አቶ ማሙሸት አማረ የሽብር ተልዕኮን በማስፈፅም ወንጀል ተከሰሱ


አቶ ማሙሸት አማረ የሽብር ተልዕኮን በማስፈፅም ወንጀል ተከሰሱ
(FANABC) — አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 25፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ራሱን ግንቦት ሰባት በማለት ከሚጠራው የአሸባሪ ቡድን ጋር በመገናኘት በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ተቀስቅሶ የነበረው ሁከት ወደ አመጽ እንዲስፋፋ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉት አቶ ማሙሸት አማረ ክስ ተመሰረተባቸው።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በዛሬው እለት ለተከሳሹ ክሱ እንዲደርሳቸው አድርጓል።

ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴር፣ ማነሳሳት እና ሙከራ ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ነው በአቶ ማሙሸት አማረ ላይ ክስ የመሰረተው።

አቶ ማሙሸት ውጪ ሃገር ሆነው የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ እንዲመሩ በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት ኬንያ ለመሄድ በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ ሞያሌ ከተማ ውስጥ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ተከሳሹ በነበሩበት የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አመራርነታቸውን በመጠቀም የሽብርተኝነት ድርጊት ፈጽመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም ሽመልስ ለገሰ በተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል አማካኝነት ተመልምለው የሽብር ቡድኑ አባል እንደሆኑ የአቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል።

“ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በትጥቅ እናስወግዳለን” በማለት የሽብር ቡድኑ አመራሮች በሰጡት ተልዕኮ መሰረት ከአዲስ አበባ፣ ከሰሜን ሸዋ እና ከጎንደር አካባቢ የመለመሏቸውን የሽብር ቡድን አባላት ወታደራዊ ስልጠና እንዲያገኙ ማመቻቸታቸውም በክሱ ተጠቅሷል።

ተከሳሹ በውጪ የሚኖሩ የሽብር ቡድኑ አባላት በ2008 ዓ.ም በተለያየ ጊዜ በላኩላቸው 260 ሺህ ብር ለምልምል አባላቱ የጦር መሳሪያ ገዝተው በማስታጠቅ፣ ስንቅ እንዲደርሳቸው በማድረግ እና ለወታደራዊ ስልጠና የሚሆን ቦታ ማዘጋጀታቸውም ነው በክሱ የቀረበው።

በአማራና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ሁከት እንዲቀጥል ከቡድኑ አመራሮች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመፈጸም መንቀሳቀሳቸውንም አቃቤ ህግ በክሱ አብራርቷል።

ተከሳሹ የፖለቲካ አመራርነታቸው እንደሽፋን ተጠቅሞ በሃገር ውስጥ ወታደራዊ ጣቢያ ለመመስረት መንቀሳቀሳቸውና ለዚህ የሽብር ተልዕኮ ከአዲስ አበባ አባላትን መልምለው በሁመራ በኩል ወደ ኤርትራ መላካቸውንም የክሱ ዝርዝር ያሳያል።

ፍርድ ቤቱ የክሱን ይዘት በችሎት አንብቦ መቃወሚያ ካለ ለመስማት ለነሃሴ 9 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

 

በኤርምያስ ፍቅሬ