የሪፖርተር ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት፣ ከኦሮሚያ ክልልና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጣና በከፍተኛ የመንግሥት አመራር የሚመራ ቡድን ተቋቁሞ አስተዳደራዊ ወሰኑን ሲያጠና ቆይቷል፡፡ በዚህ መሠረት የወሰን ማካለል ኮሚቴው ጥናቱን ያጠናቀቀ በመሆኑ፣ በቅርቡ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ እንደሚፀድቅ ታውቋል፡፡ ይህ አስተዳደራዊ ወሰን አዲስ አበባ ወደ ጎን የማደግ ዕድሏን ሊያጠብ የሚችል ነው፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ኦሮሚያ ክልል ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ጋር በነበረው የአስተዳደራዊ ወሰን ግጭት ምክንያት በሁለቱ ወገኖች መካከል የሰው ሕይወትና ንብረት መውደሙ ይታወሳል፡፡ የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አረጋ ዓርብ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከወራት በፊት በሁለቱ ክልሎች መካከል በተደረሰው አስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ስምምነት መሠረት ከኦሮሚያ ክልል ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በመወሰድ ታስረው የነበሩ 600 ሰዎችን ማስመለስ ተችሏል፡፡

እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ኦሮሚያ ክልል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ ታስረው የነበሩ ዜጎችን ከማስፈታት በተጨማሪ፣ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ሰላማዊ ኑሮ መኖር ጀምረዋል፡፡

ኦሮሚያ ክልል ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር ባለው የድንበር ውዝግብም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡ ከሁለቱ ክልሎች በተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮችና በአገር ሽማግሌዎች አማካይነት የወሰን ማካለል ሥራው አሁን እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል ባሉ ሁለት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 18 ቀበሌዎችና 71 የግጭት ቦታዎች ላይ እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከጋምቤላ ክልል ጋር ባለው የወሰን ግጭት ሳቢያም፣ በአሁኑ ወቅት የግጭት መንስዔ የሆኑ ስምንት ቀበሌዎች ተለይተው አስተዳደራዊ ወሰኑ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አቶ አዲስ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ኦሮሚያ ክልል ከድሬዳዋና ከሐረሪ ክልሎች ጋር የሚዋሰን በመሆኑና በእነዚህ አካባቢዎች እስካሁን ግጭቶች ባይኖሩም፣ ወደፊት ሰላሙ የተረጋገጠ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት ጠንክሮ እየሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በቅርብ ወደ አመራር የመጣው የኦሮሚያ ክልል አዲሱ ካቢኔ ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ጋር ያለውን አስተዳደራዊ ወሰን ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር በተለየ ሁኔታ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው አዲሱ የኦሮሚያ ክልል፣ ክልሉን ከሚያዋስኑት ክልሎች ጋር ብቻም ሳይሆን ከአጎራባች አገሮች ጋር ያለውን የድንበር ችግር ለመፍታትም ጥረት እያደረገ መሆኑ ይነገራል፡፡ በቅርቡ አቶ ለማ ከኬንያ ጋር ያለውን ድንበር ማካለል በተመለከተና በሁለቱ አጎራባች አገሮች መካከል የሚፈጠረውን ግጭት በሚፈታበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ከፌዴራል መንግሥት የልዑካን ቡድን ጋር ወደ ኬንያ አቅንተው እንደነበር ይታወሳል፡፡