በጨለንቆ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን እልቂት ኣስመልክቶ የቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ መግለጫ

ትላንት በሚኒሊክና በጎበና በጨለንቆና በኣኖሌ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ ታሪክ  ዛሬም በሕወሃትና ኣጫፋሪዎቹ እየተፈጸመ ነው።

FXG Itti Fufee Manni Barumsaa Preparatory Amboo Cufame. በጨለንቆበጨለንቆ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን እልቂት ኣስመልክቶ የቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ መግለጫ

ፊንፊኔ፡ ኦሮሚያ

“በጨለንቆ ለ2ኛ ዙር ልጆቻቸው ለእልቂት ለተዳረጉባቸው የኦሮሞ ቤተሰቦች እንዲሁም በዚህ ሃዘን ቅስሙ ለተሰበረው የኦሮሞ ህዝብ መጽናናትን እንመኛለን”

ዛሬ በጨለንቆ የተከሰተው ዘግናኝ ወንጀል መላውን የኦሮሞ ህዝብና ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞን ያሳዘነና በ1880ዎቹ ውስጥ በኣኖሌና በጨለንቆ የወቅቱ ንጉስ ሚኒሊክና ጎበና በኦሮሞዎች ላይ የፈጸሙትን የታሪክ ጠባሳ የሚያስታውስ ነው።

በ1880ዎቹ ውስጥ የወቅቱ የኣማራ ንጉስ ሚኒሊክ ከሃዲውን ጎበናን ይዞ በወቅቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ዜጎችን በመግደል፣ በማሰርና በባርነት ወደ ሩቅ ሃገራት በመሸጥ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የፈጸማቸው ፍጅት፥ የኦሮሞን ህዝብ እስከዛሬ ድረስ ለገባበት ወደር የማይገኝለት የጭቆና ቀንበር የዳረገ ነው።

ዛሬም ስልጣን በተፈራረቁት የሃበሻ ገዢ ስርዓቶች በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲፈጸም ከነበረው ጋር በሚመሳሰል መልኩ ወያኔ/ሕወሃት ቅጥረኛ ተላላኪ ድርጅቱ ኦፒዲኦን ይዞ የጨለንቆን ታሪክ ለ2 ጊዜ በመድገም የኦሮሞ ዜጎችን በጅምላ በመፍጀት የዘር-ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው።

ባለፈው ዓመት በሀርሰዴ የኢሬቻ ክብረ-በዓል ላይ በኣንድ ቀን ያለኣንዳች ጥፋት የሕወሃት መንግስት የፈጃቸው ከ700 በላይ ኦሮሞዎች በሃገር ቤትና በውጪ ሃገራት ያለውን መላውን የኦሮሞ ህዝብ ለከፋ ሃዘን የዳረገ መሆኑ ይታወሳል። በዚህ ዓመት 2017 ውስጥም በኦሮሚያ ውስጥ ሲፈጸም የነበረው ፍጅት፣ ረሃብ፣ ሰቆቃ፣ እስራት፣ በኦሮሚያ ሃብት ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ ካሁን በኋላ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እንዳይፈጸም የኦሮሚያ ክልል ኣስተዳደርን ቀይረናል በሚል የኦፒዲኦ ኣመራሮች በድጋሚ ቃል ገብተው ነበር። ይህ ሁኔታ ሳይሆን ቀርቶ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ጭቆና ይበልጥ እየከፋ በመሄድ ላይ ይገኛል። በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው እስራት፣ ግድያ፣ ሳይወድ ከትውልድ መሬቱ መፈናቀል፣ መዘረፍና ከሃገሩ መሰደድ ከቀድሞው የላቀ መሆኑ ይታወቃል። ህዝባችን በየዕለቱ ይህ ሁኔታ ከዛሬ ነገ ይቀየራል በሚል ሲጠብቅ በሚዲያ ላይ ወተት ከሰማይ ይዘንብላችኋል ብለው በውሸት ተስፋ ረሃቡን ኣሳድረውት፡ ከኢህኣዴግ/ወያኔ መንግስት ይህን የውሸት የተስፋ ለውጥ እንዲጠብቅ ለማድረግ የስርዓቱ ካድሬዎች፡ ኦፒዲኦ ህዝቡን እያሳሳቱ እንዳሉ ይታወቃል።

ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ ባለፉት 7 ዓመታት በመላው ኦሮሚያ ውስጥ በወያኔ ስርዓት ላይ የኣንገዛም-ባይነት ኣመጾችን በማካሄድ የኦሮሞን ህዝብ ድምጽ በመላው ዓለም ማሰማትና የኦሮሞ ህዝብም ከጊዜ ወደ ጊዜ ነቅቶ ለመብቱ እንዲፋለም በማድረግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል። ለነጻነቱ ጥማት ሲል የኦሮሞ ህዝብ እየከፈለ ያለው ይህ መስዋዕትነት ምንም የማስመስለው ወያኔ/ሕወሃት ዛሬም በንቀትና በማናለብኝነት ለ2 ዙር በጨለንቆ ላይ ከ50 በላይ የሚሆኑ ንጹሃን የኦሮሞ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፥ በርካቶችንም ኣቁስሏል። ይህ ሁኔታ የኦሮሞን ህዝብ ኣንጀት የሚያቆስልና በእጅጉ የሚያሳዝን ቢሆንም ከትግሉ እንደማይገታው ግልጽ ነው።

ዛሬ በጨለንቆ በደረሰው እልቂትና በተለያዩ ጊዜያት በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ባለው ፍጅት ላይ በመመርኮዝ ይህን መሰሉ ሃዘንና የዘር-ማጥፋት ወንጀል ካሁን በኋላ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እንዳይፈጸም ዘንድ ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ ከዚህ በታች ያሉትን ነጥቦች ያስገነዝባል።

  1. ባጠቃላይ ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ እያካሄደ ያለውን ትግል ይበልጥ በማጠናከር ከዛሬው ዕለት ኣንስቶ በመላው ኦሮሚያ ውስጥ የጭቆና ፍጻሜ ኣመጽ በበለጠ መልኩ በመቀጠል፥ የመንግስት ሰራተኞች፣ የወያኔ ጦርና ፖሊስ ሃይሎች ውስጥ በቄሮ መዋቅር ስር የሚገኙ የኦሮሞ ብሄርተኞች ካሁን በኋላ ወደ ህዝባዊ ኣመጽ በማንቀሳቀስ ለባርነት ፍጻሜ ለማበጀት ቅድመ-ዝግጅታችንን ይበልጥ በእጠፍ-ድርብ መጨመራችንን ለኦሮሞ ህዝብ እናሳውቃለን
  2. የኦፒዲኦ ኣመራሮች ለህዝቡ በኣፋችሁ ብቻ ቃል መግባት ከጀመራችሁ ውሎ ኣድሯል። እስካሁን በመሬት ላይ የታየ ኣንዳችም ተጨማጭ ለውጥ ግን የለም። የኦሮሚያ ሃብት በባዕዳን ኢንቨስተሮች እየተዘረፈ ነው፣ ለመብታቸው የተፋለሙ የኦሮሞ ዜጎች በእስር ቤት ውስጥ እንግልት እየደረሰባቸው ነው፣ ህዝባችን በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስና በፌዴራል ሃይሎች ዘመቻ ከቀዬው ተፈናቅሎ በመሰቃየት ላይ ይገኛል፣ ረሃብና ሰቆቃ ከኦሮሞ ህዝብ ላይ ሊቀር ኣልቻለም። ስለሆነም ከማውራት ያላለፈው ለህዝቡ የገባችሁት የለውጥ ቃል ውሎ ሳያድር በተግባር ለኦሮሞ ህዝብ እንዲታሳዩ ኣጥብቀን እናሳስባለን
  3. በሃገር ቤትና በውጪ ሃገራት ያለው ህዝባችን፥ ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ እያካሄደ ያለውን ንቅናቄ ይበልጥ እያጠናከረ በመሆኑ ድጋፍና እገዛችሁ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ኣለበት። በፖለቲካና በሞራል ከቄሮ ቢሊሱማ ጎን በመቆም እያደረጋችሁት ያለው ድጋፍ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ኣፋጥኖ ከግቡ ለማድረስ ወሳኝ በመሆኑ በያላችሁበት ለባርነት ፍጻሜ እራሳችሁን ኣዘጋጁ
  4. በፍትሓዊ የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ላይ የምትገኙ ሃይሎች፥ የትግላችን ኣጋር የሆናችሁ ብሄሮችና ብሄረሰቦች እንዲሁም በውጪ ሃገራት የምትገኙ የኦሮሞ ምሁራን፡ ኢትዮጵያ ተብላ በምጠራው ሃገር ውስጥ በኣሁኑ ወቅት በኦሮሞ ላይ እየደረሰ ላለው ሁኔታ ፍጻሜ ለማበጀት የኦሮሞ ህዝብ እያካሄደ ካለው የጸረ-ባርነት ትግል ጎን በመቆም ከሃገር ቤት እየተካሄደ ካለው ንቅናቄ ጎን እንድትሰለፉና የጭቆና ፍጻሜ ዋዜማ እንዲሁም በሰው-በላው የወያኔ ስርዓት ውድቀት ላይ ከቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ ጎን እንድትቆሙ በኣክብሮት እንጠይቃለን።

ዘመኑ የጭቆና ፍጻሜ ዘመን ነው!

ድል ለኦሮሞ ህዝብ!

ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ

ፊንፊኔ፥ ኦሮሚያ

ታህሳስ 11 ቀን 2017ዓም