በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅላይ ምኒስትሩ አረጋገጡ

በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅላይ ምኒስትሩ አረጋገጡ

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋገጡ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ከዕኩለ ለሊት በኋላ በብሔራዊ ቴሌቭዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ በባሕር ዳር በተፈጸመው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከባሕር ዳሩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ “በአማራ ክልል ያጋጠመውን ችግር እና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሆኖ እያስተባበረ እና እየመራ የነበረውን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በቅጥረኛ የተገዙ የቅርብ ሰዎች አሁን አመሻሽ ላይ የምንወደውን የምናከብረውን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም መሰል ጥቃት ተፈፅሞበታል” ብለዋል።

በኤታማዦር ሹሙ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ «በቀረንም ጊዜ በዚህ ጉዳይ ተባባሪ፤ ተሳታታፊ፣ አጋዥ የሆኑ በሕግ አግባብ ሊታዩ የሚገቡ ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር እናውላለን» ብለዋል።

ወታደራዊ መለዮ ለብሰው በቴሌቭዥን የቀረቡት ዐቢይ የመከለከያ ሰራዊት እና ለፌድራል ፖሊስ አባላት በመግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ለአገሪቱ ጦር ባቀረቡት ጥሪ ዕዝ እና ቁጥጥር እንዲከበር አሳስበዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው በጥቂት ግለሰቦች እንጂ በአንድ ብሔር አለመሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ምኒስትሩ የሰራዊት አባላት የብሔር ጥቃት እንዳይሰማቸው ተማፅኖ አቅርበዋል።

«የመከላከያ ሰራዊታችን፤ የፌድራል ፖሊስ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ባንዲራውን እና አገሩን አስቀድሞ፤ በዘር ሊከፋፍሉን እና ይቺን ታላቅ አገር ሊበትኑ የሚያስቡ ሰዎች ከእነ ዕኩይ ሐሳባቸው ጥቃታቸውን የምንከላከል እና ኢትዮጵያን የምናስቀጥል እንጂ በተፈጠረብን ትንኮሳ፣ በከፈልንው አሳዛኝ እና አስከፊ መስዋዕትነት ሸብረክ የማንል መሆኑን ዳግም ጀግነቱን እንዲያረጋግጥ ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ» ብለዋል

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ለኢትዮጵያ ሕዝብም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። «መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ጨለማ ጊዜ፣ በዚህ የችግር ጊዜ፤ የዛሬ ሰላሳ፣ አርባ አመት ኢትዮጵያ ውስጥ ተሞክረው የከሸፉ፤ ወደ ፊትም የማይሳኩ ሐሳቦችን የሚያራምዱ ግለሰቦችን ፤ ምንም እንኳ ጥቂት ቢሆኑ ያደረሱብን በደል፤ ያደረሱብን ጥቃት በቀላሉ የሚታይ አይደለም» ብለዋል።

ከአንድ አመት በፊት በመስቀል አደባባይ ለእርሳቸው በተካሔደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት ያስታወሱት ጠቅላይ ምኒስትሩ «ሸብረክ ሳንል በአንድ ልብ፣ በአንድ መንፈስ ጠላቶቻችንን መክተን ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን» ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

በጠቅላይ ምኒስትሩ መግለጫ መሰረት በባሕር ዳር ከተማ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገው ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተካፈሉበት ስብሰባ በመካሔድ ላይ ሳለ ነው። በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በጥይት ከተመቱት ውስጥ «ከፊሉ መሞታቸውን እና ከፊሉ መቁሰላቸውን» ጠቅላይ ምኒስትሩ ተናግረዋል። የሟቾችም ሆነ የቁስለኞች ቁጥር በጠቅላይ ምኒስትሩ አልተገለጸም።

ለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የክልሉ ገዢ ፓርቲ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ የተመራ ክልላዊ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መደረጉን ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር። ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ የአማራ ክልል የሰላም እና የደሕንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ናቸው።

በአሜሪካ በጉብኝት ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን «አሳፋሪ እና አሳዛኝ» ሲሉ ገልጸውታል።

DW Amharic