በሶማሌ ክልል የነዳጅ ማውጫ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ያልተለመደ የጤና ችግር እየገጠመን ነው ይላሉ

ሶማሌ ክልል የነዳጅ ማውጫ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ያልተለመደ የጤና ችግር እየገጠመን ነው ይላሉ

(bbcamharicnews)–በሶማሌ ክልል አንድ የቻይና ድርጅት የነዳጅ ቁፋሮ በሚያካሂድበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምንነቱ በግልፅ ላልታወቀ የጤና እክል እየተጋለጡ መሆኑን ከቀናት በፊት ዘጋርዲያን ዘግቧል።

በቆራሄይ ዞን፤ ሽላቦ እና ደቦ ወይን በተባሉ አካባቢዎች ችግሩ እንደተስተዋለም ተገልጿል። ምንነቱ ያልታወቀው ይህ በሽታ በስፋት ተሠራጭቶበታል በተባለው አካባቢ ደቦ ወይን ተወልዶ ያደገው የ27 ዓመቱ አህመድ መሐመድ ችግሩ መታየት የጀመረው ከስድስት ዓመታት በፊት ነው ይላል።

• “ልዩ ነዳጅ መኖሩን አልደረስንበትም” የማዕድን፣ የፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

• አሜሪካ ከህዳሴ ግድብ አደራዳሪነት እንድትወጣ የሚጠይቀው የዋሽንግተን ዲሲ ሰልፍ

“አንድ ሰው ለሳምንት ሊታመም ይችላል። ዓይኑ ቢጫ ይሆናል። ከተወሰነ ቀን በኋላ ወደ ሆስፒታል ሲሄድ ካንሰር ይዞታል ወይም ምን እንደታመመ አልታወቀም ሊባል ይችላል” ሲል ሁኔታው ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ይገልፃል።

በ1997 ዓ.ም 14 ወጣት ወንዶች በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሞታቸውን አስታውሳለሁ የሚለው አህመድ፤ የሟቾቹ ዕድሜ ከ14 እስከ 20 ዓመት እንደሚሆንም ይናገራል።

አህመድ እንደሚለው በሽታው የያዘው ሰው ከእንቅልፉ ሲነሳ መስማት ሊያቆም ይችላል። እስከዚህ ድረስ ከባድ ነው።

“ከ25 በላይ አረጋውያን በካንሰር ሞተዋል። አጎቴ ጅግጅጋ እና አዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች እየታከመ ነበር። ሐኪሞች አይተርፍም ስላሉ ወደ ደቦ ወይን ተመልሷል” ሲልም በራሱ ቤተሰብ ላይ የደረሰውን የጤና ቀውስ ያስረዳል።

ሆስፒታል ቢሄዱም በሽታው ምን እንደሆነ እንደማይታወቅ ነው የሚነገረን ይላል።

“ታላቅ እህቴ እጅና እግር የሌለው የማይናገር ልጅ ነው የወለደችው። እሷ ብቻ ሳትሆን በዚህ አካባቢ በርካታ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ተከስተዋል። ታናሽ ወንድሜ ላለፉት አምስት ወራት ታሞ ነበር። ኩላሊቱ ተጎድቷል” ሲል ለተሻለ ሕክምና ወደ ህንድ ሊወስዱት እያሰቡ እንደሆነ ይገልፃል።

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚደንት አብዲ መሐመድ ኡመር [አብዲ ኢሌ] ሥልጣን ላይ ሳሉ ለክልልም ሆነ ለፌደራል መንግሥት ስለምንም ጉዳይ ቅሬታ ማቅረብ አይቻልም ነበር የሚለው አህመድ፤ ስለመብቱ የሚጠይቅ ሰው ይታሰር እንደነበርም ያስታውሳል።

“በዚህ ነዳጅ በሚወጣበት አካባቢም የቻይናው ድርጅት እና የኢትዮጵያ ወታደሮች ከተወሰነ አካባቢ ማለፍ አይቻልም ብለዋል። ከዚያ ያለፈ ሊገደል ይችላል” ሲል በወቅቱ የከፋ ሁኔታ እንደነበር ይናገራል።

ችግራቸው ሳይፈታ ብቻ ሳይሆን ሳይናገሩ ዓመታትን መግፋታቸውን ያወሳል።

“አሁን ሙስጠፋ ሥልጣን ሲይዝ ስለችግሩ መናገር ብንችልም፤ ምንም ምላሽ ግን አልተሰጠንም። ካምፓኒው በደረቅ ወቅት እንደ አፈር ወይም ስኳር ያለ ነጭ ነገር ይደፋል። ዝናብ ሲመጣ ይሄ ነጭ ነገር ወደ ወንዝ ይገባል። ሰዎች ውሀውን ሲጠጡ በሽታው ይይዛቸዋል። የአገር ሽማግሌዎች ወደ ሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንት ሄደው ስለ በሽታው ተናግረዋል። ግን ምንም ምላሽ አላገኙም” ሲል ቅሬታውን ያሰማል።

ሌላኛዋ ያነጋገርናት የአካባቢው ነዋሪ ፈርዶሳ አብዱላሂም ተመሳሳይ ነገር ነው ለቢቢሲ የተናገረችው። ፍርዶሳ የ36 ዓመት ጎልማሳ ስትሆን የ7 ልጆች እናት ናት።

