በግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚባክነውን ሀብት የሚያስቀር ረቂቅ የህግ ማዕቀፍ

በግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚባክነውን ሀብት የሚያስቀር ረቂቅ የህግ ማዕቀፍ በተያዘው ወር መጨረሻ ይፋ ይሆናል

በግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚባክነውን ሀብት

(.fanabc.) –አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የዲዛይን ለውጥ ምክንያት የሚባክነውን ሀብትና ጊዜ የሚያስቀር ረቂቅ የህግ ማዕቀፍ በተያዘው ወር መጨረሻ ይፋ እንደሚያደርግ የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ገለፀ።

ታላላቅ የመስኖ፣ የመንገድ፣ የስኳር ፋብሪካ እና የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እና ወጪ ሲጠናቀቁ አይስተዋልም።

የፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜና ወጪ አለመጠናቀቅ “የዲዛይን ለውጥ ችግር” በተደጋጋሚ የሚሰጥ ምላሽ ነው።

ለአብነትም የርብ፣ መገጭ፣ ተንዳሆ እና ከሰም የመስኖ ግድቦች ብቻ፥ ከተያዘላቸው የግንባታ ወጪ በላይ 13 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ወጪ መጠየቃቸውን ከዚህ ቀደም በሰራነው ዘገባችን መግለጻችን ይታወሳል።

መገጭ የመስኖ ግድብ ብቻውን ይጠናቀቃል ከተባለበት ሶስት ዓመት ዘግይቶ የግንባታ ሂደቱ ስድስት ዓመታትን ወስዷል።

የህንጻ፣ የመንገድና የግድብ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና ወጪ ለምን አልተጠናቀቁም በሚል፥ በሰራናቸው በርካታ ዘገባዎች ከተቋማት “የዲዛይን ለውጥ ችግር” የሚሉ ምላሾችን መስማት የተለመደ ነው።

የፕሮጀክቶች የጥናት እና የግንባታ ስራዎችን ጎን ለጎን ማስኬድ ለግንባታ ወጪውም፥ ለተያዘለት ጊዜ መጨመርም አብይ ምክንያት ሆኖ ይነሳል።

የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎት የስኳር፣ የባቡር፣ የኬሚካል እና የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽኖች የተቋማዊ አስተዳደር እና የፋይናንስ አጠቃቀም ላይ ጥናት አድርጓል።

በዚህም ተቋማቱ የፕሮጀከቶችን የአዋጭነት ጥናት በተሟላ ሁኔታ አለማቅረብ የገንዘብ ብክነት፣ የጥራት ቁጥጥር አለማድረግ እና ተናቦ ያለመስራት ችግሮች ይሰተዋሉባቸዋል ብሏል።

የመንግስት ፕሮጀክቶችን አዋጭነት ለይቶ ወደ ተግባር እንዲገቡ የሚያደርግ ራሱን የቻለ ተቋም ለረጅም ጊዜ አለመኖሩ፥ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንዳይቻልም ምክንያት ሆኗል።

ከቅርቢ ጊዜ ወዲህ ግን የፕሮጀክቶችን አዋጭነት በመለየት ወደ ተግባር የማስገባት ስራ በብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን በኩል እንዲፈጸም ስልጣን ተሰጥቶታል።

ኮሚሽኑ ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቶችን መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል አዲስ የህግ ማዕቀፍ እያዘጋጀሁ ነው ብሏል።

ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እና ወጪ አለመጠናቀቃቸው፥ በተቋማት ኃላፊዎች ብቻ የፕሮጀክቶች አዋጭነት በአግባቡ ሳይጠና ወደ ትግበራ መግባታቸው የፈጠረው ችግር ነው ብሎ ያምናል ፕላን ኮሚሽኑ።

ይህም ለፕሮጀክቶች የተመደበው በጀት በትክክል ለታለመለት አላማ እንዳይውል ያደርጋል።

በኮሚሽኑ የኮርፖሬት ከፍተኛ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ፈቃዱ ለማ፥ በተቋማት ኃላፊዎች ይሁንታ ብቻ ግልፅ የፋይናንስ አመዳደብን ሳይከተሉ ወደ ተግባር የሚገቡ ፕሮጀክቶች በጊዜና በተቀመጠላቸው በጀት አይጠናቀቁም ነው ያሉት።

አቶ ፈቃዱ አንድ ፕሮጀክት የተፈቀደለትን የጊዜ ገደብ እና ወጪ አለፈ ማለት፥ ፕሮጀክቱ ከመነሻውም ችግሩን ለይቶ አልገባም ነበር ማለት ነው ሲሉ ይናገራሉ።

የፕሮጀክቶች መጓተት መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ ሲዳርግ፥ ዜጎችን ከፕሮጀክቱ የመጠቀም ተስፋን እያቀጨጨ ለመልካም አስተዳደር ችግሮችም ምንጭ ሲሆን ቆይቷል።

የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን የሚያወጣው አዲሱ የህግ ማዕቀፍ ፕሮጀክቶችን የሚሰሩ ድርጅቶችን ከመምረጥ ጀምሮ፥ በተባለው ጊዜ ባላጠናቀቁት ላይ የሚወሰዱ ርምጃዎችን ያካትታል ተብሏል።
ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ለመከታተል የሚያስችለው ረቂቅ የህግ ሰነድ በተያዘው ወር መጨረሻ ተጠናቆ ለውይይት ይቀርባል።

ከስድስት የመንግስት ተቋማት ለፕሮጀክት ስራ ጋር ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ተለይተው፥ ረቂቅ ህጉን ለማዘጋጀት ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያው አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል።