳል።

በታህሳስ 1993 አልጀርስ ላይ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ሁለቱ ወገኖች የድንበር ውዝግቡን በፍርድ ለመቋጨት ተስማሙ።

ሁለቱ ወገኖች በጋራ ያቋቋሙትና 5 አባላት ያሉት የድንበር ኮሚሽን የሚወስነውን ውሳኔ ያለይግባኝ ለመቀበል ሁለቱም በመስማማታቸው ኮሚሽኑ የግራ ቀኙን ማስረጃ ሲመረምር ቆይቶ ሚያዚያ 5/1994 ውሳኔ አሳልፏል።

ወዲያውንም የኢትዮጵያ መንግስት ባድመ ለእኛ ተወሰነ ሲል መግለጫ ሰጠ። በማግስቱም በመስቀል አደባባይ የደስታ ሰልፍ ተደረገ፣የድንበር ኮሚሽኑም ተመሰገነ።

ሆኖም የኮሚሽኑ ውሳኔ ግን ባድመን ለኤርትራ የወሰነ መሆኑ ሲታወቅ የኢትዮጵያ መንግስት ባድመን ለመስጠት ቅድመ ሁኔታ አቀረበ።

ይህም የቀደመ ግንኙነታችን ይቀጥል ወይንም ይታደስ የሚል ነበር። ኤርትራ መጀመሪያ ውሳኔው ይከበር በማለቷ ጉዳዩ ሳይቋጭ ቀጠለ።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ትላንት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውሳኔውን እቀበላለሁ በማለቱ ጉዳዩ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ጉዳዩ በኢትዮጵያውያንናበሕወሃት ደጋፊዎች ዘንድ አብይ መወያያ ሆኖ ወቷል።

Via: ESAT