Kichuu

ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ቀሪ የአቃቢ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ ተሰጠ

በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ቀሪ የአቃቢ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ ተሰጠ ( የታህሳስ 20 የፍርድ ቤት ውሎ)

ታህሳስ 20 በዋለው ችሎት 2ት ምስክሮች ተሰምተዋል:: አቃቢ ህግ በ6ኛ (ገላና ነገራ) እና 11ኛ(በየነ ሩዳ) ተከሳሽ ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮች እንደቀረቡ ለችሎት አሳውቆ የሚመሰክሩበትን ጭብጥ አሲዟል፡፡

( Ethiopian Human Rights Project) – 11 ተከሳሽ በሆነው በየነ ሩዳ ላይ ለመመስከር የቀረቡት አቶ ዳውድ አበጋዝ ሲሆኑ በ20/05/2008ዓም በፌደራል ወንጀል ምርመራ ማእከል ተገኝተው ከተከሳሽ ኢሜል፣ ፌስቡክ እና ሞባይል ላይ መረጃዎች ሲወጡ የታዘቡትን እንደሚመሰክሩለት አቃቢ ህግ በጭብጥነት አሲዟል፡፡

ምስክሩ በ20/05/2008ዓም ማእከላዊ የምትሰራ ዘመዳቸውን ለመጠየው ሄደው በነበረበት ወቅት ካፊቴሪያ ሆነው ሻይ እየጠጡ ሳለ መርማሪ ፖሊስ መጥቶ ለደረጃ ምስክርነት እንደጠየቃቸው እና እሳቸውና ሌላ አብረዋቸው ታዛቢ ለመሆን ፈቃደኛ ከሆኑት አቶ ተስፋዬ ሃ/ማርያም ከሚባሉ ግለሰብ ጋር በመሆን ከመርማሪው ጋር ወደ ቢሮ ቁጠር 31 እንደገቡ ገልፀዋል፡፡ ተከሳሽ በየነ ሩዳን ከችሎት ለይተው ያሳዩ ሲሆን በወቅቱ ተከሳሽ አቶ በየነ ሰላማዊ ሰው ሆነው ወደ ምርመራ ክፍል መግባታቸውን የገለፁት ምስክሩ መርማሪው ይዞ የመጣውን ሞባይል የኔ ነው ብሎ ተከሳሽ ሲከፍት አይቻለሁ ብለዋል፡፡

ተከሳሽ ፌስቡክ አካውንታቸውን እና ኢሜላቸውም በፈቃደኝነት ከፍተው ከፌስቡክ የወጣ 40ገፅ ከኢሜል የተገኘ ደግሞ 3ት ገፅ እራሳቸው ተከሳሽ ፕሪንት አድርገው ከራሳቸው የተገኘ መሆኑን አምነው ከፈረሙ በኋላ እሳቸው እና ሌላኛው ታዛቢ ምስክር እንደፈረሙበት ተናግረዋል፡፡ ፕሪንት የተደረጉት ሰነዶች በኦሮምኛ የተፃፉ በመሆናቸው ይዘቱን ማወቅ እንደማይችሉ የተናገሩት ምስክሩ ተከሳሽ በየነ፡ አብዲ ቱፋ ከተባለ ግለሰብ እና ሌሎች ሰዎች ጋር የተፃፃፉት የመልእክት ልውውጥ እንደሆነ ግን እንደሚያስታውሱ ተናግረዋል፡፡ የፈረሙበት የሰነድ ማስረጃ ከሌላ ማስረጃዎች ጋር ተደባልቆ ተሰጥቷቸው ለይተው አሳይተዋል፡፡ ሞባይሉ ሲከፈት የወታደሮች ምስል ያለበት፣ የኦነግን ባንዲራ ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ የሚያሳይ ፎቶ እና ቪዲዮም እንደነበር ተናግረዋል ምስክሩ፡፡ የኦነግን ባንዲራ እንዴት ሊለዩት እንደቻሉ ሲጠየቁ፡ ባንዲራው አረንጓዴ እና ቀይ ቀለም ያለው መሆኑን በቴሌቭዢንም አይተውት የሚያውቁት በመሆኑ እንዲሁም ባንዲራው ላይ መፈክር ተጽፎበት የነበረ በመሆኑ ሊለዩት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ኦሮምኛ ቋንቋ እንደማያወቁ የተናገሩት ምስክሩ ባንዲራው ላይ አለ የሚሉትን ፅሁፍ መፈክር እንደሆነ እንዴት እንዳወቁ ሲጠየቁ መፈክሩ በኦሮምኛ ቋንቋ የተፃፈ ቢሆንም ሲታይ ሁከት እና ብጥብጥ የሚጠራ ይመስላል ብለዋል፡፡

