በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ ሹም ሽር ሊካሄድ ነው::

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ ሹም ሽር ሊካሄድ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ ሹም ሽር ሊካሄድ ነው

(ethiopianreporter)——በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን እንዲሆኑ የተሰየሙት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የካቢኔ አባላት ሹም ሽር ሊያካሂዱ መሆኑ ተሰማ፡፡ ከካቢኔ ሹም ሽር በተጨማሪ ከመጠን በላይ በመስፋታቸው ምክንያት ለአሠራር አላመቹም የተባሉ መሥሪያ ቤቶች ይታጠፋሉ ተብሏል፡፡

ከፌዴራል መንግሥትና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ አመራሮች፣ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ የካቢኔ አባል ሆነው የሚሠሩ ተሿሚዎች እየመለመሉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 34 የካቢኔ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአዲስ አመራር ይተካሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው የከተማውን ቁልፍ ከአቶ ድሪባ ኩማ በተቀበሉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካና የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ብትሆንም ነዋሪዎቿ የሚገባቸውን አገልግሎት ከማቅረብ አንፃር ብዙ ይቀራታል፡፡

‹‹መዲናችን አዲስ አበባ አካታችና ዘመናዊነትን የተላበሰች እንድትሆን ለማድረግ ብቁና አገልጋይ አመራር፣ እንዲሁም ብቃት ያለው አደረጃጀት ያስፈልጋታል፤›› ሲሉ ለውጥ እንደሚኖር አመላክተው ነበር፡፡

ከዚህ በመነሳት ከቀድሞዎቹ ከንቲባዎች አቶ ኩማ ደመቅሳና በቅርቡ አምባሳደር ሆነው በተሾሙት አቶ ድሪባ ኩማ አመራር ዘመን ወደ ከተማው የመጡ አመራሮችን በአዲስ የመተካት ዕቅድ ተይዟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ቢሮ፣ በአንድ ባለሥልጣንና በአንድ ኤጀንሲ ሥር በርካታ ራሳቸውን የቻሉ ክፍሎች የሚገኙ በመሆናቸው፣ ይህም ለሥራ አመቺ መሆን ባለመቻሉ የተወሰኑት በድጋሚ ይታጠፋሉ ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ የመንገድ አውታሮችና የትራንስፖርት ሥምሪት ከፍተኛ የነዋሪዎች ምሬት የሚነሳባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳደርና የቆሻሻ አወጋገድ ችግሮች ኅብረተሰብን የሚያስመርሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ትንበያ በ2009 ዓ.ም. የከተማው ሕዝብ ቁጥር ከ3.43 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ቢገለጽም፣ በየጊዜው በፍልሰት ወደ ከተማው የሚመጣው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ከፍተኛ የአገልግሎት አቅርቦት ችግር እያጋጣመ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚሁ ጋር በተለይ የመሠረተ ልማት ተቋማት የመናበብ ችግር ያለባቸው በመሆኑ፣ አንዱ ሌላው የሠራውን የሚያፈርስ ስለሆነ ከተማው በዓመት ሦስት ቢሊዮን ብር እንደሚያጣ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ብዙ ሥራዎች የሚጠብቀው የምክትል ከንቲባ ታከለ አስተዳደር በቅርቡ የካቢኔ አባላት ሹም ሽር በማካሄድ፣ በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