ኢሕአዲግን በማንበርከክ በኢትዮጵያ የታየዉ የፖለቲካ  ለዉጥ አመራር በብልጣብልጥ

ኢሕአዲግን በማንበርከክ በኢትዮጵያ የታየዉ የፖለቲካ  ለዉጥ አመራር በብልጣብልጥ የኢሕአዲግ ርዝራዦች ተነጠቀ

By: Deressa Ebba Geneti

ላለፉት 26 ዓመታት በተለይ በኦሮሞ ሕዝብና በተቀሩትም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ሲደረግ የነበረዉ ትግል የኢሕአዲግን አምባገነናዊ ሥርአት ለመገርሰስና በምትኩ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት ነበር

ነገር ግን ብዙ ጊዜ በአንዳንድ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎችና አንዳንድ አክቲቪስቶችም ጭምር፣ በሕዝቦች ትግልና በተለይም በኦሮሞ ቄሮዎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተደረሰበት ለዉጥ ከኢሕአዲግ ዉስጥ የተገኙ የተወሰኑ የሕዝቡን ትግል የተቀላቀሉ ኃይሎች ግን ደግሞ እንደ ፓርቲ ቀደም ሲል ስልጣን ላይ የነበረዉን ገዥ ፓርቲ እንዳለ ይዘዉ ለዉጡን እንዲመሩ አደራ ተሰጥቷቸዋል ሲባል ይሰማል።

ለመሆኑ ሕዝቡና በተለይም ቄሮዎች ናቸዉ ምሩን ብለዉ የወከሏቸዉና አደራ የሰጧቸዉ ወይስ  እነኚህ ከኢሕአዲግ ዉስጥ በ11ኛዉ ሰዓት ላይ ብቅ ያሉ ኃይሎች ናቸዉ ለዉጡን እኛዉ እንመራለን ብለዉ ሥልጣን ላይ የተቆናጠጡት፤ ይኸ ጉዳይ መምታታት የለበትም፣ ትክክለኛ ገጽታዉ መታወቅ አለበት። ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚባለዉ ሁሉ፣ የአንዳንድ ከሁኔታዉ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች አፈጮሌነትና ግልብያ ብቻ ለለዉጡ መሳካት ዋስትና አይሆንም።

ዛሬ እያየን ያለነዉ የተፍረከረከና በዉስጣቸዉ በእርስ በእርስ የሥልጣን ሽኩቻ ተተብትበዉ ጦርነት ቀረሽ ደረጃ ላይ ያለ ያረጀ ያፈጀ የኢሕአዲግ  ፓርቲ በምን መመዘኛ ነዉ ሕዝባዊዉን ለዉጥ መምራት የሚችለዉ፣ ምንስ ቢደረግ ነዉ በትግሉ ላይ የአንበሳ ድርሻ የነበራቸዉ ወገኖችና ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉት ወደ ዳር ተገፍተዉ ታዛቢ መሆን የቻሉት። ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ለገዥዉ ቡድን የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቀናጁ የመንግስት ዝግጅቶችና ግብዣዎች ላይ ሲታዩ እንጂ በነጻነት በለዉጡ ሁኔታ ላይ በይፋ ሲመክሩ አይታዩም።

በኢትዮጵያ በተለይ ላለፉት 50 ዓመታት ያለማቋረጥ ሕዝባዊ ትግሎች ሲካሄዱ እንደነበርና ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት እንደተከፈለበትም ግልፅ ነዉ። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ከታዩት ሁኔታዎች ሕዝባዊዉ ትግል ጨቋኝ ሥርአቶችን ለማፍረስ ቢችልም በመጨረሻ ላይ በተደራጁ ጥቂት ኃይሎች እየተቀማ የትግሉ ዓላማ የነበረዉን ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል የሽግግር መንግስት ፈጥሮ ለመምራት አልታደለም። ይኸም ሊሆን የቻለበት ዋናኛዉ ምክንያት የሕዝቡ ትግል በተደራጀና በተቀናጀ ኃይል መመራት ባለመቻሉ ነዉ። በአለማችን ላይ በትጥቅ ትግል ሥልት የተጠቀሙ ኃይሎች የትግል ዉጤት እንከን አልነበረዉም ባይባልም፣ ሰላማዊ ትግል( Non-violence struggle) ተብሎ የሚታወቀዉን የትግል ሥልት የተከተሉትን አብዛኞቹን ያጋጠመዉ እንቅፋትም ይኸዉ ከላይ የተገለጸዉ ሁኔታ ነዉ። በግብፅ፣ በቱኒዝያ፣ በሊቢያ፣ በታይላንድ፣ በቬኔዙዌላና በመሳሰሉት አገሮች የተደረጉት ሕዝባዊ መነሳሳቶች ያጋጠሟቸዉ መሰናክሎች ዋነኛዉ ይኸዉ ሁኔታ ነበር ማለት ይቻላል፤ አሁን በቅርብም የሱዳን ሕዝባዊ ትግል የአምባገነኑ ሥርአት ቁንጮ የነበረዉን ኦመር አልበሺርን ቢያንበረክከዉም ወታደራዊዉ ጁንታ ሥልጣን ላይ ተፈናጦ ለዉጡን እመራለሁ በማለቱ ሕዝቡ እምቢ አሻፈረኝ ብሎ ደም እያፋሰሰ ያለ ከፍተኛ ፍጥጫ ላይ ናቸዉ።

