በፊኒፊኔ ላይ የመሬት ወረራ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ተገለጸ። 

በፊኒፊኔ ላይ የመሬት ወረራ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ተገለጸ። 

በከተማው ውስጥ የሚታየው የመሬት ወረራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ፣ለመሬት ወረራ ሀይ ባይ ባለመኖሩ እጅግ አሳሳቢና አስከፊ ደረጃ መድረሱን የቦሌ እና የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች የሥራ ኃላፊዎች አስታውቁ።

የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጥላሁን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ የመሬት ወረራ ከገበሬው መሬት በተጨማሪ ወደ መሬት ባንክ የገቡና ለመዝናኛ የተባሉ ቦታዎች ሁሉ በስፋት ተወረዋል። ለችግሩ መባባስ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ደንብ አስከባሪዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው ነው።

ወረራው የሚካሄደው በመንግሥት ኃላፊዎች ጭምር መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው ገል ጸዋል። በህገወጥ የተያዙ መሬቶችን በህገወጥ መንገድ ህጋዊ ማድረግ ሌላኛው ችግር መሆኑንም አመልክተዋል።

የሊዝ አዋጅ 721/2004 በአንቀጽ 35 አምስት ላይ እንደሚለው አንድ ሰው በመሬት ወረራ ተሰማርቶ ከተገኘ ከአምስት እስከ አስራ ሁለት ዓመት ፅኑ እስራትና በብር መቀጮ ደግሞ ከ30 ሺ እስከ 150 ሺ ብር እንደሚቀጣ ደንግጓል ያሉት አቶ ተስፋዬ ፣ነገር ግን መረጃዎች በክፍለ ከተማ፣ በወረዳና በደንብ አስከባሪዎች ሆን ተብሎ ስለሚሰወር ከክስ የዘለለ ዕርምጃ አልተወሰደም፡፡ ይህ ሁኔታ ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ችግር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የመሬት ባንክ ኦፊሰር አቶ አብዱላዚቅ አወል በበኩላቸው ‹‹መሬት ወረራ ከቃል በላይ ነው፡፡ ችግሩ በጣም አስከፊ ደረጃ ደርሷል፡፡ በተለይ ደግሞ ወረዳ ሦስት አካባቢ ለመዝናኛ፣ ለኢንቨስትመንትና ለተለያዩ አገልግሎት ለማዋል የታሰቡ ቦታዎች ሳይቀሩ በህገ ወጥ መንገድ ቤት ተሠርቶባቸዋል፡፡ ይሸጣሉ፤ ይለወጣሉ ›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ለተለያዩ አገልግሎት ይውላሉ ያላቸው መሬቶች በፍጥነት አለመልማትና ለበርካታ ዓመታት ክፍት መሆናቸው የመሬት ወረራውን ከአነስተኛ ደረጃ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ አድርጎታል ያሉት ኦፊሰሩ፣ጉዳዩ አሳሳቢ ከመሆኑ አንፃር መንግሥት በተቀናጀ መልኩ ዕርምጃ አለመወሰዱ ሌላኛው ችግር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አዲስ ዘመን ነሀሴ 12/2011

ሚሚ ጎበና