“በሽታው በጣም እየጎዳን ነው፤ ልጆችና ወጣቶችም ይያዛሉ። በበሽታው የተያዘ ሰው ያተኩሰዋል፣ ፊቱ ያብጣል፣ ወዲያው ይሞታል። ትላንት አብሮሽ የነበረ ጓደኛሽ ወይም ጎረቤትሽ ዛሬ ሊታመም ይችላል። በበሽታው ሳቢያ ማየት የተሳናቸው እና የአእምሮ በሽታ የያዛቸው ልጆችም አሉ” በማለት በእሷ ቤተሰብ ላይ ግን ምንም እንዳላጋጠመ ገልጻለች።

“ነገር ግን የታመሙ ዘመዶች ግን አሉኝ። በበሽታው ከተያዘ ሰው የሚተርፈው ጥቂቱ ብቻ ነው። የሚሞተውን ሰው መቁጠር ያዳግተኛል” ስትል በሽታው ከነዳጅ አውጪ ድርጅቱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ እምነት እንዳላት ለቢቢሲ ተናግራለች።

• በናይጄሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ተገኘ

• “ዘራፊው ለሕዝብ ጥቅም እየተባለ ክሱ እንዲነሳ ከተደረገ ውርደቱ ለአቃቤ ሕግ ነው” አቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤል

ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የሶማሌ ክልል የጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር የሱፍ መሐመድ፤ እስካሁን በእነሱ በኩል ከነዳጅ ማውጣት ሂደቱ ጋር በተያያዘ ምክንያት የታመመ ወይም ሕይወቱ ያለፈ ሰው ስለመኖሩ የተረጋገጠ መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ይህንኑ ለማጣራት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመነጋገር ከተለያየ ዘርፍ የተውጣጡ ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው እንደሚያመሩም ዶ/ር የሱፍ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ወደ ሥፍራው የሚላኩ ባለሙያዎች የራሳቸውን ምርመራ አድርገው ካልመጡ በስተቀር እስካሁን በራሳቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለም ገልፀውልናል።

“እዚያ አካባቢ ካሉ ጤና ጣቢያዎች፣ ሆስፒታሎች እና ከወረዳዎች በየጊዜው ሪፖርት ይደርሰናል፤ ነገር ግን እስካሁን በአካባቢው የተከሰተ አዲስ ነገር የለም” ብለዋል ዶክተር የሱፍ።

ምንም እንኳን ሰዎች እየታመሙ ወደ ጤና ተቋማት ቢሄዱም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ያጋጠመ የጤና ቀውስ የለም ሲሉ ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የማኅበረሰቡ የሕይወት ዘይቤ በመለወጡ ምክንያት እንደ ወባ፣ ቲቢ፣ የሳንባ ምች፣ የካንሰር በሽታዎች፣ የምግብ እጥረቶች እና ሌሎች የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ መምጣታቸውን የሚጠቅሱት ዶ/ር የሱፍ፤ ይህ ግን ከሌላው አካባቢ ጎልቶ የሚታይ አይደለም ይላሉ።

“የእነዚህ በሽታዎች መስፋፋት ከነዳጅ ማውጣት ሥራው ጋር ይገናኛል፤ አይገናኝም የሚለው ጉዳይ ቡድኑ ወደ ሥፍራው አቅንቶ ጥናት አድርጎ ከመጣ በኋላ ነው የሚታወቀው” ብለዋል። አክለውም ከዚህ በፊት በቦታዎቹ እንደዚህ ዓይነት ክስተት አጋጥሞ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

ዶ/ር የሱፍ “በነዳጅ ማውጫው አካባቢ የሚጠቀሙት ኬሚካሎች አሉ። በትንሹ ሰልፈሪክ አሲድ ይጠቀማሉ። ታዲያ ይህንን ኬሚካል የሚያጓጉዙበትን ጀሪካኖች እያነሱ ለውሃ መቅጃ የሚጠቀሙ ሰዎች አሉ። ይህ የሚያመጣው የጤና ጉዳት አለ። አካባቢው የታጠረ ቢሆንም ከቦታው የሚወጣ ፍሳሽ ሳሮችንና ሌሎች እፅዋቶችን ያጠፋል” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ጠቅሰዋል።

በዚህ የተነሳ እዚያ አካባቢ ባለው የአካባቢ ለውጥ ምክንያትም አብዛኛው አርብቶ አደር ተጎጂ ይሆናል። ይህም የምግብ እጥረት በሽታ ከፍ እንዲል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አብራርተዋል።

በፌደራል በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ እየተሠራ ቢሆንም፤ ነዳጅ አውጪ ድርጅቱ ግን ይህን ተግባራዊ እያደረገ ነው? የሚለውና አስከተለ የተባለውን ጉዳት ማወቅ የሚቻለው ጥናቱ ከተካሄደ በኋላ መሆኑን ዶ/ር የሱፍ አስረድተዋል።

የጤና ቀውሱ እንደተከሰተ በተወራባቸው እና ለነዳጅ ጉድጓዶቹ ቅርበት ባላቸው በቆራሄይ ዞን፣ ሽላቦ፣ ደቦ ወይን እና ጎዴ አዋሳኝ ቦታዎች በቋሚነት የሚኖሩና አርብቶ አደሮች [ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ] ማኅበረሰቦች ይገኛሉ።