በዚህ ሁኔታ ላይ ታዲያ ላለፉት 26 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝቦች በጦር ኃይል ብቻ ረግጦ በመግዛትና ለብዙ ዜጎች ደም መፍሰስ ምክንያት በሆነዉ የኢሕአዲግ ርዝራዦች አመራር ብቻ በሁሉም ወገኖች ተስፋ የተጣለበት ለዉጥ ሊሰምር ይችላል ብሎ መጠበቅ ከንቱና አደገኛም ነዉ፤ ከአንድ ዓመት የለዉጡ ጉዞ በኋላም እየታየ ያለዉ ሁኔታም ይኸዉ ነዉ።

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ትልቅና  የብዙ ብሔር-ብሔረሰቦች መናሃሪያ የሆነች አገር፤ እንደዚሁም ለረዥም ዓመታት አብዛኞቹን ብሔር-ብሔረሰቦች ያገለለ ጨቋኝና አምባገነን የማዕከላዊ መንግስት  ታሪክ ያላት አገር፣ ለረጅም አመታት ሲደረግ በቆየዉ የሕዝቦች ትግል የተሳተፉት ወገኖች ሁሉ ተሳትፎ ባላገኘ የለዉጥ አመራር ለዉጡ የታለመለትን ዓላማ ይመታል ብሎ መጠበቅ አዳጋች ነዉ።

ስለዚህ በኢሕአዲግ ርዝራዦች አመራር ብቻ ለዉጡ ይሳካል ብሎ ከመጠበቅ፣ ነገ ሳይሆን ከዛሬዉ ከሁሉም ወገኖች (ኢሕአዲግን ጨምሮ ማለት ነዉ) የተዉጣጡ ተወካዮች የለዉጡን የሽግግር ጊዜ የመምራት ኃላፊነት መረከብ ይኖርባቸዋል። ይኸ ደግሞ ሊሆን የሚችለዉ ሥልጣኑን ለብቻዉ የሙጥኝ ብሎ ባለዉ የኢሕአዲግ ቡድን መልካም ፈቃድ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ ያለ ምንም አድርባይነት በቆራጥነትና በአንድነት ቆመዉ ገዥዉ ቡድን ላይ ተፅእኖ በመፍጠር ነዉ፤ ትግሉ ገና ያልተጠናቀቀ ስለሆነ ዋጋ ሊያስከፍል ይችል ይሆናል፣ ግን በዚህ ደረጃ አማራጭ የሌለዉ ጉዳይ ነዉ።

የዚህ አማራጭ መፍትሄ ሀሳብ በኦፌኮ ድርጅት በተደጋገሚ ቢቀርብም ገዥዉ የኢሕአዲግ ቡድን ጆሮ ዳባ በማለቱና ሌሎች የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶችም ጭምር ለጉዳዩ እጅግ አስፈላጊነት ከተናጠል ድርጅታዊ ፍላጎትና የግል ፍላጎት ማነቆ ወተዉ ማየት ስላልቻሉ ጉዳዩ እስከ ዛሬ ተቀባይነት አላገኘም።

በኢሕአዲግ አመራር ብቻ መጪዉ ብሔራዊ ምርጫ ፍትሓዊና ዲሞክራሲያዊ ይሆናል ብሎ መጠበቅ የፖለቲካ ጅላጅልነትና የሕዝቡን መራር ትግል ያለ ዉጤት መና ማስቀረት ብቻ ነዉ።

ከዚህ በተረፈ ያለዉ አማራጭ ማለቂያ በሌለዉ ዙሪያ ጥምጥም ዉስጥ መዳከርና አይቀሬ ለሆነዉ የሕዝቦች ትግል መዘጋጀት ብቻ ይሆናል።