በነ ኡርጌሳ አያኖ የክስ መዝገብ ዐቃቤ ህግ ለሁለተኛ ቀን ምስክር አሰምቷል፡፡

15202630_1206908136012520_6553086052460271744_n

(በነ ኡርጌሳ አያኖ የክስ መዝገብ ዐቃቤ ህግ ለሁለተኛ ቀን ምስክር አሰምቷል፡፡

በነ ኡርጌሳ አያኖ የክስ መዝገብ የፈዴራል አቃቤ ህግ በ20ኛ ተከሳሽ አብዲ ታምራት ደሲሳ ላይ ያስረዱልኛል ብሎ ካቀረባቸው ሁለት ምስክሮች መካከል አንዱን በዛሬው ዕለት አስመስክሯል፡፡ ችሎቱ የተሰየመው በ18ኛ ችሎት አዳራሽ ከጠዋቱ 3፡30 ሲሆን እስከ 4፡30 አከባቢ ሌሎች የክስ መዝገቦችን ሲሰማ ቆይቶ ወደ እነኡርጌሳ አያኖ የክስ መዝገብ ተሸጋግሯል፡፡

የሀያኛው ተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንድሙ… እስከ 4፡50 ድረስ ተጠብቀው አለመቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ ሲገልጽ ከ1ኛ-4ኛ ተከሳሾች ጠበቃ የሆኑት አቶ አመሐ መኮንን እና አቶ አባጆቢር ተከሳሹ ፍቃደኛ ከሆኑ በእነርሱ በኩል የሙያ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ፍቀደኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የተከሳሹን ይሁንታ ጠይቆ ፍቀደኛ መሆኑን ስላረጋገጠ ጠበቆቹ ተከሳሹን ወክለው ቀርበዋል፡፡

የፌ/ዐ/ህግ ሀያኛ ተከሳሽ በሆኑት አቶ አብዲ ታምራት ደሲሳ ላይ በፌስቡክ ገጻቸው የለጠፏቸው ጽሑፎች እና ምስሎች እንዲሁም የተለዋወጧቸው መልዕክቶች ታትመው ሲውጡ የተመለከቱ በክስ መዝገቡ ማስረጃ ቁጥር 14 የሰፈሩ የሰነድ ማስረጃዎችን ያስረዱልኛል ያላቸውን በ24ኛ እና 25ኛ ተራ ቁጥር የተመዘገቡ ሁለት ታዛቢ ምስክሮች እንዳቀረበ የገለጸ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በጉለሌ ክ/ከተማ ትራንስፖርት እና መገናኛ ዘርፍ የተሰማሩት የ38 ዓመቱ አቶ አብርሃ ወልዴን ለምስክርነት ጠርቷል፡፡

ምስክሩ ከቀረቡ በኃላ ቃለ መሃላ ሳይፈጽሙ በቀጥታ የገቡ ቢሆንም በተከሳሽ ጠበቆች አሳሳቢነት ፍርድ ቤቱ ወደኋላ ተመልሶ ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ አድርጓል፡፡ በመቀጠል ምስክሩ ተከሳሹን ከተከሳሾች መካከል ለይተው ለፍርድ ቤቱ እንዲያሳዩ ጠይቋል፡፡ ምስክሩ ከምስክር ሳጥን ወርደው የተከሳሾች ገጽን በቅርብ ቢመለከቱም ተከሳሹን ካየኋቸው አንድ አመት አከባቢ ስለሆናቸው ለመለየት እንደቸገራቸው ለፍርድ ቤት ገልጸዋል፡፡ በመቀጠል ምስክር ዐቃቤ ህግ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ተከሳሹን የሚያውቋቸው በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ቢሮ ቁጥር 31 ሲሆን በዚያው ቀን ከሌላኛው ተዛቢ ምስክር ጋር ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘረፍ አከባቢ በሚገኘው ቢሮቸው አከባቢ በሚገኝ መንገድ ላይ ቆመው ሳለ መረጃ ሲወጣ እንዲታዘቡ በፖሊስ ተጠይቀው ወደምርመራ ዘርፉ እንደመጡ ከ30-40 ደቂቃ የሚደርስ ጊዜ በዚያ እንዳሳለፉ ተከሳሹን ከጥር 24/2008 ዓ.ም. በፊትም ሆነ በኋላ አግኝተዋቸው እንደማያቁ መልሰዋል፡፡

