በቤንሻንጉል ክልል ካማሼ ዞን በሚገኙ 5 ወረዳዎች የመንግስት ሥራ ከተቋረጠ ሁለት ወር እንዳለፈው ተገለፀ

በቤንሻንጉል ክልል ካማሼ ዞን በሚገኙ 5 ወረዳዎች የመንግስት ሥራ ከተቋረጠ ሁለት ወር እንዳለፈው ተገለፀ

(bbc)–በቤንሻንጉል ክልላዊ መንግሥት በካማሼ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በነበረው ግጭት ምክንያት ላለፉት ሁለት ወራት የመንግሥት ስራ በመስተጓጎሉ ሰራተኞች ደመወዝ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም መሰረታዊ አገልግሎቶችንም እያገኙ አለመሆኑን ከክልሉ ኃላፊዎች ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በካማሼ ዞን ስር በሚገኙ አምስት ወረዳዎች፣ ከአሶሳ ዞን ደግሞ ኦዳ ወረዳ እንዲሁም ማኦ ኮሞ ወረዳዎች የመድሃኒት አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸው የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐብታሙ ታዬ ለቢቢሲ ገለፀዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ በካማሼ ዞን 69 ቀበሌዎች ያሉ ሲሆን በሁሉም ቀበሌዎች የጤና ኬላዎች አሉ፤ በተጨማሪ ደግሞ 8 ጤና ጣቢያዎች ቢኖሩም በአሁኑ ሰዓት ሁሉም የመድሀኒት አቅርቦት ችግር ገጥሟቸዋል።

• የካማሼ ዞን አመራሮች በታጣቂዎች ተገደሉ

• በነቀምት የሚገኝ አንድ ቤተሰብ ለ1000 ተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረገ ነው

• የካማሼ ዞን ተፈናቃዮች አሁንም ስጋት ላይ እንደሆኑ ገለፁ

በዞኑ የሚኙ ወረዳዎች ቆላማ በመሆናቸው ምክንያት የወባ ስርጭት እንዳለ ያስታወሱት ኃላፊው ፤በተለይ በሶስት ወረዳዎች ላይ በአንድ ሳምንት ብቻ ከ600 ሰዎች በላይ በወባ ታምመው ወደ ጤና ኬላዎች መምጣታቸውን መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።

ካማሼ ዞን ውስጥ ትልቅ ሆስፒታል የለም ያሉት ኃላፊው እስከ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው ህክምና ሲኖር ከዚህ በፊት ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎች በመሄድ ህክምና እንዲያገኙ ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን በፀጥታው ምክንያት የተሻለ ህክምና የሚያስፈልጋቸው እናቶች ወደ ኦሮሚያ ሄደው መታከም ባለመቻላቸው አምስት እናቶች በዞኑ በህክምና እጦት ምክንያት መሞታቸውን መረጃ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጤና ቢሮ ኃላፊ እንደሚሉት ከሆነ በካማሼ ዞን በነበረው ግጭት ምክንያት በዞኑ ስር ከሚገኙ አምስቱም ወረዳዎች የለቀቁ ባለሙያዎችም አሉ።

ከዚህ በፊት ወደ ካማሼ ዞን መድሃኒት ይደርስ የነበረው ከነቀምት ወይንም ከአሶሳ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ሰዓት ወደ ካማሼ ዞን የሚወስዱት ሁለቱም መንገዶች በፀጥታ ችግር ምክንያት በመዘጋታቸው መድሃኒት ማቅረብም ሆነ የተሻለ ህክምና የሚፈልጉ ሰዎችን ወደ አጎራባች ክልል የሕክምና ተቋማት መውሰድ አልተቻለም ብለዋል።

አልፎ አልፎ በክልሉ በምትንቀሳቀሰው ሄሊኮፕተር መድሃኒት ለመላክ መሞከራቸውን የተናገሩት የጤና ቢሮ ኃላፊው በአሁኑ ሰአት ግን በወባ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እጨመረ መሆኑንና የወባ መድሃኒትም አለመኖሩ ስጋታቸውን ጨምሮታል።

በዞኑ የሚሰሩ የጤና ቢሮ ሰራተኞች ደሞዝ ከተከፈላቸው ሁለት ወር እንዳለፋቸውም ጨምረው አስረድተዋል።

የግብርናና የእንስሳት ኃብት ኃላፊ የሆኑት አቶ አባበክር ሐሊፋ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት የግብርና ባለሙያዎች በማህበረሰቡ ውስጥ በነፃነት መንቀሳቀስ እና መስራት አልቻሉም ብለዋል። ባለሙያ ቀበሌ ላይ የለም የሚሉት ኃላፊው ደሞዝም ባንክ የገንዘብ እጥረት ስለገጠመው መክፈል አለመቻላቸውን አስረድተዋል።

ወደ አሶሳ ከተማ ተፈናቅለው የመጡ ባለሙያዎች እንዳሉ ያስረዱት ኃላፊው ሁሉም ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወደ ህዝቡ መሄድ የነበረባቸው ነገሮችም እንዳልደረሱ የሚያስረዱት ኃላፊው “በአሁኑ ሰዓት መሰብሰብ የነበረበት እህል መሰብሰብ አልተቻለም፣ የሰሊጥ ምርቱም ዝም ብሎ ማሳ ላይ ባክኖ ቀርቷል” ይላሉ።

በዞኑ የነበሩ የምርጥ ዘር ስራዎች በፌደራል፣ በክልሉና ባለሀብቶች የሚሰሩ ስራዎች ባክነው መቅረታቸውን ተናግረዋል። ወደ ዞኑ መሄድ ስለማይቻልም የተፈጠረውንና ያለውን ችግር ለመፍታት አለመቻላቸውን አስረድተዋል።

የግብርና ኃላፊው በካማሼ ዞን ጋር ከተቆራረጡ ሁለት ወር እንደሆናቸው አስረድተው ከማኦ ኮሞ ወረዳ ጋርም ከተገናኙ ስድስት ወር እንዳለፋቸው ተናግረዋል።

ወረዳው 32 ቀበሌዎች ያሉት ሲሆን እስከ ትናንትና ድረስ ቀበሌ ውስጥ መንቀሳቀስ አደገኛ ነው የሚሉት ኃላፊው ወደ ድንበር አካባቢ የምትገኝ ላቂ የምትባል ቀበሌ በዝናብ እጥረት ምክንያት 960 ሰዎች ተፈናቀለው ወደ ማኦ ኮሞ ከተማ መምጣታቸውን መስማታቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ የሰው ሀብት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ሐሸሪፍ ሀጅ አኑር ደግሞ የካማሼ ዞን አምስት ወረዳዎች እንዳሉት አስታውሰው ከእነዚህ ወረዳዎች አራቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ አለመግባታቸውን ገልፀዋል።

ሰዳል የሚባለው ወረዳ ከመጀመሪያውም ግጭት ስላልነበረበት የመንግስት ስራ በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። የመንግስት ስራ በተቋረጠባቸው ስፍራዎች ትምህርትም መስተጓጎሉን ገልፀው ማኦ ኮሞ ላይ ከካማሼ ዞን አንፃር የተሻለ ሁኔታ አለ በማለት አስረድተዋል።

የቤንሻንጉል ክልል የኮሙዩኑኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘላለም ጃለታ በበኩላቸው ካማሼ ዞን ያለውን ችግር ለመፍታት የክልሉ አስተዳደር ከኦሮሚያ አመራሮች ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን ነግረውናል።