በ6ኛ ተከሳሽ ገላና ነገራ ላይ ለመመስከር የቀረቡት ምስክር ሻምበል አሰፋ ተሾመ ይባላሉ፡፡ የካቲት 24-6-2008 ቀን ማእከላዊ ተገኝተው ተከሳሽ ገላና ቃሉን በፈቃደኝነት ሲሰጥ መታዘባቸውን የሚያስረዱ ምስክር እንደሆኑ አቃቢህግ በጭብጠነት አስመዝግቧል፡፡

ሻምበል አሰፋ በአራዳ ክ/ከተማ የሚገኝ ወረዳ ፅ/ቤት አስተዳዳሪ እንደሆኑ የተናገሩ ሲሆን ከወረዳው ወደ ማእከላዊ የተላኩት ለታዛቢነት እንደሚፈለጉ ተነግሯቸው እንደሆነ እና ሌላ አብሯቸው በወረዳ የሚሰራ አቶ ዘሪሁን የሚባልም እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ ተነግሮት ማእከላዊ እንደተገናኙ ገልፀዋል፡፡ በምርመራ ክፍል 32 እሳቸው እና ሌላኛው ታዛቢ አቶ ዘሪሁን ከተገኙ በኋላ መርማሪው ተከሳሽ ገላናን ይዞ በመምጣት ማንነታቸውን እና ለምን እንደመጡ እንዳስተዋወቃቸው ተናግረዋል፡፡ ተከሳሽ ቃሉን በፈቃደኝነት እንዲሰጥ ያለመስጠት መብትም እንዳለው ቃሉን ቢሰጥ ግን ለፍርድ ቤት ማስረጃ እንደሚሆነው እና እንደሚጠቅመው መርማሪው ለተከሳሽ ከአስረዳ በኋላ ተከሳሽም ተስማምቶ ቃሉን መስጠት እንደጀመረ ገልፀዋል፡፡ ተከሳሽ የሰጠውን ቃል ሙሉ ለሙሉ ባያስታውሱም፡ የሆነ ሰው ከውጪ ደውሎለት ጎበዝ ነህ ሚስጠር ጠባቂ ነህ ብሎ ሃገር ውስጥ ከሚገኝ ሌላ ሰው ጋር እንዳገናኘው፡፡ ምስራቅ ሸዋ ጀልዱ የሚባል ቦታ ጫካ ውስጥ ወጣቶችን ማደራጀቱን፣ ‘የኦነግ ታጣቂ ሃይል እኪመጣላችሁ ድረስ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ፀብ እንዳትፈጠሩ’ የሚል ትእዛዝ መቀበሉን ለመርማሪ ሲገልፅ መስማታቸውን እንደሚያስታውሱ ገልፀዋል-ምስክሩ፡፡ ተከሳሽ ቃሉን ከሰጠ እና መርማሪው ካነበበለት በኋላ እንዳስፈረመው፡ እሳቸው እና ሌላኛው ታዛቢ በበኩላቸው የሰሙትን ቃል የሚገልፅ ሌላ ሶስት ገፅ ሰነድ ላይ መፈረማቸውን፣ ተከሳሽ ስንት ገፅ ቃል እንደሰጠ እና እንደፈረመ እንደማያሰታውሱ፣ ተከሳሽ በወቅቱ ምንም የተለየ ነገር እንደማይታይበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

