በኦሮሚያ በርካቶች እየታሰሩ ነው ተባለ 

በኦሮሚያ በርካቶች እየታሰሩ ነው ተባለ

ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች እየታሰሩ መሆኑን የአይን ምስክሮች አስታወቁ። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት እና የኃይማኖት መሪዎች ጭምር መታሰራቸዉን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላቱን ጨምሮ በርካቶች በተለያዩ ቦታዎች መታሰራቸውን መረጃ እንደደረሰው ገልጿል፡፡

DW News – የኢትዮጵያ ዕለታዊ ዜና መጽሔት March 28, 2018

ባለሥልጣናት እና የኃይማኖት መሪዎች መታሰራቸው ተነግሯል
ኢትዮጵያ የእስር ቤት በሮቿን ወለል አድርጋ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ከለቀቀች ገና ሁለት ወር እንኳ ሳይሞላ ድጋሚ በእስር ዜና ትናጥ ይዛለች፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ባህርዳር፣ ከቡራዩ እስከ አምቦ፣ ከሰበታ እስከ ጭሮ በርካቶች መያዛቸው እየተነገረ ነው፡፡ ሰዎቹን የሚያስረዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት መሆኑን በየአካባቢው ያሉ የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡

ከየቤታቸው የተወሰዱ ታሳሪዎች ያሉበትን ለማወቅ ቤተሰብም ሆነ ወዳጅ ዘመድ መቸገሩን ያስረዳሉ፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአምቦ ከተማ ነዋሪ እርሳቸው በሚኖሩበት አውቶብስ ተራ አካባቢ ብቻ ባለፈው ሳምንት ሶስት ሰዎች መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

“እዚህ አካባቢ ያሉ አንዳንድ ለፖለቲካ አቅርቦት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን በማስገደድ እና በመያዝ እያሰሯቸው ነው ያለው፡፡ ሰው ከገባ በኋላ ጸጥ በሚልበት ሰዓት በዚያ ሰዓት ነው እየገቡ እያሰሩ ያሉት፡፡ ማታ ላይ ነው የሚመጡት ምክንያቱም ቀን ላይ ሲሆን አብዛኛው ሰው ምንድነው ብሎም የመከራከር ነገርም ስለሚኖር ለመሸሽ ሲሉ ወደ ማታ ላይ በመምጣት እያንዳንዱን ሰው እየያዙ ያስገባሉ፡፡ የት እንደሚሄዱም አይታወቅም፡፡ እዚያ አከባቢ ያለ ማረሚያ ቤት ራሱ አይገኙም፡፡ የሉም፣ እንዲዘህ አይነት ሰው አልተያዘም፣ አልታሰረም ይላሉ፡፡ ለምንድን እንደተወሰዱ ራሱ ለጥያቄ ነው የምንወስዳቸው፣ ጠይቀን እንመልሳችዋለን ይባላል፡፡ አይመለሱም፤ ይሄዳሉ፤ በዚያው ይቀራሉ፡፡ እንግዲህ ለጊዜው የኮማንድ ፖስት ሰዎች ናቸው የሚይዟቸው፡፡ የአካባቢው ፖሊሶች አይደሉም፤ አናውቃቸውም፡፡ እንደ አጋዚ አይነቶች ናቸው፡፡ ከኮማንድ ፖስት ጋር በጋራ በመሆን እነሱ ናቸው ይሄን ነገር እየሰሩ ያሉት” ይላሉ፡፡

እስራቱ በርትቶባቸዋል ከተባሉት የኦሮሚያ አካባቢዎች አንዱ በሆነው በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በአካባቢያቸው በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ ታሳሪዎች ወጣቶች ናቸው ይላሉ፡፡ የከተማይቱ ከንቲባ እና የሰላም መስጊድ ኢማምን የጨመረ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

“እንዳንድ ሰዎች ያው እየታሰሩ ነው፡፡ እንዳለ የሚያዙት በመኖሪያ ቤታቸው በማታ ነው፡፡ ኮማንድ ፖስት ነው እየያዘ የሚወስዳቸው፡፡ ዝም ብለው ነው እንግዲህ ይህ ነው ብለው የሚናገሩት የለም፡፡ ድሬዳዋ ነው እየወሰዱ የሚያስሯቸው፡፡ አይናገሯቸውም ያው ቀጥታ ይዘዋቸው ነው የሚሄዱት፡፡ እዚያ ቤተሰብ ተከትሎ ለመጠየቅ እንኳ አይችልም፡፡ እዚህ ከተማ ብዙ ሰው ነው የታሰረው፡፡ የአካባቢ ሽማግሌ፣ ትልልቅ ሰዎች፣ ባለፈው ለተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታ ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከንቲባው ራሱ ታስሯል፡፡ አሁን እዚያ ከወሰዱት አንድ ሳምንት ይሆናል” ሲሉ በጭሮ ከተማ የተከሰተውን ይገልጻሉ።

የጨለንቆ ከተማ ነዋሪ የሆኑ እና ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ግለሰብ የአካባቢው አንድ ባለስልጣን መታሰራቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ የሜታ ወረዳ የጸጥታ ኃላፊ የሆኑት ኢንስፔክተር አህመድ ኡስማንን ጨምሮ በርካታ የከተማይቱ ወጣቶች በቁጥጥር ስር እንዳሉ ያብራራሉ፡፡

“ከሶስት ሳምንት በፊት በዚህ ከተማ አድማ አድርገን ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አንድ ኃላፊ በአድማ ምክንያት ታስሯል፡፡ ኢንስፔክተር አህመድ ኡስማን ይባላል፡፡ ድሬዳዋ ሽንሌ የሚባል አለ እዚያ ተይዞ ሄዶ እዚያው ታሰረ፡፡ በግድ ሱቆቹን ሰዎቹ እንዲከፍቱ አስድርግ ተብሎ እርሱ ‘ሰዎቹ በራሳቸው ነው የዘጉት፣ እኔ ከአቅሜ በላይ ነው’ ሲል በዚያ ምክንያት እስካሁን ታስሯል፡፡ ኢንስፔክተር አህመድ የታሰረ ጊዜ ከእርሱ ጋር ዘጠኝ ልጆች ታስረው እዚያ ሽንሌ ድሬዳዋ የተወሰዱ አሉ፡፡ ያለምንም ምክንያት ማለት ነው፡፡ እና ህዝቡ ከፍተኛ ስቃይ፣ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሰው ወጥቶ መግባት ራሱ ሰላም እያጣ ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ ከገጠር ወደ ከተማ መጥተው ለራሳቸው የሚፈልጉትን ገዝተው ሲመለሱ በጣም ስጋት ውስጥ ናቸው፡፡ ህዝቡ የትም ቦታ በጣም ስጋት ውስጥ ነው” ሲሉ የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