በደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤት እሳት ተነሳ

በደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤት እሳት ተነሳ

የደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤት እሳት አደጋ

(bbc)–ታራሚዎች ያስነሱትን አመፅ ተከትሎ የደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤት ለእሳት አደጋ መዳረጉን የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አስታወቀ።

የማረሚያ ቤቱ ምክትል መምሪያ ሃላፊ እና የታራሚዎች አያያዝና አስተዳደር ቡድን መሪ የሆኑት ምክትል ኮማንደር ባንቴ ጥበቡ ስለሁኔታው ለቢቢሲ ሲያብራሩ፤ አመፁ የተጀመረው ትናንት ምሽት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ የምህረት አዋጅን በተመለከተ በቴሌቭዥን የሰጡትን ዝርዝር ተከትሎ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከምክትል ኮማንደር ባንቴ መረዳት እንደቻልነው ታራሚዎቹ በምህረት አዋጁ ተጠቃሚ አንሆንም የሚል ዕምነት አድሮባቸዋል።

• በደሴ ከተማ የሸዋበር መስጂድ ላይ በደረሰ ጥቃት ሰዎች ተጎዱ

• የቤተ ክርስትያኗ የክፍፍል እና የውህደት ጉዞ

ትናንት ምሽት ቁጣቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ታራሚዎችን ማረጋጋት ተችሎ እንደነበር የተናገሩት ም/ ኮማንደሩ ”ዛሬ ጠዋት ግን የታራሚዎች ማደሪያ በር ከተከፈተ በኋላ ታራሚዎች በሮችን ገነጣጠሉ ከዚያም የመሳሪያ መጋዘን ቤቶችን ለመስበር ጥረት አድርገዋል” ሲሉ ስለተፈጠረው ሁኔታ አብራርተዋል።

ቆየት ብሎም በተቀሰቀሰ እሳት የማረሚያ ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና የማደሪያ ቤቶች በእሳት መያያዛቸውን ም/ኮማንደር ባንቴ ጥበቡ አክለው ነግረውናል።

ቃጠሎው ከተፈጠረ በኋላ በስፍራ ከደረሱ የከተማው ነዎሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ማረው አበበ በበኩላቸው በቃጠሎው ወቅት የታራሚዎች ጩኸት እና የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር ተናግረዋል።

• በደብረማርቆስ ‘ባለስልጣኑ አርፈውበታል’ የተባለው ሆቴል ጥቃት ደረሰበት

• ቀኝ እጇን ለገበሬዎች የሰጠችው ኢትዮጵያዊቷ ሳይንቲስት

የማረሚያ ቤቱን ሁኔታ ለመከታተል የተሰበሰበው የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር እየጨመረ በመጣ ወቅት ጠባቂዎች አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ህዝቡን ለመበተን ጥረት ማድረጋቸውን የዓይን ምስክሩ ያክላሉ።

ከሰዓት በኋላ እሳቱ እንደቆመ በምትኩ ጭስ ብቻ ይታይ እንደነበር ያጋሩን አቶ ማረው፤ በህይወት ላይ ስለደረሰው ጉዳት እንደማያውቁ ሆኖም በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያለው የዕደ-ጥበብ ማስተማሪያ ክፍል በእሳት እንደተቃጠለ ሲነገር መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሰው ህይወት ላይ ስለደረሰ ጉዳት ያገኘነው መረጃ የለም።

የደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤት በተለያዩ ወንጀሎች ጥፋተኛ ናቸው የተባሉ እና ፍርዳቸውን የሚጠብቁ ከአንድ ሺ በላይ ታራሚዎችን እና ተጠርጣሪዎችን በውስጡ የያዘ ነው።