መርማሪው ቃሉን ተቀብሎ እና የፃፈውን ለተከሳሽ አንብቦ ለማስፈረም በነበረው ሂደት አንድ ሰአት ያክል ምርመራ ክፍል ውስጥ እንደቆዩ የሚናገሩት ምስክሩ መርማሪው ተቀምጦበት የነበረው ወንበር ከእርሳቸው ራቅ ይል ስለነበረ መርማሪው የተከሳሽን ቃል ይቀበልበት የነበረው ወረቀት ከዛ በፊት የተፃፈበት የሁን አይሁን የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነገር ግን ወረቀቱ ላይ ይፅፍ እንደነበረ እና ያን ይፅፍበት የነበረ ወረቀት ላይ ተከሳሽን እንዳስፈረመው ገልፀዋል፡፡

ወደ ማእከላዊ የሄዱበትን ቀን የተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንድሙ በመስቀለኛ ጥያቄ ወቅት ጠይቀዋቸው ምስክሩ ህዳር 24፣2008 መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እርግጠኛ እንደሆኑም አቃቤ ህጉ ሲጠይቅ “አዎ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል፡፡

የጠዋቱ ችሎት ከመጠናቀቁ በፊት አቶ ደጀኔ ጣፋ የተሰማው ቅሬታ ለዳኞች ተናግሯል፡፡ “አቃቤ ህግ ትክክለኛ ፕሮሲጀሩን መጠበቅ አለበት፡፡ በዚህ ችሎት ከዳኞች የምናየው ጥሩ ነገር እንዳለ ሆኖ በግልፅ ለአቃቤ ህግ የሚጎድላቸውን ነገር እያየን ነው፡፡ ዳኞች ጋር ያለን ጭላንጭል ዲሞክራሲን ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡ እናም እንዲስተካከል ነው የምንጠይቀው “ ሲል ሃሳቡን ተናግሯል፡፤ ዳኞችም “በአካሄዳችን ላይ እንገማገማለን፡ የሚስተካከለውን እናስተካክላለን፣ በሂደቱም እንነጋገራለን፡ መጨረሻውን ብቻ ሳይሆን ሂደቱ ላይም አተኩረን ነው የምንሰራው፡፡ ትልቅ ሃላፊነት እና ጫና ነው ያለብን፡፡ ጥርጣሬ ባይኖርባችሁ መልካም ነው፡፡” ብለዋል፡፡

በከሰአቱ ችሎት አቃቤ ህግ ምስክሩ እንዳልመጣ ስልክ ቢደወልለትም እየመለሰ ባለመሆኑ በቀጣይ ሳምንት በተያዘው ቀጠሮ (ታህሳስ 25-27) ከሌሎች ምስክሮች ጋር እንዲሰማ ጠይቋል፡፡ ዳኞች ለአቃቤ ህግ “ታስሮ እንዲቀርብ ነው የሚፈልጉት?” ሲሉት ከሌሎች ምስክሮች ጋር በቀጠይ ቀጠሮ ሳይታሰር እንዲቀርብ እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡

የ13ኛ እና የ7ኛ ተከሳሽ ጠበቆች ከታህሳስ 25-27 የተያዘው ቀጠሮ ምስክሮች በዚህኛው ቀጠሮ ወቅት ቀርበው ጊዜ ካልበቃቸው ተብሎ የተያዘ መሆኑን አሁን ግን አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ማቅረብ አለመቻል ብቻም ሳይሆን የማቅረብ ፍላጎትም እንደሌለው፡ [ለምሳሌ ዛሬ መቅረብ የነበረበት ምስክር ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ታስሮ እንዲቀርብ ሲጠየቅ ታስሮ እንዲቀርብ አለመፈለጉ] ይቅረቡ በተባለ ወቅት ያልቀረቡ ምስክሮችን ተጨማሪ ቀጠሮ መስጠት አሳማኝ አለመሆኑን፣ ደንበኞቻቸው ከአመት በላይ በእስር ያሉ መሆናቸውም ከግምት ውስጥ እንዲገባላቸው በማሳሰብ ምስክር ለማስማት ሌላ ቀጠሮ ይሰጥ የሚለውን የአቃቤ ህግ ሃሳብ አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡

