ታጋዮችን ኣድኖ ማሰር ሃገርና ህዝብ ለገባበት ቀውስ መፍትሄ ኣይሆንም

ታጋዮችን ኣድኖ ማሰር ሃገርና ህዝብ ለገባበት ቀውስ መፍትሄ ኣይሆንም
(የኦነግ መግለጫ –ህዳር 2, 2020)
 
[SBO – Sadaasa 02,2020] በወጣቶች ላይ ተነጣጥሮ እየተካሄደ ካለው የጅምላ ግድያና እስራት ዘመቻ ጎን ለጎን በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣባላትና ደጋፊዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ኣድኖ የማዋከብ ዘመቻ እየተባባሰ መምጣቱን በኦሮሚያ ውስጥ ያለው ሁኔታ በቂ ምስክር ነው።
ህዳር 1, 2020ዓም በደህንነት ሃይሎች የኦነግ የቁጥጥርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን ኣቶ ኣለማየሁ ድሮን ከመኖሪያ ቤታቸው ኣፍኖ በመውሰድ በቡራዩ ከተማ ኣስረዋል። ኣቶ ኣለማየሁ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ክብርና ፍቅር ያላቸው ምሁርና የሃገር ሽማግሌ ሲሆኑ ኦነግ እያካሄደ ባለው ሰላማዊ ትግል ውስጥም ሰኔ 2019ዓም በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ለድርጅቱ የቁጥጥርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ በመመረጥ የትግል ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ሲሆኑ ከዚህም በተጨማሪ ባላቸው እውቀትና ሙያ ወገናቸውን በመርዳት የላቀ ክብር ኣላቸው።
ባላፈው ሰሞን የኦነግ ሊቀ-መንበር በመኖሪያ ቤታቸው በወቅታዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ በመስጠት ላይ ሳሉ በደህንነት ሃይሎች እንዲያቋርጡ ተደርገው የስነ-ስርዓቱ ተካፋይ እንግዶችም በታጎሩበትና በታሰሩበት ወቅት፣ ታጉረው በኋላም ሲወጡ ተይዘው በመታሰር ከተለቀቁት መካከል ኣቶ ኣለማየሁ ድሮ ኣንዱ ነበሩ።
 
በደህንነት ሃይሎች እየተፈጸመ ያለው በሰላማዊ መንገድ ትግል እያካሄደ ያለን ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ኣመራር ኣካል በየቦታው ኣድኖ የማሰርና የማንገላታት ተግባርን ኦነግ በጽኑ ያወግዛል። ይህ ሃገሪቱና ህዝቡ ከገቡበት ኣስከፊ ችግር ለማላቀቅ በሚደረግ ጥረት ከፍተኛ ሚና ያላቸውን ምሁራንና የሃገር ሽማግሌዎችን ማዋረድና በእስር የማሰቃየት እርምጃ ያለውን መጻዒ ሁኔታ ወደባሰ ኣሳሳቢ ደረጃ ያሸጋግረዋል እንጂ መፍትሄ ሊሆን ኣይችልም ብለን እናምናለን።
 
የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመትን ጨምሮ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ችግሮች ባጠቃላይ በብዙ መስክ ቀውሶች ታምሳ ዜጎቿ ኣስጊ የኑሮ ሁኔታ ላይ ለሚገኙባት ሃገር መፍትሄው በህገ-ወጥ መንገድ ስልጣን ላይ መንጠላጠልና በጠመንጃ ኣፈሙዝ ኣሰቃቂ ወንጀል በመፈጸም ህዝቡን ለማንበርከክ መሞከር ሊሆን ኣይገባም።
መፍትሄው የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራትና የተለያዩ ኣካላት ባጠቃላይ ሁሉም ዜጎች የሚሳተፉበትና እምነት የሚጥሉበት የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው።
 
ለዚህም የቀውሱ ማዕከል ተደርጎ የተተኮረበት ኦሮሚያና መላው ዜጎችን ከተቃጣባቸው ኣደጋ ለመታደግ ለብሄራዊ የኦሮሚያ የሽግግር መንግስት ምስረታ ኦነግ ላቀረበው ጥሪ ምላሽ መስጠት ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ ነው።
በህዝቡ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያና እስራት በንቃት እየተከላከሉ ሁሉንም ዜጎች ከዘርፈ-ብዙ ችግሮች የሚያላቅቀውን የመፍትሄ ሃሳብ ለማሳካት የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ መልዕክታችን ነው።
 
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በሰላማዊ መንገድ ትግል በማካሄድ ላይ ባሉ ኣባሎቻንና ደጋፊዎቻችን ባጠቃላይም በንጹሃን የሃገሪቱ ዜጎች ላይ በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ያለውን ወከባና እስር የምንቃወም መሆኑን እየገለጽን ይህንን ወንጀል ለማስቆምና የህዝቡን ተስፋና ምኞት እውን ለማድረግ ይዞት እየተንቀሳቀሰ ያለውን ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ትግሉን በቆራጥነት እንደሚቀጥል ለሁሉም ያረጋግጣል።
ድል ለሰፊው ህዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ህዳር 2, 2020ዓም