በአዲስ አበባ 3.6 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ትራንስፎርመሮች የሰረቁ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታወቀ

Above Single Post

በአዲስ አበባ 3.6 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ትራንስፎርመሮች የሰረቁ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታወቀ

ADDIS ABABA POLICE FACEBOOK PAGE

(bbcamharic)—የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ባለፈው አንድ ወር ገደማ ሰባት ትራንስፎርመሮች እንደተሰረቁበት አስታወቀ። ትራንስፎርመሮቹ በተደራጀ ሁኔታ በቀን ጭምር መሰረቃቸውን የአገልግሎቱ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በየካ ክፍለ ከተማ የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም እየተባለ በሚታወቀው አካባቢ ወደ ዘጠኝ ትራንስፎርመሮች መሰረቃቸውን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፋንታ ናቸው።

በስርቆት ወንጀሉ ላይ የተሰማሩት አንዱ ሹፌር፣ ስልክ እንጨቱ ላይ ወጥቶ የሚፈታና ሌላ ይረዳ የነበረ ግለሰብ በአጠቃላይ ሦስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮማንደር ፋሲካው ገልጠዋል።

• ‘ከሕግ ውጪ’ የተዋሃዱት አምስቱ ክልሎች

ኮማንደር ፋሲካው እንዳሉት በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል አንዱ ለአስራ ሁለት ዓመት በመብራት ኃይል ውስጥ በቀን ሰራተኝነት ይሰራ የነበረ መሆኑ መታወቁን ተናግረዋል።

የአገልግሎቱ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተርም ወንጀሉ በባለሙያ ታግዞ ለመፈፀሙ ምንም ጥርጣሬ እንደሌላቸው ተናግረው፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል ከዚህ ቀደም የድርጅቱ ሰራተኛ የነበረ እንደሚገኝበት አረጋግጠዋል። አክለውም ግለሰቡ ከአስራ አምስት ቀን በፊት ሽቦ ሲሰርቅ ተይዞ በዋስትና መለቀቁን ገልጠዋል።

ትራንስፎርመሮቹ የተሰረቁባቸው አካባቢዎችንም ሲዘረዝሩ ወረገኑ አካባቢ፣ ገርጂ ማሪያም ቅጥር ግቢ ውስጥና መሪ ጎሮ ሚካኤል አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው መብራት በጠፋበት ባለፈው አንድ ወር ብቻ በምሥራቅ አዲስ አበባ ላይ ወንጀሉ መፈፀሙን ተናግረዋል።

• በኢትዮጵያ ካምፕ ውስጥ ባለ2 ፎቅ መኖሪያ የገነባው ስደተኛ

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ወንጀል ተከስሶ ጉዳዮ በፍርድ ቤት እየታየ የነበረና በዚህ መካከል ከመስሪያ ቤቱ የተባረረ ግለሰብ እንደሆነ የተናገሩት ኮማንደር ፋሲካው ግለሰቡ፣ ቀሪዎቹን ተጠርጣሪዎች ለተመሳሳይ ወንጀል በማነሳሳትና በማስተባበር ወንጀሉ ውስጥ መሳተፉን ገልጠዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ምርመራ ላይ ናቸው ያሉት ኮማንደር በሕብረተሰቡ ጥቆማና በፖሊስ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውንም አስረድተዋል።

ለስርቆቱ ትልቅ ክሬን በመከራየት ተጠቅመዋል ያሉት ደግሞ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ትራንስፎርመሩን እንዳለ አንስተው ሳይሆን የሚወስዱት ፈትተው ከውስጡ ያሉ ሽቦዎች፣ ጥቅሎችንና ኮፐሮችን እንደሆነ አስረድተዋል።

ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች እነማን ናቸው የሚለው በምርመራው ሂደት የሚታይ ነው የሚሆነው ያሉት ኮማንደር ፋሲካው ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ውስጥ አልፎ አልፎ ተመሳሳይ ስርቆት ይከሰት እንደነበር አስታውሰዋል።

• የማትተነፍሰው ከተማ: አዲስ አበባ

• የታገዱት ሞተረኞች እሮሮ እያሰሙ ነው

ወንጀሉ የሚፈፀመው በቀን የመብራት ኃይል ሰራተኛ የደንብ ልብስ ለብሰው መሆኑን የተናገሩት ኮማንደር ፋሲካው ማህበረሰቡ በነበረው ጥርጣሬ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

ሰርቀው ምን ያደርጋሉ? ለማን ይሻጣሉ? የሚለው ላይ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ገልጠዋል።

የአንድ ትራንስፎርመር አማካይ ዋጋው 400ሺህ የኢትዮጵያ ብር ነው ያሉት የኮሙኑኬሽን ዳይሬክተሩ ውድ የሚባለው 2.5 ሚሊዮን የሚያወጣ ትልቅ ትራንስፎርመር እንዳለም ተናግረዋል።