አሃዳዊ የሽግግር መንግሥት ለፌደራል አገር? በፍጹም አይታሰብም!! (በዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ)

አሃዳዊ የሽግግር መንግሥት ለፌደራል አገር??? በፍጹም አይታሰብም!! (በዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ)
KMN:- Oct, 11/2020
 
የሥልጣን ዘመኑ ያበቃው የፌደራል መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን፣ የክልሎቹም ነው።
የፌደራሉን መንግሥት አስፈላጊ ግልጋሎቶችና ኃላፊነቶች ለማስቀጠል የሚችል የሽግግር መንግሥት እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ በዘጠኙ ክልሎችም (ሲዳማን ጨምሮ ማለት ነው) ውስጥ እንዲሁ ዓይነት ተመሳሳይ ተግባርና ኃላፊነት ያላቸው የሽግግር መንግሥታት ያስፈልጋሉ።
በመሆኑም፣ በአንድ ክልል ውስጥ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ማለት “በፌደራል ደረጃ አይቋቋም፣ ወይም በፌደራል ደረጃ ስለሚቋቋመው አይመለከተንም” ማለት አይደለም። በፌደራል ደረጃ ብቻ የሽግግር መንግሥት አቋቁሞ ክልሎቹን መርሳት፣ አንድም ክልሎቹን ለመንግሥት-አልባነት እና እሱን ተከትሎ ለሚመጣው ክልላዊ ሥርዓተ-አልበኝነት የሚያጋልጥ፣ ኃላፊነት የጎደለው፣ ተግባር ነው፤ አልያም አገሪቱ ፌደራል መሆኗን በዘነጋ አሃዳዊ ጣእረ-ሞት (ghost) እየተመሩ ስለኢትዮጵያ ማሰብ ነው።
 
በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሥልጣን ክፍተትን ለመሙላት ብለህ የሽግግር/ጊዜያዊ መንግሥታት (በክልልና በፌደራል ደረጃ) የምታቋቁመው፣ በዋናነት፣ ለአገሪቱ ተጨባጭ ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ መፍትሄ ለማበጀት እንጂ፣ ዓለምን ለማስደመም አይደለም። የሽግግር መንግሥት፣ ለአንድ አገር የጭንቅ ጊዜ ሥራ የሚሠራ ጊዜያዊ መንግሥት ለማቆም እንጂ፣ ለዓለም አገሮች “እዩኝ! እዩኝ!”ለማለት፣ የዲፕሎማሲ ትዕይንት ለማሳየት፣ ወይም የቱሪስትና የእርዳታ መስህብ ለመሆን የምናቆመው መንግሥት አይደለም።
 
በሽግግር/ጊዜያዊ መንግሥት በመጠቀም፣ ክፍተት የመሙላት ሥራውና መንግሥታዊ ህልውናን ማስቀጠል (ማለትም፣ የአገርን ሉዓላዊነትና ደህንነት እንደዚሁም የክልሎችን ቀጣይነት ማረጋገጥ፣ የመንግሥታዊና ማህበራዊ ግልጋሎቶችን ፍሰትን በየደረጃው ማስቀጠል፣ ሰላም፣ ጸጥታና ፍትህን በየደረጃው ማስከበር) ደግሞ በክልልም በፌደራል ደረጃም መሠራት ያለበት ነው። በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት የተከሰተውን የሥልጣን ክፍተት መሙላትም እንደዚሁ በክልልም በፌደራል ደረጃም መተግበር ያለበት ነው።
 
የዚህ የሽግግር መንግሥት ሥራ፣ ኃላፊነት፣ መመሪያ ሕግጋት እና መርሆዎች ምን ሊሄኑ እንደሚችሉ ከዚህ በፊት እዚሁ መንደር ላይ ሃሳቤን አጋርቻለሁ።
ሙሉ የሽግግር “ቻርተር” ካልተፃፈ የምትሉ፣ ፅፋችሁ አሳዩን። (ታድያ ዘጠኙንም ነው።) ተወያዮቹ ሳይወያዩ ሰነድ ማዘጋጀት እና ለማጸደቅ ስብሰባ መጥራት ግን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ብቻ ሳይሆን፣ እብሪት የሚመራው የሴረኞች ተግባር ነው።
የሆነ ሁኖ፣ የሕገመንግሥታዊ መንግሥት ማጣት ችግር በፌደራልም በክልሎችም ተከስቶ ሳለ፣ የምናቋቁመው የፌደራል የሽግግር መንግሥት ብቻ ነው ብሎ ማለት፣ ለአንድ ፌደራላዊ አገር አሃዳዊ የሽግግር መንግሥት ለማዋቀር ከመሻት ተለይቶ አይታይም።