“በምዕራብ አትዮጵያ ‹‹ ደፈረሰ›› የተባለዉን ሠላም ለማጥለል የተቋቋመዉ ‹‹ኮማንድ ፖስት›› ( ከእነ ስሙም አያምርም) ሰሞኑን ስለተቀዳጃቸዉ ድሎች መግለጫ ሰጥቷል፡፡

By Befekadu Moreda:“በምዕራብ አትዮጵያ ‹‹ ደፈረሰ›› የተባለዉን ሠላም ለማጥለል የተቋቋመዉ ‹‹ኮማንድ ፖስት›› ( ከእነ ስሙም አያምርም) ሰሞኑን ስለተቀዳጃቸዉ ድሎች መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በተለይ በወለጋ አካባቢ ‹‹አገኘሁ›› ላለዉ ድል‹‹እንኳን በለስ ቀናህ›› ለማለት የሚያስዳዳ ዜና አድርሶናል፡፡

835 የታጠቀ ሰዉ ትጥቅ ማስፈታቱ ነዉ የተዘገበዉ፡፡ በሌላ አባባል 835 ታጣቂ መማረኩን ነዉ የሚነግረን፡፡ልዩ ትርጉም ካልተሰጠዉ በስተቀር፡፡ 835 ታጣቂ ቢያንስ ሁለት ሻለቃ ጦር ማለት ነዉ፡፡ ቀላል ኃይል አይደለም፡፡ ከዚህ ሁሉ ታጣቂ የተማረከዉ 105 ‹‹ኋላ ቀር›› የተባለ መሣሪያ ነዉ፡፡ የኋላ ቀሩ የመሣሪያዉ ዓይነት አልተነገረንም፡፡ ረሽ ነዉ? ዲሞትፎር ነዉ? ምንሽር ነዉ? ጎራዴ ነዉ? ቀስት ነዉ? እኛ እንጃ!

አራት ብሬል (መትርየስ መሆኑ ነዉ መሰል – አባባሉ ከሻዕቢያ የመጣ ነዉ) መያዙ ተነግሮናል፡፡ ከ61 መሰል ጥይት ጋር፡፡ አንድ የሞርተር ጥይትም ተማርኳል፡፡ ሞርተሩን መማረክ እንጂ አንድ የወደቀ የሞርተር ጥይት ማግኘት እንዴት ዜና ሊሆን ይችላል? የመከላከያ ሚኒስቴር ዓመታዊ የንብረት ቆጠራ ሪፖርት ይመስላል፡፡ 835 ታጣቂ ‹‹ተያዘ›› በተባለበት ዜና ‹‹ሁለት የወገብ ትጥቅ አግኝተናል›› ይላሉ፡፡ 835ቱ ታጣቂ ሁለት የወገብ ትጥቅ እየተዋዋሰ ነበር የሚታጠቀዉ? አራት ሽጉጥ ከ42 ጥይት ጋር፣ 71 የክላሽ ጥይት፡፡ ከ835 ታጣቂ…የነገረ ዉትድርና አዋቂዎች ፍረዱን፡፡

ሁለት ነገር አለ፡፡

አንደኛ እዉነት እዉነት የሚሸት ነገር ንገሩን፡፡ ‹‹835 የታጠቀ ኃይል በቁጥጥር ሥር አዋልኩ›› ብሎ ስለሁለት የወገብ ትጥቅ፣ ስለአራት ሽጉጥ… ምርኮ ይነግረናል? ንቀት ነዉ፡፡

ሁለተኛ፣ በእናታችሁ በቋንቋ አጠቃቀምም ተሀድሶ አድርጉ፡፡ ‹‹ ፀረ ሠላም ኃይሎች…፡፡›› ምንድነዉ ‹‹ፀረ ሠላም››ማለት? ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ካልሆነ በስተቀር የሰዉ ልጅ ሆኖ የሰላም ጠላት የለም፡፡ዉሸት ነዉ፡፡አንፃራዊም ነዉ፡፡ ‹‹ ይሁን›› ቢባል እንኳ ባለፉት ሃያ ምናምን ዓመቶች የሰለቸ፣ ዉጤት ያላመጣ አባባል ነዉና ሌላ ትቀይሩልን ዘንድ በትዕብትና በጀብዱ እንጠይቃለን፡፡ አናሳዝናችሁም?