በመቀጠል ከኮምፕዩተር ታትመው ስለወጡት መረጃዎች በዝርዝር እንዲያስረዱ ሲጠየቁ የኦነግ ባንዲራ ያለበት ምስል እና ወደ አርባ ገጽ የሚደርሱ የተለያዩ የተለጠፉ ጽሑፎች እና ከተለያዩ ግለሰቦች የተላላኳቸው መልዕክቶች ከተከሳሽ ፌስቡክ ገጽ ሲወጡ እንደተመለከቱ ገልጸዋል፡፡ የጽሑፎችን ይዘት እንደማያስታውሱ ለፍርድ ቤቱ ግልጸው በዕለቱ ግን በአስተርጓሚ አማካኝነት ይዘቱ እንደተነገራቸው አስረድተዋለው፡፡ ተከሳሹም በዕለቱ የተረጋጋ እንደነበር ገልጸው ታትመው በወጡት ሰነዶች ላይ ተከሳሹ “ከእኔ የፌስቡክ አካውንት የተገኘ” ብለው ከፈረሙ በኋላ እርሳቸው እና ሌላኛው ታዛቢ እንደፈረሙ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም በዐቃቤ ህግ ጥያቄ ጥያቄ መሰረት ተከሳሹን የሚመለከቱት ሰነዶች ከሌሎች ሰነዶች መካከል ለይተው ለፍርድ ቤቱ አሳይተዋል፡፡
በመቀጠል የተከሳሽ ጠበቆች ለምስክሩ መስቀለኛ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በሌሎች የክስ መዝገቦች መመስከራቸውን የገለጹት ምስክሩ በዛሬው ዕለት እየታየ ያለው የክስ መዝገብ በጥር 24/2008 ዓ.ም የታዙበት ሰነድ መሆኑን ተከሳሹን በአካል ባለዩበት ሁኔታ እንዴት መለየት እንደቻሉ ተጠይቀው መልስ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ በወቅቱ ተከሳሹ በምን ቋንቋ ከመርማሪው ፖሊስ ጋር ይነጋገሩ እንደነበር ተጠይቀው ተከሳሹ ትንሽ ትንሽ አማርኛ መናገር ስለሚችሉ በዚያው ቋንቋ እንደተግባቡ ገልጸዋል፡፡ በአስተርጓሚነት ስለሰነዶቹ ምንነት ለታዛቢዎቹ ያስረዱት ሰው ከዚያው ከፖሊስ ጣቢያ የመጡ ሰው መሆናቸውን ተናግረው የደንብ ልብስ መልበስ አለመልበሳቸውን እንደማያስታውሱ ገልጸዋል፡፡ ጽሑፎቹ በላቲን ፊደል መጻፋቸውን ገልጸው አስተርጓሚው አማካኝነት ይዘቱ እንደተነገራቸው ሲገልጹ አርባ ገጽ ሙሉ ሰነድ ነው ተነቦ የተተረጎመሎት ተብለው ሲጠየቁ ቀጥታ መልስ መስጠት አልቻሉም፡፡ በአስተርጓሚው አማካኝነት ስለተነገራቸው የጽሑፎች ይዘት ለፍርድ ቤቱ የሚያስተውሱትን እንዲናገሩ ሲጠየቁ ስለመስሎቹ ደጋግሞ ከማውራት በቀር ስለይዘቱ ማስረዳት አልቻሉም፡፡

በተጨማሪም ተከሳሹ ከየት እንደመጣ እና ሰነዱ ሲወጣ ምንም ተጽእኖ እንዳልተደረገበት ንብረትነቱ የፖሊስ የሆነውን ኮምፒዩተር መርማሪው ገመዶች እንደሰካለት፣ ተከሳሽ በራሱ እጅ ኮምፕዩተሩን አብርቶ የፌስቡክ ገጹ ላይ ማለፊያ ቃል በማስገባት ከፍቶ ሰነዶቹን ወደ ወረቀት እንዳተመ ገልጸው ከዚያ ሰዓት በፊትም ሆነ በኋላ በተጽእኖ ውስጥ ማለፍ አለማለፉን እንዳማያውቁ ተናግረዋል፡፡ አስርጓሚው ለመተርጎም ብቻ እንደመጣ ተጠይቀው ሲመልሱ አለማወቃቸውን ተናግረው የኦሮሚኛ የቋንቋ ችሎታውን መጠን ቋንቋውን ስለማየውቁ ማረጋገጥ እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡

ዐቃቤ ህግ በማጣሪያ ጥያቄ አስተርጓሚው ወደቢሮ ቁጥር 31 የመጣው ለምንድን እንደሆነ ሲጠይቅ የሰነዱን ምንነት ዕውቀት እንዲኖረን ለማስረዳት እንጂ ከፊርማው ጋር የማይያያዝ ነው ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በማጣሪያ ጥያቄው ከሌላ ክፍል በገመድ አልባ የኮምፒዩተር ኔትወርክ ፕሪነተር የሚታዘዝበት ዘዴ እንዳለ ግንዛቤ እንዳላቸው ምስክሩን ጠይቆ ሲያበቃ ይህኛው ሰነድ በዚህ መንገድ መገኘቱን አለመገኙተን እንዳረጋገጡ ሲጠይቅ አለማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሌላ የማጣሪያ ጥያቄው ምስክሩ በዕለቱ ማስታወሻ መያዛቸውን ከጠየቀ በኋላ በዚህ ማስታወሻቸው ላይ ካሰፈሩት መካከል ምን ምን እንደሚያስታውሱ ሲጠይቅ ምስክሩ የተከሳሹን ስም፣ ባርነት ይብቃ፣ እምቢ ለነጻነት የሚሉትን እና ከአቶ ሳምሶን ከተባለ ሰው ጋር መልዕክት ማስተላለፋቸውን እንደሚያስታውሱ ተናግረዋል፡፡ ዐቃቤ ህግ ሁለተኛው ምስክር ተመሳሳይ ጭብጥ የሚመሰክሩ መሆኑን ገልጾ አንዲቀርለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ተቀብሎ የምስክሮች ቃል ወደ ጽሑፍ እንዲገለበጥ፣ ለአስተርጓሚ እንዲከፈል እና ተጨማሪ ምስክሮችን ለማድመጥ ህዳር 24/2008 ዓ.ም. ቀጠሮ በመያዝ ችሎቱን ዘግቷል፡፡

Via: Ethiopia Human Rights Project/FB