አስቸኳይ አዋጁ ተጥሷል: ከስታዲየም ውስጥ ነው። ከወዲያ ማዶ ደጋፊዎች ”ይሰማል?”

አስቸኳይ አዋጁ ተጥሷል : ከስታዲየም ውስጥ ነው። ከወዲያ ማዶ ደጋፊዎች ”ይሰማል?” ይላሉ በህብረት። ከወዲህ በተቃራኒው የስታዲየሙ ክፍል ያሉት ደግሞ ”አዎ!” ይላሉ። ”ወያኔ” ይላሉ ከማዶ ያሉት ፡ ”ሌባ ነው” በማለት ይመልሳሉ ከወዲህ ያሉት። እንዲህ እንዲህ እያለ በስታዲየሙ ያለው ፖለቲካዊ ግለት ጨመረ። አስቸኳይ አዋጁ በጥብቅ የሚከለክለው ይህንኑ ጉዳይ ነበር። ”በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶችን ማስተላለፍ……” ብሎ በጥብቅ ይከለክላል። የባህርዳር ከነማ ደጋፊዎች ቀጠሉ።

”ቢመችሽም፡ ባይመችሽም፡ አንቺ ወያኔ አይቀርልሽም።”
” መሰናበቻ፡ መሰናበቻ፡ ያሆ! አሁን የቀረን ወያኔ ብቻ”

ዛሬ ባህርዳር ጥሳዋለች። ወለጋም ተጥሷል። ወሊሶ ከሁሉም ትቀድማለች። የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ዛሬ ያወጣችው መግለጫ የአዋጁን አንድ ክፍል የሚጥስ ነው። ”አዋጁን መቃወም አይቻልም” የሚለውን ክልከላ ወደጎን ያደረገችው ቤተክርስቲያኗ አዋጁ እንዲሰረዝ ጠይቃለች። አንዳንድ የተቃዋሚ አመራሮችም በአዋጁ የተቀመጠውን ”ለሽብርተኛ አቀንቃኝ ሚዲያዎች ቃለመጥይቅ መስጠት” የሚለውን አንቀጽ ጥሰው መልዕክታቸውን በተከለከሉ ሚዲያዎች እያስተላለፉ ነው። ዝርዝሩ ይቀጥላል።

ዛሬ ባህርዳር የነበረው ትዕይንት የታቀደ በስሌት የተካሄደ ለመሆኑ ቅንጅቱ ያረጋግጣል። የባህርዳር ከነማ ደጋፊዎች ዋንኛ ትኩረታቸው አዋጁን በመጣስ ለትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የትኛውም ህግና አዋጅ እንደማይገዙ ማሳየት መሆኑን በግልጽ የተመለከተበት ትዕይንት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ትዕይንት ከማክሰኞ በፊት ቢሆን ብዙም ላያስደንቀን ይችል ነበር። የአዋጁ አፈጻጸም በዝርዝር ከተገለጸበት ቀን ወዲህ መሆኑ መልዕክቱን ግልጽና ጠንካራ ያደርገዋል። ትውልዱ ፍርሃትን ተገላግሏል። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የቀረው ብቸኛ በስልጣን የመቆያ መንገድ ወታደራዊ አዋጅ ነበር። እሱም ተጣሰ።

በእርግጥ ከጨዋታው በኋላ ግጭት ተፈጥሯል። የባህርዳር ከነማ ደጋፊዎችና የአገዛዙ ታጣቂዎች መሀል ግጭት የተፈጠረ ሲሆን ህዝቡ ታጣቂዎችን ድንጋይ በመወርወር ማጥቃቱ ተሰምቷል። ከዚያን በኋላ የከነማን ማሊያ ለብሶና ሰንደቅ ዓላማ ይዞ የተገኘ እየታሰረ ነው ተብሏል። የሚጠበቅ ነው። ዋናው ጒዳይ በስታዲየም ውስጥ የሆነው ነው። አስቸኳይ አዋጁ ተጥሷል።

በቅርቡ ከእስር የተለቀቁት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) አመራሮች ወለጋ ናቸው። አዋጁ የሚከለክለው ያልተፈቀዱ ህዝባዊ ትዕይንቶችን ነው። በወለጋ ይህ ተጥሷል። በየከተሞቹ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ አደባባይ ግልብጥ ብሎ በመውጣት መሪዎቹን ሲቀበል የነበረው ትዕይንት እጅግ አስገራሚ ነው። ህዝብ ከወደደ እስከጥግ ይደግፋል። ትልቁ ነገር አስቸኳይ አዋጁ መጣሱ ነው። አመራሮቹ በበርካታ ከተሞች እየተዘዋወሩ ደጋፊዎቻችቸውን ሲያመሰግኑ ቆይተው ነቀምት በማምራት ላይ እያሉ መታገታቸው ተሰምቷል። ደንቢዶሎ አከባቢ በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱም ይነገራል። እነመረራ በፌደራል ፖሊስ አማካኝነት ባሉበት እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዋል። ይህን ማስታወሻ በምጽፍበት ጊዜም እንድታገቱ ነበር። ለማንኛውም አስቸኳይ አዋጁን የጣሰው የህዝቡ እርምጃ የሚያስደንቅ ነው። ፍርሃት ተሰብሯል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ዛሬ ያወጣችው መግለጫም ከአንድ ለእግዝያብሄር ቃል ተገዢ ከሆነ መንፈሳዊ ተቋም የሚጠበቅ ሃላፊነት በመሆኑ ልትመሰገን ይገባታል። እነአቡነ ማቲያስ የትግራይ ነጻ አውጪ ቡድን ካድሬ እንደሚያደርገው ከሌሎች አባቶች ጋር ቤተመንግስት ሄደው ለሃይለማርያም ”ውዳሴና ቡራኬ” በሚያዥጎደጉዱበት በዚህ ሰሞን የመካነየሱስ ቤተክርስቲያን አዋጁን በመቃወም እንዲሰረዝ መጠየቋ ተገልጿል። በአዋጁ አንድ አንቀጽ ላይ አዋጁን መቃወም በራሱ ክልክል ነው ይላል። የመካነየሱስ ቤተክርስቲያን ይህን ክልከላ ወደጎን በማድረግ አዋጁ እንዲሰረዝ በመጠየቅ ሃላፊነቷን ተወጥታለች። የካድሬዎች መጠራቀሚያ የሆነችው ቤተክህነት አሰላለፏን ከጨቋኙ ስርዓት ጋር ማድረጓ በሰማይም በምድርም ሲያስወቅሳት ይኖራል።

አዋጁ እዚህም እዚያም እየተጣሰ ነው። ተገቢ ነው። ትግሉ በዚህ ላይ መቀጠል አለበት። አዋጁን መጣስ ወቅታዊና ወሳኝ እርምጃ ነው። የትግራዩ ገዢ ቡድን የቀረውን ሃይል አሟጦ በመጠቀም ላይ ነው። ይህን ወቅት ከተሻገረ የተወሰነ ጊዜ ለመቆየት የሚያስችል አቅም ሊያጠራቅም እድሉን ያገኛል። ይህ እንዳይሆን ማድረግ የወቅቱ ትግል መሪ ዓላማ መሆን አለበት።

Mesay Mekonnen