‹‹ለጠላት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ…›› የሚል ነገርም አለበት፡፡ ‹‹ጠላት›› የሚለዉ ነገር በወታደራዊ አገላለፅ ተገቢ ቢመስልም በፖለቲካዊ አንድምታዉ ግን አክሳሪ ነዉ:: ወደድንም ጠላንም እነዚያ ሰዎች ወገኖቻችን ናቸዉ፡፡ በሀገሪቱ ዉስጥ ችግር አለ፤ በችግሩ አፈታት መንገድ/ አግባብ/አማራጭ… ላይ የተፈጠረ አለመግባባት ያመጣዉ ጣጣ ነዉ፡፡

ዉጊያ ማለት ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ የደረሰበት ያዉቀዋል፡፡ እነዚህ መሣሪያ ታጥቀዉ ጫካ ለጫካ፣ በረሃ ለበረሃ የሚንከታቱ ሰዎች እንደማናችንም ሕይወታቸዉን ይወዳሉ፡፡ መሣሪያ ታጥቀዉ ሲያምፁም በሕይወታቸዉ ላይ ፈርደዉ ነዉ፡፡ መሞት እንደሚችሉ አዉቀዉ፡፡ በገዛ ሕይወት ላይ እስከመፍረድ ያደረሰዉን ምክንያት መቀበልና መላ መፈለግ እንጂ ፣ በአመለካከት ልዩነት ያመፀን ወገናችንን ‹‹ጠላት›› እያልን የምናሳድደዉ ከሆነ በእሳት ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ ያለፈ ፋይዳ አይኖረዉም፡፡ በተለይ ለመንግሥት፡፡ እናም መንግስት ሆይ፣ ስለምትሰጠን መረጃና (ዜና)፣ ስለምትጠቀምባቸዉ ቃሎች ተጠንቀቅ፡፡ በዚያም አካባቢ የለዉጥ አየር ይንፈስ፡፡ አለበለዚያ ‹‹አመሉ ነዉ፣ ልማዱ ነዉ›› እያልን ሙድ እየተያያዝን መዝለቃችን ነዉ፡፡ መዝለቂያዉ ካለን…”


ዳውድ ኢብሳን በጨረፍታ
—-
ጸሐፊ: ተስፋዬ ገብረአብ
——
ዳውድ ኢብሳ ትውልዱ ሆሮ ጉዱሩ ነው። እንደ መለስ ዜናዊ የዊንጌት ተማሪ ነበር፡፡መለስን በሁለት አመት ይቀድመዋል፡፡ አራት ኪሎ ዩንቨርስቲ ገብቶ ስታትስቲክስ አጥንቷል፡፡ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ፍሬው ይባል እንደ ነበረ በወለጋ አሰተዳዳሪ በንጉሴ ፋንታ ስር የነበረው የደህንነቱ ቅርንጫፍ ለተሰፋዪ ወ/ስላሴ የጻፈው ሪፖርት ይጠቁማል፡፡

በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት ደርግ ዳውድን ለሁለት አመታት አሰሮ ፈቶታል፡፡ከእስር ሲለቀቅ ወደ ኦነግ የትጥቅ ትግል ገባ። ኦነግ በ1968 ሃያ ስምንት ማእከላዊ ኮሚቴ ስመረጥ ዳውድ አንዱ ሆነ ተመረጠ፡፡