“እንደሚታወቀው አቃቢ ህግ ከዚህ ቀደም ብዙ እድሎች ተሰጥተውታል፡፡ በተደጋጋሚ ሰአት አሳልፎ ነው የሚመጣው፡፡ ከ1-42ኛ የአቃቢ ህግ ምስክሮች ተጠርተው በቅደም ተከተል መሰማት እያለበት አቃቤ ህግ እንደተመቸው እያዘበራረቀ እንዲያሰማ ተፈቅዶለታል፡፡ የምስክሮቹን ሁኔታ እንኳን ከቁጥር በዘለለ ለችሎት እያስረዳ አይደለም-አቃቤ ህግ፡፡ ከዚህ የበለጠ ግን እድል ሊሰጠው አይገባም፡፡ እኛ ታስረን ነው ያለነው፡፡ ብዙ ስቃይ እያሳለፍን ነው፡፡ ያለንበትን ሁኔታ በኛ ቦታ ያለ ካልሆነ ማንም አይረዳውም፡፡ አቃቤ ህግ ምስክር እንዲያመጣ የተነገረው ለመጨረሻ ጊዜ ተብሎ ነው፡፡ ይቅረብ ከተባለ እንኳን ዛሬ ሳይመጣ የቀረውን ምስክር ብቻ እንዲሰማ የተቀሩት ግን በፈቃዳቸው እንደቀሩ ተደርጎ ይቆጠርና ይታለፍ” ሲል 4ኛ ተከሳሽ የሆነው የኦፌኮ ም/ፕሬዝዳንት አቶ በቀለ ገርባ የተሰማውን አስተያየት የሰጠ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጣፋም የሚከተለውን ሃሳብ ሰጠቷል “ይሄኛው ቀጠሮ የመጨረሻ ቀጠሮ ተብሎ ታዞ ነበረ፡፡ በጠቅላላ የተመዘገቡት 42 ምስክሮች ናቸው፡፡ በቀን 10 ቢሰማ እንኳን በ5ቀን ያልቅ ነበር፡፡ 10ሩን ትተን በቀን 5 ምስክር ማሰማት ቢችል ኖሮ 8 ቀን በቂ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ጊዜ ምስክር ለመስማት በሚል እየተንገላታን ነው፡፡ አቃቤ ህግ የፈለገውን ማድረግ ይችላል፡፡ ሃይል አለው፡፡ አሉኝ የሚላቸውን ምስክሮች አስሮ ማቅረብ የሚችል አካል ነው፡፡ አቃቤ ህግ ግን ይህን ማድረግ፣ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም፡፡ እኛ መጉላላት እና መሰቃየት የለብንም፡፡ ሆን ተብሎ እየተሰቃየን እንደሆነ ታዩታላችሁ፡፡አቃቤ ህግም የኛ ችግር ሊሰማው ይገባል፡፡ መንግስት ያለውን ጉልበት እኛ ላይ አያሳይ፡፡ እኛ ኢትዮጵያኖች አይደለንም? አቃቤ ህግ የፍ/ቤቱን አቅም እየፈተነ ነው በግልፅ ጫና እያደረጉባችሁ ነው፡፡ ስለዚህ ፈርሞ ቀረ የተባለው ብቻ ታስሮ ቀርቦ እንዲመሰክር የተቀሩት ግን መጥተው ይመስክሩ በሚል ሌላ ቀጠሮ አንዳይሰጥ ስል እጠይቃለሁ”

አቃቤ ህግ በበኩሉ ከታህሳስ 25-27 የተያዘው ቀጠሮ ተከሳሾች እንዳሉት ጊዜ ካልበቃ ተብሎ ሳይሆን ምስክር የመሰሚያ ጊዜ መሆኑን እነደሚያውቅ፣ በባለፈው ቀጠሮ ታስረው ይቅረቡ የተባሉትን ምስክሮች ያልመጡበትን ምክንያት እንደማያውቅ ገልፆ በቀጣይ ቀጠሮ የቀሩትን 12 ምስክሮች እንዲያሰማ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

