በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት በአሽከርካሪዎች ላይ ጫና መፍጠሩ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት በአሽከርካሪዎች ላይ ጫና መፍጠሩ ተገለጸ

(ena)—-አዲስ አበባ  ጥር 7/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት በአሽከርካሪዎች ላይ ጫና መፍጠሩን የታክሲና የባጃጅ አሽከርካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ያጋጠመውን ወቅታዊ የነዳጅ አቅርቦት ችግር በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት እንደሚፈታ አመልክቷል።

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎችና ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) አሽከርካሪዎች ከነዳጅ ማደያ ቤንዚን ለማግኘት በመቸገራቸው በእለት ኑሯቸው ላይ ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል።

የእለት ገቢ እያገኙ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ በመሆኑ ረጅም ሰዓት በነዳጅ ማደያ ተሰልፈው በማሳለፋቸው ገቢ እያገኙ እንዳልሆነ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በሰበታ ከተማ አስተዳደር ወለቴ ቴሌ ባጃጅ ማህበርን ወክለው የመጡት አቶ ተካልኝ ወልዴ እንደተናገሩት የነዳጅ ችግር በዚህ በሁለት ቀናት ጎልቶ ታይቷል፡፡

የነዳጅ ችግሩን ተከትሎ ስራቸውን በአግባብ መስራት እንዳልቻሉና መንግስት በተቻለ አቅም መፍትህ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ስዩም መኮንን የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌር በበኩላቸው ይህ የነዳጅ እጥረት በአገር ኢኮነሚ  በህብረተሰቡነና በታክሲ ሾፌሮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

ነዳጅ ፍለጋ ያልዙሩበት ቦታ እንደሌለ የተናገሩት አቶ ስዩም በፍለጋ ብቻ ህብረተሰቡን የሚያገለግሎበት ግዜ እንደባከነ አስታውቀዋል፡፡

በምዕራብ ጎንደርና በአፋር ክልል በተከስተ ችግር ሰሞኑን ያጋጠመው እጥረት በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ የሚፈታ መሆኑን የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማሪያም ለኢዜአ ገልጸዋል።

ችግሩ ተፈትቶ የነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ወደ መዲናዋ እየገቡ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በአገሪቱ በቂ መጠባበቂያ የነዳጅ ክምችት መኖሩን የገለጹት አቶ ታደሰ እንዲህ አይነት ወቅታዊ የሆነ እጥረት ሲያጋጥም ክምችቱ ጥቅም ላይ እንደማይውል ተናግረዋል።

ለመጠባበቂያነት የተያዘው ነዳጅ እጅግ ወሳኝ ለሆነ ጉዳይ የሚውል እንደሆነም ጠቁመው አሁን ያጋጠመው ጊዜያዊ የሆነ የቤንዚን እጥረት የሚፈታ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ጊዜያዊ የሆነ የነዳጅ እጥረት በማንኛውም አገር የሚያጋጥም በመሆኑ ህብረተሰቡ በትዕግስት በመጠበቅ ለማግኘት መንቀሳቀስ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

”እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ለባለታክሲዎችና ለባለባጃጆች ቅድሚያ መሰጠት ቢለመድ መልካም ነው” ያሉት አቶ ታደሰ በሁለትና በሶስት ቀን የሚፈታን ችግር ህብረተሰቡ እንደ ትልቅ ችግር ማሰብና መረበሽ እንደሌለበት አስረድተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነዳጅ አቅርቦት ላይ በሚፈጠር ሰው ሰራሽ ችግር የተነሳ እጥረት እየተከሰተ ይገኛል።

መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ተገልጿል።

በየቦታው በህገ ወጥ መንገድ ነዳጅ የሚሸጡ አካላትና ነዳጅ የሚያሸሹ ህገወጦች ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትብብር እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሚገኝም አቶ ታደሰ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በየአመቱ ወደ አገር ውስጥ ለምታስገባው የነዳጅ ምርት 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ትከፍላለች።