በ1971 ኦነግ ትግሉን በምእራብ ኢትዮጵያ ለማሰፋፋት ይወሰናል። ዳውድ እና የኦቦ ሌንጮ ለታ ወንድም አባ ጫላ ለታ ዋናና ምክትል ሆነው የምእራቡን ትግል እንዲመሩ ይመደቡና በጥቅሉ 17 ሆነው በሱዳን በኩል አቋረጠው ወለጋ ቤጊና ጊዳሚ አካባቢ እንቅሰቃሴ ይጀምራሉ፡፡

ደርግ ይህን የኦነግ የምእራብ እንቅስቃሴ ለማፈን ትኩረት ሰጥቶ ማጥናት ይጀምራል፡፡ የጊዳሚ ወረዳ አሰተዳዳሪ ሂካ መሳዲ እና የወለጋ ክ/ሀገር አስተዳዳሪ ንጉሴ ፋንታ የትግሉን ጅማሮ ለማጨናገፍ አንድ መላ ይዘይዳሉ፡፡

በዳውድ ኢብሳ ይመሩ ከነበሩት 17 ታጋዮች የአንዱ ወንድም ዘካሪያስ ሾሮ ይባላል፡፡ ሂካ መሳዲ ዘካርያስን ጠርቶ ግዳጅ ይሰጠዋል።
“ወንድምህንና ጓደኞቹን ቤትህ ራት ጋብዛቸው፡፡ የምንሰጥህን መርዝ ምግቡ ውስጥ ትጨምርና ታበላቸዋለህ፡፡ ይህን የማትፈጽም ከሆነ ከእነ ቤተሰብህ ትገደላለህ! ከብትህ ይዘረፋል! መሬትህን ታጣለህ! ዘርህ ከምድረ ገጽ ይጠፋል”። ዘካሪያስ ግዴታ ሆኖበት እንደ ተስማማ የደህንነቱ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል፡፡

ዘካሪያስ ወንድሜን “እንዴት እገላለው” ብሎ አቅማምቶም ነበር፡፡

“ከቻልክ ወንድምህን ለይተህ እንዳይበላ አድርገው፡፡ ካልተቻለ ግን “አብሮ ይሙት! ወንድምህ አገር ሊያጠፋ የተቀጠረ ከሃዲ ነው” ፊት ለፊት ይነግሩታል፡፡
የገበሬ ልብስ የለበሱ ወታደሮች በአከባቢው አድፈጠው ዘካርያስ ሾሮ እንዳያመልጥ ይጠብቁት ነበር፡፡ ምግብ ውስጥ የሚጨመር መርዝ ከአዲሰ አበባ ተልኮ በንጉሴ ፋንታ በኩል ለሂካ መሳዲ ተሰጠ፡፡ ሂካ መሳዲ ለዘካርያስ አሰረከበው፡፡

ዘካርያስ ለወንድሙና ለጓደኞቹ የራት ግብዣ ጥሪ ከላከባቸው በሃላ በግ አርዶ ጥሩ ምግብ አዘጋጀ፡፡ በዚያን ሰሞን 17፥የኦነግ ታጋዮች ለሁለት ተከፍለው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ አባ ጫላ ዘጠኝ ራሱን ሆኖ በሌላ አቅጣጫ ይንቀሳቀሰ ነበር፡፡ ዳውድ እና ቀሪዎቹ ታጋዮች የዘካርያስን የራት ግብዣ ተቀብለው ማምሻው ላይ በገበታው ዙሪያ ተገኙ፡፡

ዘካርያስ ወንድሙን ለይቶ ለማስቀረት ሳይቻለው ቀረ፡፡ “አንተ ቆይ በሃላ ትበላለህ” ቢለው ወንድሙ አሻፈረኝ ብሎ ለገበታው ቀረበ፡፡ ወንድሙና ጓደኞቹ በመርዝ የተለወሰውን ምግብ ስበሉ ዘካርያስ የጎጆውን ምሰሶ ተደግፎ በትካዜ ይመለከታቸው ነበር፡፡