አቃቤ ህግ ቀሩኝ የሚላቸውን ምስክሮች ዝርዝር እና ምክንያት ዳኞች ጠይቀውት የሰጠ ሲሆን የሰጣቸው ዝርዝር ግልፅ አለመሆኑን የተዘበራረቀ ነገር መሆኑን ዳኞች ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ በባለፈው ቀጠሮ ታስሮ እንዲቀርብ የተባለውን ምስክር ዛሬ ለዳኞች ሲሰጥ መጥሪያ ተሰጥቶት በዛሬው ቀጠሮ እንዳልቀረበ ተገልፅዋል፡፡ በዚህም መሰረት ይህ ምስክር በድጋሚ ታስሮ እንዲቀርብ ነበር እንዲታዘዝለት ነው የጠየቀው፡፡ ይህን እና የመሳሰሉ ችግሮችን ዳኞች ለአቃቤህግ ነግረውት እሱም በተደጋጋሚ የሚጠይቁትን እያስተካከለ ለዳኞች ሰጥቷል፡፡ ዳኞች አቃቤ ህግ ጨርሶ ተገቢ ስራ እየሰራ እንዳልሆነ፤ ከታህሳስ 25-27 የተያዘው ቀጠሮም አቃቤ ህጉ እንደሚለው ምስክርነት ለመስማት የተያዘ ቀጠሮ ሳይሆን፡ ተከሳሾች እንዳሉት በዚህኛው ቀጠሮ ቀርበው ጊዜ ሳይበቃ ሲቀር እነሱን ለመስማት የተያዘ መሆኑን፣ ታስረው ይቅረቡ ለተባሉ ምስክሮች ድጋሚ መጥሪያ መስጠት ብሎ ነገር እንደሌለ ይህ ደግሞ ፍ/ቤቱን ትእዛዝ ካለማክበር የመነጨ መሆኑን ተናግረው አሰራሩን እንዲያስተካክል መክረውታል፡፡

ተከሳሾች ከጥርጣሬ ወጥተው እንዲያስቡ፤ በእውቀታቸው መጠን የትኛውንም አካል ሳይወግኑ ገለልተኛ እና ነፃ ሆነው እየሰሩ እንዳለ ዳኞች ተናግረዋል፡፡ ይህንም መዝገብ በተለየ አፅንኦት ሰጥተው እያዩት እንደሆነም አክለው ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የሚከተለውን ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

  1. በዛሬው እለት የተቀዳው የምስክሮች ቃል ከቀጣይ ቀጠሮ በፊት ተገልብጦ ከመዝገብ ጋር እንዲያያዝ
  2. በባለፈው ቀጠሮ ታስረው እንዲቀርቡ የተወሰነባቸው ምስክሮች በቀጣይ ቀጠሮ ለ24 ሰአት ታስረው እንዲቀርቡ፡ በዚህኛው ቀጠሮ ያልቀረቡበትን ምክንያትም እንዲገለፅ
  3. በዚህኛው ቀጠሮ መጥሪያ ደርሷቸው ያልቀረቡ ምስክሮች በቀጣይ ቀጠሮ ለ24 ሰአተ ታስረው እንዲቀርቡ
  4. በዛሬው ችሎት ከሰአት ይቀርባሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበረው ምስክርም 24 ሰአት ታስሮ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርብ
  5. በሰጡት አድራሻ ማግኘት ያልተቻሉ ምስክሮች፡ በተጠቀሰው አድራሻ የማይገኙ መሆናቸው ተጠቅሶ በአካባቢው ከሚገኝ አስተዳደር የተፃፈ ደብዳቤ እንዲቀርብ

ቀጣይ ቀጠሮ ከታህሳስ 25-27/2009 ተይዟል፡፡

 

Exit mobile version