መንግስት ከክልሎች መሬት ተረክቦ የሚያስተዳድርበት አሰራር እንዲቀር ተወሰነ

የፌዴራል መንግስት በውክልና ከክልሎች መሬት ተረክቦ የሚያስተዳድርበት አሰራር እንዲቀር ተወሰነ

መንግስት በውክልና ከክልሎች መሬት ተረክቦ የሚያስተዳድርበት አሰራር እንዲቀር ተወሰነ

(FBC ) –አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ሲባል የፌዴራል መንግስት በስምምነት ሰነድ ከክልሎች በውክልና መሬትን ተረክቦ ሲያስተዳድርበት የነበረው አሰራር እንዲቀር ተወሰነ።

በምትኩ መሬቱን የማስተዳደርና የማስተላለፍ ስራ በክልሎች ይከናወናል ተብሏል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትእዛዝ በጋምቤላ ክልል የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ያሉ ክፍተቶች ከተለዩ በኋላ ነው ውሳኔው የተሰጠው።

ከዓመታት በፊት የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንትን ለመጀመር ሲታሰብ ጋምቤላን ጨምሮ ከአራት ክልሎች የፌደራል መንግስት ከ3 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በውክልና ተረክቦ ለባለሀብቶች የማስተላለፍና የማስተዳደር ስራ የጀመረው።

መሬቱን ከክልሎች በስምምነት ሰነድ በመረከብ የማስተዳደሩን ስራ የጀመረው በአሁኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ነው፤ አስፈጻሚው ደግሞ የግብርና ኢንቨስትመንትና የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት፥ ዘርፉ ወስብስብ ችግሮች ገጥመውት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትእዛዝ ጥናት እንዲደረግበት ከተደረገ በኋላ ለሰፋፊ እርሻ በስምምነት ሰነድ ከክልሎች በፌዴራል መንግስት ሲተዳደር የነበረው አሰራር እንዲቀር ተወስኗል ብለዋል።

ይህም መሬት የማስተዳድር እና የማስተላለፍ ሃላፊነት የክልሎች እንዲሆን ያደርጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ በስምምነት ሰነድ መሬት ወደ ፌደራል መንግስት ማስተላለፍ እንዲቆም ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል።

እርግጥ የሀገሪቱ ህገ መንግስት መሬቱ በክልሎች እንዲተዳደር ቢደነግግም ለአሰራር ምቹነት ሲባል ነው በስምምነት ሰነድ በውክልና የፌዴራል መንግስት መሬቱን እንዲያስተዳደር የተደረገው።

የመሬት አሰራሩ ላይ ብዥታ ነበረ የሚሉት አቶ አበራ፥ ስለዚህም ነው አሰራሩ ወደ ነበረበት እንዲመለስ የተወሰነው ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ ለሁሉም ክልሎች እንዲሰራ የተወሰነ ሲሆን፥ ጥናት በተደረገበት የጋምቤላ ክልል ደግሞ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ጭምር የመሬት መለየትና የመረጃ ቋት ውስጥ አስገብቶ በብቁ ባለሙያዎች የመስራቱ ስራ እንዲከናወንም ነው የተቀመጠው።

ምክንያቱም በዚህ ክልል ካሉ 623 የሰፋፊ እርሻ ባለሀብቶቹ ለ381 ባለሀብቶች ከ45 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ተደራርቦ ተሰጥቷል።

በክልሉ 2004 ዓ.ም በወጣው ህግ መሰረት ለሰፋፊ እርሻዎች የመሬት ካርታ መስጠት ያለበት የክልሉ አካባቢ ጥበቃ፣ መሬት አስተዳደርና ደን ልማት ቢሮ ብቻ መሆን እንዳለበት ቢደነገግም የመሬት ካርታዎች ከቢሮ ውጪ መኖርያ ቤት ብሎም በጫት ቤቶች ውስጥም ጭምር እየተሰሩ ይሰጡ ነበር ተብሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተቀምጧል።

መሬት አሰጣጡ ላይም የመንግስት ባለስልጣናትና ባለሀብቶች አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ነበራቸው የተባለ ሲሆን፥ ይህ ነገር ሄዶ ሄዶ የህዝብ ሀብትን እስከማባከን የደረሰበት ሁኔታ እንዳለም ተብራርቷል።

ግለሰቦች በአራጣ የተበደሩትን ገንዘብና የራሳቸው ያልሆነ ንብረትን ለባንክ ብድር አላማ ሲያቀርቡ ከመንግስት አካላት ድጋፍ ነበራቸውም ተብሏል።

የዚህ ውጤት ከባንክ የተገኘ ብድር ለታለመት አላማ ላለመዋሉም መንገድን ከፍቷል።

ለምሳሌ በጥናቱ እንደተጠቆመው ባለሀብቶች ለስራ ማስኬጃ ብለው የተበደሩት 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለምን አላማ እንደዋለ ለመተንተን እንዳልተቻለ ነው።

ስለዚህም በጋምቤላ ክልል ያለው የዘርፉ አሰራር ተቋማዊ በሆነ መልኩ በእጅጉ እንዲሻሻል ታዟል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢንቨስትመንት መሬቶችን በመናበብ ሀገራዊ መረጃዎች ይደራጃሉ ብለዋል።

አሁን ላይ ለፌደራል መንግስት የተሰጠው ሃላፊነት ድጋፍ የመስጠት ነው ያሉት አቶ አበራ፥ ይህም በየቦታዎች የሚስተዋሉ ቅሬታዎችን ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል።

ከቀረጥ ነጻ ገብተው ሲፈለጉ ባልተገኙ መሳርያዎች ጉዳይ ላይም እርምጃ ይወሰድ ተብሏል።

በጋምቤላ ካሉ 623 ሰፋፊ እርሻ አልሚዎች 242 ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚ ናቸው፤ ነገር ግን በመስክ ጉብኝት ላይ የተገኙት 225 ብቻ ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥም ከቀረጥ ነጻ ያስገቡትና በመስክ ላይ የተገኙት መሳርያዎች ቁጥር ተለያይቷል።

ከቀረጥ ነጻ ገቡ ከተባለው 565 ትራክተሮች መስክ ላይ የተገኘው 312፣ ከ731 ማረሻ የተገኘው 523፣ ከ261 ፒክ አፕ ተሽከርካሪ የተገኘው 102፣ ከ62 ዶዘር 42 ብቻ የተገኘ ሲሆን፥ በአንድ ግለሰብ ከ261 ሜትሪክ ቶን በላይ ብረት ከቀረጥ ነጻ አስገብተው ብረቱ በቦታው አልተገኘም።

እንዲሁም በክልሉ በኢንቨስትመንት ላይ አሉ የተባሉ 29 ባለሀብቶች በስፍራው ያልተገኙ ሲሆን፥ ይህም ተጨማሪ ማጣራትን ይጠይቃል ተብሏል።

ለዚህ ሁሉ ያልተገባ አሰራር መንገድ የተከፈተው ሲጀመር ከቀረጥ ነጻ ለሚገቡ እቃዎች ከተሽከርካሪ በስተቀር ሌላ መመሪያ አለመኖሩ ባለው ላይም በቂ ቁጥጥር አለመደረጉ ነው።

ስለዚህም የጎደሉ መመሪያዎች እንዲሟሉ ከቀረጥ ነጻ ገብተው ላልታለመ አላማ የዋሉ ንብረቶች ዙርያ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ እርምጃ ይውሰድ ተብሏል።

በጋምቤላ ክልል በሰፋፊ እርሻ ዘርፍ ላይ ለተፈጠሩት እነዚህ ችግሮች የመንግስት አመራሩ ሰፊውን ድርሻ የሚወስዱ ሲሆን፥ ባለሀብቶችም እንደየ አቋማቸው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።

በክልሉ ካሉ 623 ባለሀብቶች 451 ወደ ስራ መግባት አለባቸው፤ ቀሪዎቹ ከገቡበት ጊዜ አንጻር ብዙ አይጠበቅባቸውም ተብሏል።

ከ451 ባለሀብቶች ውስጥ ግን የተሻለ ሁኔታ ላይ ያሉት 87 ባለሀብቶች ሲሆኑ፥ ደካማ አፈጻጸም ላይ ላሉት 27 ባለሀብቶች የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ነው አቅጣጫ የተቀመጠው።

እንዲሁም በጣም ደካማ ለሆኑት 269 ባለሀብቶች ደግሞ ሁኔታቸው ታይቶ ያላለሙትን መሬት በመንጠቅ ውላቸው እንዲቋረጥ ተብሏል።

 

በካሳዬ ወልዴ