በጅማ ሰቃ ለእስር የተዳረጉት አቶ አብዶ አባ-ጆቢር ማናቸው?

በጅማ ሰቃ ለእስር የተዳረጉት አቶ አብዶ አባ-ጆቢር ማናቸው?
Pandemic

(bbcamharic)—ከትናንት ጀምሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ እጃቸው ወደኋላ ታስረው እና በበርካታ በታጠቁ ወታደሮች ተከበው የሚታዩ ሰው ምስል በስፋት ሲጋራና ስለምንነቱ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ለመሆነ እኚህ ሰው ማናቸው?

በምስሉ ላይ የሚታዩት አቶ አብዶ አባ-ጆቢር ይባላሉ። ምስሉ የተነሳው ዕረቡ እለት በጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ከመኖሪያ ቤታቸው በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወሰዱ የሚሳይ ነው።

“ከሰዓት 11፡30 ላይ መጥተው መኖሪያ ቤታችንን ከበቡ። ከዚያ በሩን በርግደው ወደ ውስጥ ገብተው እጁን ወደኋላ አስረው እየደበደቡ ይዘውት ሄዱ” ሲሉ የአቶ አብዶ አባ-ጆቢር ባለቤት ወይዘሮ ጀሚላ አባራ ራያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እኚህ ሰው ማናቸው? ለምን በዚህ መልኩ ተያዙ?

አቶ አብዶ አባ-ጆቢር የጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባትም ናቸው።

አቶ አብዶ የሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ትምህርት ቢሮም ተቀጣሪ ናቸው።

“የነበረውን ሁኔታ መግለጽ ከባድ ነው። ፊልም የሚሰሩ እንጂ አንድ ሰው ለመያዝ የመጡ አይመስሉም። መኖሪያ ጊቢያችን በፖሊስ ተሞልቶ ነበር” ይላሉ ወ/ሮ ጀሚላ የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዱ ጨምረውም መኖሪያ ቤታቸውም ተፈትሿል።

እንደ ወ/ሮ ጀሚላ ከሆነ ባለቤታቸው የየትኛውም ፓርቲ አባል አይደሉም።

“አንድ ሰው በዚህ ወረዳ ውስጥ የወረዳውን አመለካከት ካልተከተለ፤ እንደ ተቃዋሚ ነው የሚታው” በማለት ባለቤታቸው ባላቸው የግል አመለካከት ብቻ ለእስር መዳረጋቸውን ይናገራሉ።

በተመሳሳይ ቀን በሰቃ ጮቆርሳ ወረዳ በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች ሰዎችም ስለመያዛቸው ለማወቅ ተችሏል።

አራቡ ካሊፋ የተባለ አንድ ወጣት ለቢቢሲ እንደተናገረው ረቡዕ ጠዋት ላይ ቤታቸው በጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ከተከበበ በኋላ ወላጅ አባቱ እና ወንድሙ ተይዘው መወሰዳቸውን ይናገራል።

“እኛ የየትኛውም የፖለቲካ አባል አይደለንም። በማንነታችን እንኮራለን፤ ለሕዝብ እንቆረቆራለን። እነሱ ግን ‘ከኦነግ ጋር ግነኙነት አላችሁ’ ይሉናል” ይላል አራቡ።

ፍተሻ

ለአቶ አብዶ አባ-ጆቢር እስር እና መኖሪያ ቤቱ ለምን እንደተፈተሸ የተሰጣቸው ምክንያት “በመኖሪያ ቤታችሁ ውስጥ የተለያየ አይነት የጦር መሳሪያና ሰዎችን ለመግደል እቅድ የተያዘበት ቃለ-ጉባኤ አለ” የሚል መሆኑን ባለቤታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“‘መኖሪያ ቤትህ ውስጥ የጦር መሳሪያ አለ። እሱን ሳንወስድ አንደሄድም’ አሉት። እሱ ደግሞ ‘ከፈለጋችሁ ቤቴን አፍርሳችሁ ፈልጉ። ምንም አታገኙም። የጦር መሳሪያ ካገኛችሁ ስቀሉኝ’ አላቸው” በማለት ወ/ሮ ጀሚላ በባለቤታቸው እና በጸጥታ አስከባሪዎቹ መካከል የነበረውን ንግግር ያስታውሳሉ።

በተደረገው ፍተሻ የጦር መሳሪያ አለመገኘቱን እና ልጆቻቸው ይጫወቱበት የነበረው የፕላስቲክ ሽጉጥ እና የታሪክ መጽሃፍ ይዘው መሄዳቸው ወ/ሮ ጀሚላ ተናግረዋል።

አቶ አብዶ ለእስር የተዳረጉት ረቡዕ ከሰዓት እንደነበረ እና እስከ ትናንት (ሐሙስ) ምሽት ድረስ 12፡30 ድረስ ቃል እንዳልተቀበሏቸው ባለቤታቸው ይናገራሉ።

“በጥሪ ወረቀት መጥራት ሲችሉ ልክ እንደሽፍታ እጁን ወደኋላ አስረው እየደበደቡ ይዘውት ሄዱ” የሚሉት ወ/ሮ ጀሚላ ፤ በአሁኑ ሰዓት ባለቤታቸው ታስረው የሚገኙት ከበርካታ ሰዎች ጋር መሆኑ ለኮቪድ-19 ይጋለጡ ይሆን ብለው እንደሚሰጉ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ አስተዳደር፣ የወረዳው ፀጥታ ጽህፈት ቤት እንዲሁም የወረዳውን ፖሊስ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።