በኦዲት ግኝት እንዲመለስ ከተጠየቀው 798 ሚሊዮን ብር የተመለሰው 124 ሚሊዮን ብቻ ነው … የፌዴራል ዋና ኦዲተር

በኦዲት ግኝት እንዲመለስ ከተጠየቀው 798 ሚሊዮን ብር የተመለሰው 124 ሚሊዮን ብቻ ነው … የፌዴራል ዋና ኦዲተር

Oditara Muummee Federaalaa

(ena)–አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ)ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በ2010 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ለመንግስት መመለስ ከነበረባቸው 798 ሚሊዮን ብር የተመለሰው ጥቂቱ ብቻ መሆኑን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በየዓመቱ የሚያስመዘግቡት የኦዲት ግኝት አሳሳቢነት አሁንም ቀጥሏል ይላል።

ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በመንግስት ላይ ከፍተኛ የበጀት ብክነት እያስከተሉ ነው።

ዋና ኦዲተር የፋይናንስ ህጋዊነትና የክዋኔ ኦዲት በማድረግ የገንዘብ አያያዝን በሁለት መንገድ ይመረምራል ያሉት አቶ ገመቹ፤ ከገንዘብ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ የኦዲት ግኝቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የኦዲት ግኝት ከሚታይባቸው መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከትንሽ እስከ ትልቅ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ዋናዎቹ ናቸው ነው ያሉት።

አቶ ገመቹ እንደ ማሳያ የጠቀሱት በመስሪያ ቤታቸው የ2011 ዓ.ም የኦዲት ግኝት በባለ በጀት መስሪያ ቤቶች አሳማኝ ባልሆነ መልኩ የተከፈለ 798 ሚሊዮን ብር ተመላሽ እንዲደረግ መወሰኑን ነው።

መስሪያ ቤቱ እንዲህ ቢልም ከዚህ ውስጥ ለመንግስት ተመላሽ የሆነው ከ124 ሚሊዮን ብር የማይበልጥ  ነው ይላሉ።

ሁኔታው ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አመላካች እንደሆነም ነው ያብራሩት።

በቅርቡ ለከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የስልክና ላፕቶፕ ኮምፒውተር ግዢ በተጋነነ ዋጋ መፈጸሙ ይታወሳል።

ለአንድ ተንቀሳቃሽ ስልክ /ሞባይል/ 94 ሺህ ብር፤ ለአንድ ላፕቶፕ 152 ሺህ ብር ወጪ መደረጉን የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲም “ህገወጥ” ብሎታል።

አቶ ገመቹም ጉዳዩ በኦዲት ግኝትም የሚያስጠይቅና እርምጃ የሚያስወስድ መሆኑን ተናግረው፤ “አሁንም እርምጃ መወሰድ አለበት ብዬ ነው የምጠብቀው” ብለዋል።

በተመሳሳይ ከሁለት ዓመት በፊት አንድ ተቋም የሞባይል ስልክ በ32 ሺህ ብር ገዝቶ በመገኘቱ ገንዘቡ ተመላሽ ይሁን መባሉን ያስታውሳሉ።

ከኦዲት ግኝት ጋር የተያያዘ ችግር ተባብሶ መቀጠሉ መንግስትን ገንዘብ እያሳጣ ከመሆኑ በላይ የፍትሃዊነት ጥያቄም እያስከተለ ነው ይላሉ ዋና ኦዲተሩ።