ብሔራዊ ጥቅም አልባዋ ሃገር- ኢትዮጵያ

ብሔራዊ ጥቅም አልባዋ ሃገር- ኢትዮጵያ

አንዲት ሃገር እንደሃገር ከምትቆምባቸው ምሰሶዎች አንዱ የራሷ የሆነ ብሔራዊ ጥቅሟ (National Interest) ነው። መጠኑ እንደአቅም ቢለያይም በሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ያለው ግን ከማንም ጋር ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።
ኢትዮጵያ ከ1983 ዓም ጀምሮ ብሔራዊ ጥቅም የሚባል ነገር የላትም። የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስት ጠላት አድርገው የተነሱት ከሃዲ ኃይሎች በሃገሪቷ ታሪካዊ ጠላቶች ተደግፈው ስልጣን ከያዙ በኋላ የመሰረቱት መንግስት ብሔራዊ ጥቅም የሚባል ነገርን አያውቅም። በእርግጥ እንዲኖራቸውም አይጠበቅም። ህገመንግስት ተብሎ የተፃፈው ሰነድም ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያስችል አይደለም።
 
ህገመንግስቱ ላይ የስልጣን ባለቤት ተብለው የተቀመጡት ስብስቦች(ብሔር/ብሔረሰቦች) በተፃራሪ ጥቅም የሚፋጩ ደመኞች እንጅ የጋራ ራዕይና ሀገር አለን ብለው የሚያስቡ ዜጎች አይደሉም። ህገመንግስቱም የግጭት መፈልፈያ ማሽን እንጅ በሰላም አብሮ የመኖሪያ መድረክ አይደለም።
የኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም ውድቀት አንዱ ማሳያ የኤርትራ ጉዳይን እስካሁን እያስተናገድንበት ያለው መርህ አልባ ጉዞ ነው።
 
ሌላው በልማት ጉዳይ እንኳ የጋራ አቋም መያዝ አለመቻላችን ነው። በተፃራሪ ጠባብ ብሔርተኛ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው አለመተማመን በታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ሳይቀር አደጋ ደቅኗል። የህዳሴ ግድብ በይፋ ሲጀመር ለሀገር ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አካላት ሳይቀር ተቃውመውታል። ካይሮ ላይ ግድቡን ተቃውመው ሰልፍ የወጡት እነጃዋር ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ “የአባይ አብዛኛው ገባር ወንዞች ከኦሮሚያና ከደቡብ የሚነሱ ናቸው” በማለት በጂኦግራፊና በፖለቲካ ድንቁርና አሳልጠው “አባይ ኬኛ” ብለዋል። አዲስ አበባ ላይ “ግድቡን አጠናቀን የመለስን ራዕይ እናሳካለን” ያሉት እነጌታቸው ረዳ መቐለ ላይ “ግድቡ ተሸጧል” አሉ። በእርግጥ ሀገርን በአክሲዮን መስርተናል ለሚሉ ኃይሎች የሀገር ፍቅራቸውን በሚያገኙት የትርፍ ድርሻ (dividend) ልክ ቢያሰሉት ሊገርመን አይገባም።
 
ይሄ ሁሉ የብሐራዊ ጥቅም ጉዞ አልባነት ዛሬ አረቦች “የአባይ ግድብ ጉዳይ የእኛ ብሔራዊ ጥቅም ነው” እንዲሉ በር ከፍቶላቸዋል። የብሔራዊ ጥቅም አልባነት ደግሞ የሀገር አልባነት ምልክት ነው።
ሀገራችንን ወደ ቦታዋ እንመልስ!
Dan Dimension