ዳውድ ከምግቡ ትንሽ ቀማምሶ ሲያበቃ ደጅ ጥበቃ ላይ የነበረውን ጓደኛቸውን ለመተካት ገበታውን ትቶ ወደ ደጅ ወጣ፡፡ ሌሎቹ መርዙን መብላቱን ቀጠሉ። ብዙም አልቆዩ። ታጋዮቹ ሰውነታቸው እንደ እሳት እያቃጠለ እየጮኽ ይወድቁ ጀመረ፡፡ ዘካርያስ የወንድሙን ሬሳ እጁ ላይ ታቀፈ፡፡ ዳውድ ብዙም የተመገበ ባይሆንም ከመመረዝ አላመለጠም፡፡

በጥበቃው ላይ እያለ ሰውነቱ ሲቃጠልበት ቅጠላ ቅጠልና አፈር እየቃመ ውሃ በብዛት ጠጣበት፡፡ ደግሞ ደጋግሞ አሰታወከ፡፡ ሆኖም ከመውደቅ አልዳነም፡፡ራሱን ስቶ እንደ ጓደኞቹ ከዘካርያስ ጓሮ ወደቀ፡፡

የገበሬ ልብስ ለብሰው በአከባቢው አድፍጠው ውጤቱን ይጠብቁ የነበሩት ወታደሮች በተያዘላቸው ቀጠሮ ዘካርያስ ቤት ሲደርሱ ሰባቱ ታጋዮች ሞተው ዳውድ ግን ነፍሱን እንደሳተ አገኙት፡፡ ዳውድን ይዘው ወደ ደምቢዶሎ ከነፉ፡፡ የኦነግን ሚስጢር ከእሱ ለማገኘት ፍላጎት ሰለ ነበራቸው ፈጣን ህክምና ሰጥተው ህይወቱን አተረፉት፡፡ ከደምቢ ዶሎ ወደ ነቀምት አዛዋውረውም ተጨማሪ ህክምና ሰጡት፡፡
ነቀምት ላይ እንዳገገመ ወደ እስር ቤት ወስደው ገልብጠው ይገርፉት ጀመር፡፡

የወለጋው የደህንነት ሪፖርት እንደሚገልጸው ከፍሬው አንደበት አንዳችም ሚሰጢር ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ሲያቅታቸው ወደ አዲሰ አበባ ወደ ማእከላዊ ላኩት፡፡ በቤንዚንና በቆሻሻ ውሃ የተሞላ በርሜል ውሰጥ እየደፈቁ መረመሩት፡፡ ዳውድ ለመሞት ዝግጁ ሰለ ነበር አንዳችም የተነፈሰው ነገር የለም፡፡ ደግመው ደጋግመው ማእከላዊና አለም በቃኝ እያመላለሱ በተለያዪ ማሰቃያ ሰልቶች እንደ መረመሩት የደህንነቱ መ/ቤት ሰነድ በዝርዝር ያብራራል፡፡

ዳውድ በአለም በቃኝ አምስት አመታት ታሰረ፡፡ ከመላመድ ብዛት ጠባቂ የነበረውን ፖሊስ ማግባባት ቻለ። ለህክምና ሲወጡም ከሁለት ባልደረቦቹ ጋር ከሆስፒታል አምልጦ ወለጋ ገባ፡፡ የቤንሻጉል ጫካዎች አቋረጠው ኦነግ ከአለበት ቦታ ለመድረስ የሁለት ሳምንት የሌሊት ጉዞ አድርገዋል፡፡ እሱ መርዝ በልቶ ሲማረክ ምእራብ ወለጋ ጫካ ውሰጥ የቀሩት አባጫላ ለታ እና ዘጠኝ ጓደኞቹ ከአንድ ብርጌድ በላይ ሰራዊት ሆነው ጠበቁት፡፡ የመሪያቸውን በህይወት መመለስ ማመን ያልቻሉት ታጋዮች በታላቅ ደሰታ ተቀበሉት!!
—–
ተስፋዬ ገብረአብ
የጋዜጠኛው ማስታወሻ
ገጽ 330-332

Via: Dábessá Gemelal